የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ከተቋቋመ 18 ዓመታትን አስቆጥሯል። የተቋቋመው ማቲዎስ የተባለውን የአራት ዓመት ልጃቸውን በካንሰር ሕመም ምክንያት ባጡት አቶ ወንዱ በቀለና ባለቤታቸው፤ እንዲሁም፣ ከሌሎች መሥራች አባላት የጋራ ትብብር ነው።
ሶሳይቲው ከተቋቋመ ጀምሮ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች አጠቃላይና ለካንሰር አጋላጭ ከሆኑት መንስኤዎች መካከል፣ መከላከልን ጨምሮ፤ ሕክምናው በሚገኝበት ዙሪያ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል።
በሌላ በኩልም፣ ለካንሰር ሕክምና አዲስ አበባ መጥተው መጠለያና ገንዘብ ያጡትንም ሕሙማን በነጻ ማረፊያ በመስጠትና የህክምና ወጪያቸውን ሙሉ በሙሉ በመሸፈን ሕክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች ማዕከል አቋቁመዋል። ለዚህ ተግባራቸውም፣ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የተለያዩ ሽልማቶችን ሰጥተዋቸዋል። በሶስት ዓመታት ውስጥም አምስት አለም አቀፍ ሽልማቶችን በማግኘት በጎነትና ማህበረሰብን ማገልገል ለራስ መሆኑንና ራሱም እንደሚከፍል አሳይተዋል። የሶሳይቲው መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንዱ በቀለ የዛሬው የሕይወት ገጽታ አምዳችን እንግዳ አድርገናቸዋል።
አቶ ወንዱ በቀለ ከዛሬ 67 ዓመት በፊት በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በፊት ደደር በሚባል ወረዳ ቡርቃ በሚባል አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት። ከሰፊ ቤተሰብና ከብዙ እህትና ወንድሞች ጋር ያደጉት አቶ ወንዱ አባታቸው በገጠርና በከተማ ትልልቅ ቤት፤ እንዲሁም የግብርና ቦታ የነበራቸው ነጋዴ ስለነበሩ በአስተዳደጋቸው ያንን ያህል ችግር ያዩ አይደሉም። በሌላ በኩልም አባታቸው እጅግ ሰው አክባሪ፣ ሀይማኖተኛና በአካባቢውም ትልቅ ሰውና የተከበሩም ነበሩ።
“….. እንግዲህ ውልደቴና እድገቴ ደደር የሚባል አካባባቢ ነው። አባቴ ሀብታም ከሚባሉት ሰዎች ተርታ የሚሰለፉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይና የቤተክርስቲያን አገልጋይ ናቸው። እስከ አሁን ከእሳቸው ባህርይ በጣም ደስ የሚለኝ ብሎም የምኮራበት ነገር ከገጠር ወደ ከተማ በምንሄድበት ጊዜ በመንገድ ላይ የሙስሊም መቃብር፣ እንዲሁም መስኪድ ሲያዩ ከበቅሏቸው ላይ በመውረድ የሚገባን ክብር ሰጥተው ነበር የሚያልፉት። ይህ ነገራቸው ደግሞ እኔም ላይ ቀርቷል፤ በጣምም ነው የሚገርመኝ” በማለት ነው የልጅነት ጊዜያቸውን የሚያስታውሱት።
አቶ ወንዱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ደደር በግራዝማች አብርሃ ግዛው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። አባታቸው ለትምህርት ልዩ ትኩረትና ክብር የነበራቸው በመሆኑ ልጆቻቸው በትምህርት ቆይታቸው እንዳይቸገሩ በትምህርት ቤታቸው አቅራቢያ ቤት በመከራየት እንድታግዛቸው አክስታቸውን አብረው በማስቀመጥ፣ ቀለብ በመስፈርና አስፈላጊውን ነገር ሁሉ በማሟላት ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያደርጓቸው ነበር።
“…. አባቴ ባይማሩም ለትምህርት ልዩ ፍቅር ነበራቸው፤ በትምህርት መቀለድ በፍጹም አይቻልም፤ ከዚያ የተነሳም እኔም እህትና ወንድሜም ከተማ ላይ አጎት እያለን እንኳን ላይመቻቸው ይችላል በማለት ቤት ተከራይተው አክስታችን ከእኛ ጋር እንድትሆን አድርገው ነው ያስተማሩን። የትምህርት ውጤታችን በሚመጣበት ጊዜም ይከታተሉ፤ ደከም ብለን ስንገኝም በጣም ይቆጡ ነበር” በማለት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያሳለፉበትን ሁኔታ ይናገራሉ።
አካባቢው ላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስላልነበር ከስምንተኛ ክፍል በኋላ ትምህርትን መቀጠል አልተቻለም፤ አቶ ወንዱ ታላቅ ወንድማቸው ቀደም ብሎ አዲስ አበባ ገብተው በመማር በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይሰሩ ስለነበር አቶ ወንዱና እህታቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ወንድማቸው ጋር ሆነው ለመማር አዲስ አበባ ገቡ። በምስራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ።
“…… ምናልባት ወንድሜ ቀደም ብሎ አዲስ አበባ ገብቶ ባይሆን ኖሮ የመማር እድሌ አናሳ ይሆን ነበር፤ ነገር ግን ወንድሜ በመኖሩ ከእህቴ ጋር መጥተን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በጥሩ ሁኔታ አጠናቅቄ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀልኩ። በዩኒቨርሲቲውም ፐብሊክ አድምንስትሬሽንና ፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ጥምረት (ሥነ መንግሥት) የሚባል ትምህርት ክፍል ተመድቤ፤ በመልካም ሁኔታም ተከታትዬ በ1972 ዓ.ም መጨረሻ የመጀመሪያ (ቢኤ) ዲግሪዬን አግኝቻለሁ” ይላሉ።
አቶ ወንዱ ከተመረቁ በኋላ በምደባ ወደ ድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በረዳት የአስተዳደር መኮንንነት ተመድበው በስምንት መቶ ብር ደመወዝ ስራቸውን “ሀ” ብለው ጀመሩ። በወቅቱ ስምንት መቶ ብር ብዙ ነገሮችን የሚያደርግ በቂ ደመወዝ የነበረ ቢሆንም እርሳቸው ግን አንድ ስራ ብቻ ይበቃኛል ብለው አልተቀመጡም፤ ይልቁንም በከተማዋ ሁለት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ድሬዳዋ ካምፓስ በመሄድ በትርፍ ጊዜያቸውም ያስተምሩ ነበር።
“…… አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በነበርኩበት ጊዜ በትርፍ ሰዓት የአየር ተቆጣጣሪ በመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ እሰራ ስለነበር ከትምህርት ጋር የተጨናነቀ ሰዓት ነው የነበረኝ። በዚህ ምክንያት ደግሞ የምፈልገውን ያህል አልተዝናናሁም። ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ስሄድ ግን አንደኛ የገንዘብ ችግር የለብኝም። ሁለተኛ ጊዜውም ነበረኝ። በደንብ አድርጌ ተዝናንቻለሁ። እናም በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት” በማለት ትዝታቸውን ይናገራሉ።
አቶ ወንዱ በስራ ላይ እያሉ የውጭ አገር (ቡልጋሪያ) የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት እድል ይመጣል። ውድድር ይደረግ ተብሎም ተወዳድረው ከተወዳዳሪዎቻቸው የተሻሉ ሆነው በመገኘታቸው እድሉ ይሰጣቸዋል። በእድሉ ደስ ቢሰኙም ብቻቸውን ወስነው ግን ለመሄድ አልፈለጉም። እናም ወደ አባታቸው ሄደው ያገኙትን እድል በመናገር ”ሄጄ ልማር ነው” ብለው ፍቃድ ይጠይቃሉ። የአባታቸው መልስም “በፍጹም መሄድ የለብህም። በተማርከው መቼ ገና ሰራህና ነው። እኔም ደግሞ አግብተህ የልጅ ልጅ ማየት እፈልጋለሁ። ስለዚህ መሄድ አትችልም” የሚል ሆነ። በሁኔታው ትንሽ ቅር ቢሰኙም ከአባታቸው ቃል ግን መውጣትን አልመረጡምና የትምህርት እድሉን ያሳልፋሉ።
ትዳር በወላጅ ምርጫ
ቡልጋሪያ የውጭ የትምህርት እድል አግኝቼ ልሄድ ነው ብለው የአባታቸውን ፍቃድ ለመጠየቅ የሄዱት አቶ ወንዱ የጠበቃቸው፤ ትዳር መስርተህ ልጅ ውለድ የሚል ሆነ። በወቅቱ የእሳቸው ምላሽ ዝግጁ አይደለሁም፤ ያዘጋጀኋት እጮኛም የለችኝም የሚል ነበር። አባታቸው ግን ይህ ምክንያት ሆኖ ሀሳባቸውን አላስቀየራቸውም። ይልቁንም እኔ የመረጥኩልህ ያዘጋጀሁልህ ጥሩ ልጅ አለች፤ ታገባለህ የሚልነበር። ከአባታቸው ቃል መውጣት ፈተና የሆነባቸው አቶ ወንዱም እየተገረሙ ወደ መጡበት ሄዱ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የታጨችላቸውን ሴት ምንም እንኳን እሳቸው ባያውቋትም አብራቸው የምትሰራ፣ እሷ በደንብ የምታውቃቸው ነበረች። ልጅቷ በታላላቅ ወንድሞቻቸው ሚስቶችም ተገምግማ አልፋለች። አባታቸውም ትሁን ብለው አጽድቀዋል። ነገር ግን አቶ ወንዱ የማግባት ፍላጎት ስላልነበራቸው ነገሩን ለማፋረስ ብዙ ለፉ። የእህል ውሃ ነገር ሆኖ ግን አንዱም ሙከራቸው ተቀባይነት አላገኘም። እንደውም ነገሩን አጠነከረው። በመጨረሻም የማይቀረው ሆነና ጋብቻው ተፈጸመ። ጋብቻውም የባለቤታቸው ቤተሰቦች ባሉበት ደሴ በዋናነት ከተፈፀመ በኋላ የአቶ ወንዱም ቤተሰበች ድሬዳዋ ድል ያለ ድግስ ደግሰው የሠርጉ ሥነ ሥርዓት ሆነ ። እነሆ ዛሬ ለ38 ዓመታት ከወይዘሮ አምሳለ በየነ ጋር በትዳር አለም ቆይተው፣ከማቲዎስ ወንዱ ጋር ሶስት ልጆችን አፈርተውና የልጅ ልጅ አይተው በመኖር ላይ ናቸው።
በ1976 ዓ.ም ትዳር ከመሰረቱ በኋላ በ1977 ዓ.ም ወደ ቡልጌሪያ ለአጭር የትምህርት ኮርስ ሄዱ። እዛም 10 ወራትን ከቆዩ በኋላ በድጋሜ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ቢጠየቁም እሳቸው “አሁን ትዳር መስርቻለሁ። ባለቤቴ ህጻን ልጅ ይዛለች። አባቴም አልፈቀደልኝም” በማለት ወደ አገራቸው መመለስን መረጡና ተመለሱ።
“…… በወቅቱ ትዳር መስርቻለሁ። ልጅ ወልጄም ልጁ ገና ህጻን ነው። አባቴም እድሜያቸው ስለገፋ እነሱን ትቶ ለተጨማሪ ጊዜያት መቆየት ሞት ሆነብኝና አይ ይቅርብኝ፤ አገሬ ተመልሼ ስራዬን ልስራ ብዬ ተመለስኩ” ይላሉ።
ወደ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ሲሄዱ ግን የገጠማቸው ነገር ሌላ ነበር። ተምረው ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ ለእሳቸው ይሆናል የተባለው የተሻለ ቦታ ያን ያህል ከፍ ያለ ደመወዝ የሚከፈልበት አልሆነም። እናም እዛ ማደጋቸው ትርጉም የሌለው መሆኑን ነግርዋቸው አዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ “ኢትዮጵያ ቃጫ ውጤቶች ፋብሪካ” አስተዳዳሪ ሆነው እንዲሰሩ ተመደቡ።
“……. በወቅቱ አዲስ አበባ መግባቴ በጣም አስደስቶኝ ነበር። በግቢው ውስጥም ጃፓኖች የሰሩት በጣም ቆንጆ ቤትም ነበር። እና ከባለቤቴ ጋር ልጃችንን እያሳደግን ከፍ ባለ ደስታ መኖር ጀመርን። ይሄ ኑሯችን ግን ከሁለት ዓመት በላይ ሊዘልቅ አልቻለም። ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አዲስ ተቋቁሟል፤ መንግስትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል። ነገር ግን ሰራተኞችና አሰሪዎች ስላልተስማሙ ወደ ስፍራው ሄደህ አረጋጋ ተብዬ ተመደብኩ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
በወቅቱ በጣም የተናደዱት አቶ ወንዱ ከብዙ አመት ስራ በኋላ ገና አዲስ አበባ መግባቴ ነው። ደግሞ ካገባሁም ቅርብ ጊዜ ነው። ውጪም ሄጄ ስለነበር ከባለቤቴ ጋር ጊዜ አልነበረኝም። እናም ወደ ስፍራው መሄድ አልችልም የሚል መልስ ሰጡ። ነገር ግን “ከአሁን በኋላ አናስቸግርህም። ይህንን ኃላፊነት ብቻ ተወጣልን። ከሁለት አመት በላይም አትቆይም። ባለቤትህም እዛው የቆዳ ፋብሪካ ላይ ስራ እንድትጀምር እናደርጋለን” ስላሏቸው ባለቤታቸውን ይዘው ኮምቦልቻ መግባታቸውን ያስታውሳሉ።
“……ኮምቦልቻ በጣም ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ስራዬንም ጥሩ አድርጌ እየመራሁት ነበር። በመካከል የ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ሆነ። ኢህአዴግ ኮምቦልቻ ሊገባ ሲል የውጭ አገር ዜጎችም ስለነበሩ አውሮፕላን ተልኮ ውጡ ተባልን። “…. እኔ ግን በወቅቱ ይህንን የመሰለ ትልቅ የአገር ሃብት ዝም ብዬ ሜዳ ላይ ጥዬ መሄድ አልችልም አልኩና ከአለቃዬና ከተወሰኑ ሠራተኞች ጋር ቀረሁ። አንሄድም ብለን የቀረን ጥቂት ሰዎች እጃችንን ሰጥተን ፋብሪካውን አስረከብን። ይህም ቢሆን ግን ማን እንደመታው ሳይታወቅ ፋብሪካው መንደድ ጀመረ። ከዛም ሌሊቱን ሙሉ እሱን አጠፋን። በኋላ ሰራተኞች እንዳይቸገሩ በማለት ከባንክ ገንዘብ አውጥተን ደመወዛቸውን እየከፈልን፣ ዳቦ እያደልን ባለንበት ጊዜ ሰራተኛው በተዛባ መረጃ ተነሳስቶ እንድንታሰር ሆነ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
እዛው ኮምቦልቻ አንድ ወር ሙሉ በእስር ያሳለፉት አቶ ወንዱ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ምንም ዓይነት ስራ አልሰራም ብለው ተማረሩ። ነገር ግን ንዴታቸው ሲበርድላቸው አጉስታ ጨርቃጨርቅ ተመድበው መስራት ጀመሩ። ነገር ግን ሲመሩት ከነበረው ፋብሪካ አንጻር በጣም ትንሽ ሆነባቸው። እናም ከሶስት ወር በላይ መስራት ሳይችሉ ቀሩ። በመቀጠልም ወደ አደይ አበባ እንዲመደቡ ሆነና ለአምስት አመታት ያህልም
እዛ ሰሩ። አደይ አበባ ያለው ስራ ትርፋማ ያልሆነ የሰራተኞች ደመወዝ ለመክፈል እንኳን ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ገጠማቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰራተኞቹ የስራ ስነምግባር ሊያሰራቸው ባለመቻሉ በተለያዩ ሁኔታዎችና ፋብሪካዎች ውስጥ በመዘዋወር ለ13 ዓመታት የሰሩበትን የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ እርግፍ አድርገው በመተው ወደ ትምባሆ ሞኖፖል ዞሩ።
“….. ትምባሆ ስመጣ እንደ ጨርቃ ጨርቁ አይነት፣ በተለይም እንደ አደይ አበባ ችግር አልገጠመኝም። እንደውም ትምባሆ በጣም አትራፊ ከመሆኑ የተነሳ ለሰራተኛው የሚከፍለውም አያጣም። የተሻለ የስራ ሁኔታ ውስጥ ነው የገባሁት ማለት ይቻላል” ይላሉ የትምባሆ ሞኖፖል የስራ ቆይታቸውን ሲያስታውሱ።
አቶ ወንዱ ትምብሆ ሞኖፖል እስከሚገቡ ድረስ ሁለት ልጆችን ወልደው ነበር። ወንድና ሴት ስለነበሩም ተጨማሪ ልጅ እወልዳለሁ የሚልም እቅድ አልነበራቸውም። ነገር ግን የወዳጆቻቸውና የሚያውቋቸው ሰዎች ግፊት ሶስተኛ ልጅ እንዲጨምሩ አስገደዳቸው። የሰው ምክርና ግፊት ሲበዛም እሳቸውና ባለቤታቸውም በሁኔታው ተገፋፉ። እናም ማቲዎስ ወንዱ ተረገዘ ይላሉ ሁኔታውን ሲያስታውሱ።
ሁለተኛዋ ሴት ልጅ በተወለደች ከአስር ዓመት በኋላ የመጣው ማቲዎስ ብዙ ነገሮችን ወደ ህይወታቸው አመጣ። “…..በጣም ይገርምሻል፣ ማቲዎስ ሳይወለድ እንኖር የነበረው አዋሬ ነበር። ማቲ ሲወለድ ግን አዲስ ቤት ሰርተን ቦሌ ሚካኤል ገባን። ቤት መስራት ብቻ ሳይሆን የቤት እቃዎቻችን ሁሉ በአዲስ መልክ ተቀየረ። ልጁ በተወለደ ዕለትም አዲሱ ቤታችን ገባን” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
በጣም ደስተኛና ተጫዋች፤ የቤቱም አይን ሆነ ማቲዎስ። እስከ ሁለት አመት ልደቱ ድረስም ጉንፋን እንኳን ይዞት የማያውቅ ልጅ ነበር።
“….. ማቲ ከመታመሙ በፊት ስለ ካንሰር ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም። ሁለተኛ አመት ልደቱን ባከበረ በሳምንቱ መነጫነጭ፣ ግድግዳ ላይ መታከክ ጀመረ። ሁኔታው ግራ ስላጋባንም ወደ ሆስፒታል ይዘነው ሄድን። ዶክተሩ የተለያዩ ምርመራዎችን አደረጉና የደም ካንሰር መሆኑን ነገሩን። በጣም ነው የደነገጥነው። የምንይዝ የምንጨብጠውን አጣን” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
በኋላም ህክምናውን በብቸኝነት ወደ’ሚሰጠው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲሄዱ የተነገራቸው የማቲዎስ ቤተሰቦች ልጅቻውን ይዝው ጥቁር አንበሳ ሄዱ። የጥቁር አንበሳ የታካሚ ብዛት ብቻ ብዙ ለወረፋ ዳረጋቸው። ለአስር ቀናት ያህልም ድንገተኛ ክፍል፣ አግዳሚ ወንበር ላይ ካስተኙት በኋላ የመኝታ ክፍል ተገኝቶለት አልጋ ያ። አልጋው ይገኝ እንጂ በሆስፒታሉ መድሃኒትም ሆነ የህክምና ባለሙያ ብዙም የለም። የማቲዎስ ቤተሰቦች ግን እውቀታቸውና ገንዘባቸው የቻለውን ሁሉ ማድረግ ቀጠሉ። በውጭ አገር ያሉ ቤተሰቦቻቸው ሁሉ ያለውን ነገር እየተከታተሉ፤ የሚያስፈልገውን መድሃኒት እየላኩ ማቲዎስን ከካንሰር ለማዳን ለፉ። ግን የእግዚአብሔር ፍቃድ ሳይሆን ቀርቶ ከሁለት አመት ሶስት ወራት ህክምና በኋላ ወደ አሜሪካን ሄዶ የመቅኔ ቅየራ ሊያደርግ ሲል እዚሁ ህይወቱ አለፈች።
የዛ የቤተሰቡ ደስታ ፍልቅልቅና ቆንጆ የነበረው የማቲዎስ ወንዱ በካንሰር በሽታ ህይወት ማለፍ በቤተሰቡ ላይ ልብ የሚሰብር፤ ሁሌም ከሆድ የማይወጣ ሀዘን ቢሆንም ለሌሎች ብርሃን እንዲሆኑ በተለይም በካንሰር ህመም ተይዘው በአቅም ማነስ ምክንያት ከህክምናና ከመድሃኒት ጋር ሳይገናኙ ስቃያቸውን አይተው ለሚያልፉ ህጻናትና ጎልማሶች ብርሃን ይሆኑ ዘንድ መንገዱን አሳያቸው።
“…… ጥቁር አንበሳ ልጃችንን እያስታመምን ባለንበት ጊዜ ወንድሜ ለማቲ የሚሆን መድሃኒት አገር ውስጥ ስለሌለ በብዛት ከውጪ ይልክ ነበር። እዛ ደግሞ ይህ እድል የሌላቸው በርካታ ህጻናትን የያዙ ወላጆች ይሰቃያሉ። እና ከማቲ በተረፈ መድሃኒት ልጆቻቸው እንዲታከሙላቸው ወረፋ እስከመያዝ ይደርሱ ነበር። ይህ ለእኔ ትልቅ የልብ ስብራት ነበር” ይላሉ ሁኔታውን ሲያስታውሱ።
ልጃቸውን ለማሳከም ያላቸውን ሁሉ ሸጠው የጨረሱት አቶ ወንዱና ቤተሰባቸው ምንም እንኳን በወቅቱ ልጃቸውን ማዳን ባይችሉም እግዚአብሔር የፈለገው ነገር አለ በማለት ልጃቸውን ማጣታቸውን ተቀብለው ፊታቸውን ወደ ሌላ ነገር አዞሩ። በዚህም “ማቲዎስን ማዳን ባንችልም ሌሎች ማቲዎሶችን እናድን” በማለት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በካንሰር ህመም ምክንያት የሚሰቃዩ ወገኖችን ለመደገፍ ተነሱ። በዚህም መሪሩን ሀዘን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር የተለየ ሥራ መሥራት ጀመሩ። ይኽንን በማድረጋቸው በመላው ዓለም አድናቆትን አትርፎላቸዋል።
“…… መስከረም ወር 1996 ዓ.ም ልጃችንን ከቀበርን በኋላ ምን እናድርግ? ምንም ገንዝብ የለንም። ግን እንዴት ነው ህልማችንን እውን የምናደርገው? ስንል አሰብን። በወቅቱም ከማቲ ኪስ አንድ ብር አገኘን፤ አሜሪካን አገር ሄዶ እንዲታከም ያመቻችልን ወዳጃችን ቤታችንን አይቶ ሁለት መቶ ብር ሰጠን። አንድ ፈረንጅ ደግሞ 2 መቶ ዶላር ሰጠን። ይህችን ብር ይዘን መኖሪያ ቤታችንን አካፍለን ስራውን ጀመረን” ይላሉ።
በማቲ መድሃኒት ታክመው የዳኑ ሰዎችን ሲያዩ በቃ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አድሮ አንድ ሊያደርግ ያሰበው ነገር አለ በማለትም ችግሩን ተቋቁመው ስራውን ለመስራት የማቲዎስ ወንዱ የካንሰር ሶሳይቲን እውን አደረጉ።
በአሁኑ ወቅት በተለይም በቤት ኪራይ ላይ ብዙ ችግር እየደረሰባቸው፣ በዓመት ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ እየከፈሉ፤ የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችን ደጅ እየጠኑ በካንሰር በሽታ ምክንያት የሚሰቃዩ በአቅም ማነስ ህክምናና መድሃኒት ለማግኘት የሚቸገሩ ከ142 በላይ ለሆኑ ህጻናትና ሴቶች ከነቤተሰቦቻቸው መጠለያ በመስጠት በቀን አራት ጊዜ በመመገብ የህክምናና የመድሃኒት፤ እንዲሁም የትራንስፖርት ወጪያቸውን በመቻል እያስተዳደሩ ይገኛሉ።
“…..በዓመት ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ ለቤት ኪራይ እንከፍላለን። እኔ ለዚህ ስራ እግዚአብሔር መርጦኛል ብዬ ስለማሰብ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ። እስከ አሁንም ባደረኩት ብዙ ህጻናትና ወጣቶች ከአስከፊው የካንሰር ህመም ድነው ህልማቸውን ሲኖሩ እያየሁ ነው። ነገር ግን ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ፣ እኛ ደግሞ በምንፈልገው ወይም በምንችለው ልክ ለጋሾችን እያስተባበርን እንዳንሰራ የቤት ችግር ፈተና ሆኖብን እዚህ ደርሰናል” በማለት የችግሩን ግዝፈት ያስረዳሉ።
ጤናማ አፍሪካ (Healthy Africa)
የዚህ ፕሮጀክት አላማ ሰው እንዳይታመም፣ በተለይም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እየደረሰ ያለውን ጉዳት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠር ላይ መስራት ነው። ሌላው ደግሞ ደሃው የህብረተሰብ ክፍል ከታመመ በነጻ እንዲታከም፣ ሀብታሙ ደግሞ በደንብ የሚከፍልበት የጤና ተቋም በአገራችን እውን ማድረግ ነው። ይህ ፕሮጀክት ”ደሃና ወጣት ተኮር” ነው የሚሉት አቶ ወንዱ መንግስት ቦታ ከመስጠት በተጨማሪ በጀት መድቦ የሚያስተዳድረውም ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም ደሃ መጥቶ የተጠየቀውን መክፈል ስላቃተው ብቻ ከበሽታው ጋር መኖርና ማቆ መሞት የለበትም። ስለዚህ ሰዎች ሳይታመሙ እንዲጠነቀቁ የሚያደርግ፤ ችግሩ ከመጣ በኋላ ደግሞ ሰዎች ተገቢውን ህክምና በቶሎ አግኝተው ከሞት የሚድኑበትን ተቋም መፍጠር ህልማቸው ስለመሆኑ ይናገራሉ።
ይህ ህልሜ ሊሳካ የሚችለው ግን በተለይም የመንግስትን ትኩረት ማግኘት ከቻልኩ ብቻ በመሆኑ፤ ይህንን የህብረተሰብ ጤና የሚያሻሽል፣ ብሎም መንግስት ካለችው ጥሪት ብዙ እንዲያወጣ የሚያደርገውን የጤና ዘርፍ ማገዝ ሲችል ብቻ ነው ይላሉ አቶ ወንዱ።
“….. በአገር ውስጥም በውጪ አገራትም ይህንን ስራ በሙያቸው መደገፍ የሚችሉ በርካታ ባለሙያዎች አሉኝ። የእኔ ችግር የመስሪያ ቦታ ነው። ይህንን ነገር የሰራን ዕለት የልጄንም ሀዘን ቁጭ ብዬ አለቅሳለሁ ፤ ከዛ በኋላ በእለቱም ብሞት አይቆጨኝም ” ይላሉ።
“……ካንሰርም፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ በተለይ በእኛ አገር ሁኔታ ሀብታሙን ደሃ፤ ደሃውን ደግሞ ይበልጥ ደሃ የሚያደርጉ ናቸው። እኔም በዚህ ዙሪያ ከፍ ያለ ጥረትን የማደርገው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ባልችል እንኳን አገሬንና ደሃውን ህዝቤን ለመደገፍ በማሰብ ነው”።
የሆስፒታሎቸን አቅም የማሳደግ ስራ
ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሳንባ ካንሰር ህክምና የሚሰጥባቸውን 15 ክፍሎች ለታማሚዎችና ለህክምና አሰጣጡ ምቹ እንዲሆኑ አድርጓል። በ7 ሚሊየን ብር ገደማም ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለን የብሮኖስኮፒና ኢባስ የህክምና ማሽን ሳይቀር አሟልቷል። አሁንም እየረዳ ነው። ሌላው ፔን ፕላስ (PEN Plus) ፕሮጀክት ሙከጡሪ፣ ኦሮሚያ ላይ እና አዲስ ዘመን፣ አማራ ክልል ያሉ ሆስፒታሎችን አሟልቶ የህክምና መሳሪያዎችን ከአሜሪካን አገር አስመጥቶ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እንዲያክሙበት እያመቻቸን ነው።
የማህጸን ጫፍ ካንሰርን በተመለከተ በ1 ሺ 3መቶ የጤና ጣቢያዎች ላይ ምርመራው እንዲደረግ የሆነው በማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ አማካይነት ነው።
ያለፉትን 18 ዓመታት ሲያስቡ ምን ይሰማዎታል
ሶሳይቲው በእስከ አሁን ሂደቱ የሰራውን ስራ ሳስበው ይገርመኛል። ዛሬ ከአንቺ ጋር ቃለ ምልልስ እያደረኩ ለኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አንድ ዶክተር ቀጥረን ስራ አስጀምረናል። ደመወዝ የምንከፍከለው እኛ ነን። ጤና ጥበቃን በከፍተኛ ሁኔታ እናግዛለን። የማህጸን ጫፍ ካንሰር ምርመራ ለሁሉም በነጻ እንዲሰጥ ያደረገው ይህ ሶሳይቲ ነው። ይህም ቢሆን ግን ቤት ማጣቴ ለህዝቤ ከዚህ በላይ እንዳልሰራ ቅፍድድ አድርጎ ነው የያዘኝ።
እስከ አሁን በሆነው እግዚአብሔር ይመስገን፤ ወገኔን የማገልገል እድል አግኝቻለሁ። ድርጅቱም እኔ እንኳን ባልኖር ራሱን ችሎ ለወገን የሚያደርገውን ድጋፍ መቀጠል በሚያስችለው ቁመና ላይ ነው የሚገኘው። ነገር ግን ከዚህ የበለጠ ተጠናክሮ የመንግስትን ሸክም ሊያቃልል፤ የህብረተሰቡንም ስቃይ ሊፈታ ሲችል በመስሪያ ቦታ ችግር ምክንያት በጣም ከአቅሙ በታች እየሰራ ነው ያለው።
ነብይ ባገሩ ……
አቶ ወንዱ በካንሰር ህመም ትንሹን ልጃቸውን ሳይጠግቡት ከተለዩት በኋላ የትኛዋም ኢትዮጵያዊ እናት ልጇን በካንሰር በሽታ ማጣት የለባትም በማለት የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ የብዙ ህጻናትን ተስፋ መልሰዋል። እናቶችን ደስ አሰኝተዋል። ይህም ቢሆን ግን በአገር ውስጥ ያገኙት እውቅና ወይም ድጋፍ የስራቸውን ያህል ሚዛን የሚደፋ፤ የድካማቸውን ያህል ደስ የሚያሰኝ አይደለም። እሳቸው ለአገሬ መቼም አልደክምም፤ ለወገኔ በምችለው አቅም ሁሉ እደርሳለሁ በሚል የማይናወጥ አላማ ሩጫቸውን አላቆሙም።
እኛ በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኖብን ተገቢውን እውቅና አንስጣቸው እንጂ ስራቸው የገባቸው በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ክብርና ሽልማትን እየሰጧቸው ነው። ከ2010 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ብቻ አምስት ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ኒውዮርክ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ኢንብለር ቪዥን አዋርድ፤ እንዲሁም፣ አሜሪካ በሚኖሩ ከ5ሺ በላይ (በሕክምናና የተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ) ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከተቋቋመው ፒፕል ቱ ፒፕል ሽልማትን አግኝተዋል።
“…..በተለይ ፒፕል ቱ ፒፕል የሰጠኝ ሽልማት ልጄ ማቲ በሞተበት ቀን፣ ህይወቱ ባለፈችበት ሰዓት ላይ መሆኑ እጅግ አስገርሞኛል። ከማስገረምም በላይ እግዚአብሔር ለህዝቤ አንድ የሆነ ነገረ እንድሰራ ፈልጓል ማለት ነው የሚል መልዕክትም ሰጥቶኛል” ይላሉ።
ሌላው ከ1ሺ 2መቶ በላይ አባላት ያሉት የአለም ካንሰር ድርጅት ”ሶስት ምርጥ ስራ አስፈጻሚዎች” ብሎ ሲመርጥ እርሳቸው አፍሪካን፣ በተለይም ኢትዮጵያን ወክለው መመረጣቸውን ይናገራሉ። እንዲሁም፣ የአለም ጤና ድርጅት በ2020 ከአፍሪካ ከሸለማቸው ጥቂት ሰዎች አንዱም ነበሩ።
ነገር ግን፣ አቶ ወንዱ የካንሰርን ህመም ለመከላከል ብሎም ታማሚዎችን ቢያንስ ህክምናቸውን ሳይቸገሩ እንዲያገኙ ለማድረግ እያደረጉ ያለውን ጥረት በሚፈለገው ልክ ተመልካችና ደጋፊ ማጣቱ ቅር ያሰኛቸዋል። “ሶሳይቲውን መደገፍ አገርና ህዝብን መደገፍ ነው። በርካታ ወጣቶች በሱስ ተጠምደው በለጋ እድሜያቸው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ህይወታቸውን እያጡ ነው። ይህንን መቀየር የሚቻለው ደግም እኛው በእኛው መረዳዳት ስንችል ነው” በማለት ሃሳባቸውን ይገልጻሉ።
መልዕክት
አቶ ወንዱ በበጎ ስራቸው ዓለምን በሙሉ መዞር ችለዋል። ነገር ግን በሄዱበት ሁሉ የሚያዩትን ነገር ”ምነው በአገሬ በሆነ …” በማለት ይመኛሉ። በተለይም በህክምና ዘርፍ። “…. የእኔ አገር ውብ ናት፤ ሁሉ ነገር ያላት። ነገር ግን በእኛ ስንፍና፣ በተለይም ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን አስቀድመን መከላከል ስንችል በከንቱ ራሳችንን እየገበርን ነው። በመሆኑም ህዝቤ በመረጃ ራሱን አደራጅቶ፣ ራሱን የሚጠብቅ ሆኖ ማየት ምኞቴ ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ሲታመም ሳይሳቀቅ የሚታከምበት፤ መድሃኒት አግኝቶ የሚፈወስበት ማዕከል እውን ሆኖ ባይ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል። ለዚህ ግን ከመንግስት ጀምሮ ሁሉም በሚችለው አቅም ሊሳተፍ ይገባል” በማለት መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም