ቆፍጠን ያሉ ናቸው፤ በውትድርና ሕይወት ውስጥ ያለፉ ስለመሆናቸው የሰውነታቸው ተክለ ቁመና፣ የቢሯቸው ውበትና ንፅህና፣ የፋይል አሰዳደራቸው ይናገራል።ሁሉ ነገራቸው ጥንቅቅ ያለ ነው።ንግግራቸው የተረጋጋ፤ ጨዋታቸው የሰከነ ነው።ህይወት እንደ ገብስ ቆሎ ፍትግ፤ እንደ ሸንኮራ አገዳ ምጥጥ አድርጋ ልትተፋቸው ስትማስን፤ እርሳቸው ግን ሰንኮፎችን ሁሉ ነቃቅለው የስኬት መንገድን በራሳቸው ጥረት ተቆናጠዋል።በቤት አባወራነትም የተመሰገኑ፤ ለልጆቻቸውም አርዓያ ስለመሆናቸው ይነገርላቸዋል።ይህን ጥረታቸውንና ጥንካሬያቸውንም አብረዋቸው ለሚሰሩ የሚያካፍሉና ከሰው ጋር አብሮ ማደግን አብዝተው የሚመኙ ስለመሆናቸውም እንዲሁ።
ሰውየው የዋዛ አይደሉም ችግር ማረፊያ ሊያደርጋቸው ፈልጎ ወደ እርሳቸው ሄደ።እርሳቸው ግን በመልካም አጋጣሚ ቀይረውታል።‹‹ቅቤ እንደምን ጣፈጥሽ ቢሏት ተገፍቼ›› ይሉት ብሂል፤ እርሳቸው ከሥራ ገበታቸው መገፋታቸው፤ የተስፋ መቁረጥ ሳይሆን የጥንካሬ ምንጭ ሆኗቸው መገፋታቸው የስኬትን መንገድ የከፈተላቸው እንደ አሎሎ ብረት ያበረታቸው፤ በቀላሉ የማይረቱ ሰውናቸው ያላሰለሰ ጥረታቸው ታክሎበት ነው።ሰዎች ስለ እርሳቸው ሲናገሩ፤ በተቻለ አቅም የሚለግሱ፤ ተስፋ የማይቆርጡ፣ አገራቸውን የሚወዱና አስተዋይ ይሏቸዋል።
የዛሬ እንግዳችን ካፒቴን ነስሩ ከማል ቀጠሯችንን ቦሌ ብራዚል ኤምባሲ አጠገብ ከሚገኝ ቢሯቸው አድርገን፤ ከብዙ ሕይወታቸውና ማንነታቸው ‹‹ዓባይን በጭልፋ›› ይሉት አይነት አጫውተውናል።
ውልደትና ዕድገት
ካፒቴን ነስሩ ከማል የተወለዱት በቀድሞ አጠራር ሸዋ ክፍለ አገር በአሁኑ ስያሜው ጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ ሎማ በምትባል መንደር ነው።ገና የአራት ዓመት ሕፃን ሳሉ ወደ አዲስ አበባ መጡ። ‹‹ሀ፤ ሁ›› ብለው ከፊደል ጋር የተዋወቁት በቄስ ትምህርት ነው።ከዚያ ከ1ኛ እስከ 6ተኛ ክፍል ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት፤ አርበኞች ትምህርት ቤት ደግሞ ከ7ተኛ እስከ 9ነኛ ክፍል ድረስ የተማሩ ሲሆን፤ ከ9ነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ደግሞ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተምረዋል ።1973 ዓ.ም በተፈሪ መኮንን 12ተኛ ክፍል ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለሞያዎችን ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቶ ስለነበር መስፈርቱን በሙሉ አሟልተው በመገኘታቸው ከሥመ ገናናው ተቋም ተቀላቀሉ።በወቅቱም መስፈርቱን ያሟሉ 80 የሚሆኑ ባለሙያዎች ተቀጥረው ነበር።በዚህ ተቋምም የሚጠበቅባቸውን ሲከውኑ ቆዩ፡፡
ከአየር ኃይል ወደ አየር መንገድ
ወደ አየር መንገድ በወቅቱ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ስለነበረችም ብዙ ፓይለቶች ይፈለጉ ነበር።ሆኖም በዚያን ጊዜ አየር ኃይል በቂ አውሮፕላኖች ስላልነበሩት ምልምል አባላት የነበሩትን ባለሙያዎች ሦስት ቦታ እንዲከፋፈሉ ተወሰነ።ከዚህም ውስጥ 21 የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲቀላቀሉ ከእነዚህ ውስጥ ካፒቴን ነስሩ ከማልም አንዱ ነበሩ።ዓላማው የነበረውም በአየር መንገድ ቆይታቸው ፈቃድ ያላቸው (ላይሰንስድ) እንዲሆኑ ማስቻል ነበር።በዚህም የንግድ አውሮፕላን ሙሉ በረራ ለማድረግ የሚያበቃ ስልጠና ወሰዱ።21 ሆነው ወደ አየር መንገድ ቢላኩም በወቅቱ ዘጠኝ ብቻ ነበር የቀሩት ፡፡
ከዚህ ስልጠና በኋላ ካፒቴን ነስሩ ከማል ተመልሰው ወደ አየር ኃይል በመቀላቀል ሌላ አውሮፕላን ላይ ተመድበው ጥቂት እንደሰሩ፤ አንቶኖቭ የሚባል አውሮፕላን እንዲያበሩ ተመድበው ሦስት ዓመት ከሰሩ በኋላ ሂልኮፍተር ላይ ተመደቡ፡፡
በወቅቱ ኢትዮጵያ የራሺያ ሂልኮፕተሮችን ከውጭ አግኝታ ነበር።ቀደም ሲል የነበሩት የአሜሪካኖቹ ሂልኮፕተሮች ነበሩ።በወቅቱ ልምድ ያላቸው አብራሪዎች ወደ ራሺያ ተልከው ልምድ ቀስመው ሲመጡ ካፒቴን ነስሩ ረዳት አብራሪም ሆነው በሂደት ደግሞ ካፒቴን ሆኑ።በዚሁም አስተማሪም ሆነው ነበር፡፡
መንግስቱ ኃይለማርያምን ሳጓጉዝ…
“በአየር ኃይል በምሰራበት ወቅት በርካታ የተከበሩ ‹‹VIP›› ሰዎችን በአውሮፕላ አጓጉዣለሁ፤ የኢትዮጵያን ፕሬዚዳንት ኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን ብዙ ጊዜ አጓጉዣለሁ በርካታ የጦር መኮንኖችን፣ ጀነራሎችን፣ ቱሪስቶችን ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ አጓጉዣለሁ።አንድ አሜሪካዊ በየዓመቱ ቱሪስቶችን ከተለያዩ የአሜሪካ ስቴቶች ይዞ ይመጣ ነበር።እነዚህንም ወደተለያዩ ኢትዮጵያ ክፍሎች አጓጉዘዋል፤ ከሰዎችም ተዋውቄያለሁ፤ አገርም አይቻለሁ።በወቅቱ የአየር ኃይል ይህን በረራ ያከናውን የነበረው ለመተባበር እንጂ ዋና ሥራው አድርጎ አልነበረም” ይላሉ-ካፒቴን ነስሩ፡፡
ኢህአዴግ ሲገባ…
የደርግ ሥርዓት በኢህአዴግ ሥርዓት ሲተካ ካፒቴን ነስሩ በማዕረጋቸው ሻምበል ነበሩ።በወቅቱ በርካታ የጦር መኮንኖችንና ባለሞያዎችን ጭምር እያደኑ ያስሯቸው ነበር።ዳሩ ግን በአጋጣሚ ሆኖ ካፒቴን ነስሩ አልታሰሩም።እንዲያውም ሁለት ዓመት ሥራ ላይ ነበሩ።ምናልባትም አሁን ላይ ሆነው ሲያስቡት የሚያስመጣላቸው ሃሳብ ነው፤ ብዙው ጊዜ በትራንስፖርት አውሮፕላን አብራሪነት ስሳተፍ ስለነበርና ጦር ሜዳ ላይ ብዙም ባለመሳተፌ ኢህአዴጎች ለማሰር የፈለጉ አይመስለኝም የሚል ግምት አላቸው።ሆኖም ብዙ ጊዜ ወደ ጦር ሜዳ በማቅናት ቁስለኛ ማንሳት፣ የጦር አመራሮችን ማድረስና መመለስ፣ ስንቅ ማድረስ የሥራቸው አካል ነበር።በተጨማሪም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለባንኮች፣ ለማዕድን ሚኒስቴርና ልዩ ልዩ የሲቪል ሥራዎች፣ ለእርዳታ ሥራ፣ ዜጎችን ከጎርፍ እና መሰል አደጋዎች ዜጎችን ለመታደግ፣ ቱሪስቶችን ለማጓጓዝና ለሌሎች ተግባራትም ይበሩ ነበር፡፡
ከአየር ኃይል ስንብት
ኢህአዴግ እንደገባ በጣም ከሚፈልጋቸው በስተቀር የአየር ኃይል ባለሙያዎችና መኮንኖችን አላሰረም ነበር።የተወሰኑትን እያፈላለገ ወደ ሥራ እየመለሰ አየር ኃይሉን በሚፈልገው መንገድ ማደራጀት ጀመር።ካፒቴን ነስሩም ሁለት ዓመት ሰርተው ነበር።በወቅቱ በነበሩ በረራዎች የኢህአዴግ አንድ ወታደር በተለይም በመጀመሪያው አንድ ዓመት ውስጥ በእያንዳንዱ በረራ ታጥቆ አብሮ ይንቀሳቀስ ነበር፤ ጥርጣሬ ስለነበረባቸው።
ካፒቴን ነስሩም ከሁለት ዓመት በኋላ የተለያዩ ጫናዎችን ስለተፈጠረባቸው ከአየር ኃይል ለቀው ወጡ።ከዚህን በኋላ መዳረሻቸው የሆነው አድማስ የሚባልና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥር የነበረ የንግድ የበረራ ድርጅት ነበር። ቀደም ብለው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ሰልጥነው ስለነበር ብዙም አልተቸገሩም።የበረራ ፈቃዳቸውንም አሳድሰው ሥራ ጀመሩ።ይሁንና ከዕለታት በአንዱ ቀን ይህ ሥራ አቁም የሚል ደብዳቤ ደረሳቸው።ይህም የሆነው ከአየር ኃይል ውስጥ ጫና የፈጠሩ ሰዎች በእጅ አዙር በመምጣት ነበር።በዚህ ጊዜ ካፒቴን ነስሩ ከማል ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት እንደማይችሉ በመረዳታቸው ሌሎች አማራጮችን ለመመልከት ተገደዱ፡፡
ስደት
የፖለቲካ እና ሌሎች ተያያዥ ጫናዎችን መቋቋም ያቃታቸውና ከሥራ የተሰናበቱት ካፒቴን ነስሩ ከማል ወደ ኬንያ በጉብኝት መልክ አመሩ።በወቅቱ ቤተሰብ መስርተው ስለነበር ጫናው ቀላል አልነበረም።በእርግጥ ቀደም ብለው ኬኒያን ለመጎብኘት ሄደው ስለነበር እዚያ ያሉትን አማራጮች ለማየት ዕድሉን አግኝተዋል።በወቅቱ ኬኒያ ብዙ የግል የበረራ ካምፓኒዎችም ነበሩ።ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አየር መንገድ እና አየር ኃይል ብቻ ስለነበሩና በሁለቱም እንዳይሰሩ ስለተከለከሉ ነበር ወደ ኬኒያ ያመሩት።በወቅቱም የበረራ ፈቃዳቸውን በኢትዮጵያ ስለነበር መስተካከል ያለበት ጉዳይ ተስተካክሎ ፈቃዳቸውን ያዙ፡፡
ወደ ታንዛኒያ
ኬኒያ ሁለት ወራት ከቆዩ በኋላ የተሻለ ዕድል ይኖራል ብለው ወደገመቱት ታንዛኒያ ‹‹አሩሻ›› የምትባል ከተማ አቀኑ።ኬኒያ ለጉብኝት በሄዱበት ወቅት ኤፍሬም ቡልቻ የሚባሉ ኢትዮጵያዊና የሬስቶራንት ባለቤት ጋር ድንገት ተዋውቀው ነበር።ካፒቴኑም ታሪካቸውን ለኤፍሬም አጫውተው ስለነበር እዚያው የሥራ አማራጮች እንዳሉም ጠቆሟቸው።በዚህን ጊዜ የካፒቴን ነስሩ ከማል ጓደኞች የጉብኝት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደየመጡበት ሲመለሱ እርሳቸው በዚያው የእንጀራቸውን መንገድ ማፈላለግ ጀመሩ።በዚህ አጋጣሚ አቶ ኤፍሬም የተባሉ ግለሰብ ለእኔ የማይረሳ ባለውታ ናቸው፤ ሁሌም ሳመሰግናቸው እኖራለሁ ይላሉ፣ ካፒቴን ነስሩ ከማል በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የኋሊት በትዝታ በማስታወስ።በዚህ የሥራ ማፈላለግ ውስጥ አንድ ድርጅት ፈቃደኛ ሆኖ ታንዛኒያ አሩሻ የምትባል ከተማ በሞያቸው ሥራ ቀጠራቸው፡፡
በታንዛኒያ ሥራ አግኝተው ለመሥራት ሂደቱን እንደጀመሩ በታሰበው ልክ ባለመሄዱና ባለቤቱ በሞት በመለየቱ ድርጅቱ ፈረሰ።አሁንም ሥራ ፍለጋው ቀጠለ።ከኢትዮጵያ ከወጡ ከሥምንት ወራት በኋላ በዚያው በታንዛኒያ ‹‹ሙዋንዛ›› በምትባል ከተማ ሥራ አገኙ።በወቅቱ ከውጭ ዘመዶቻቸው ያግዟቸው የነበረ ቢሆንም ጫናው ግን የዋዛ አልነበረም።የገጠሟቸውን ውጣ ውረዶች ሁሉ አልፈው የመጀመሪያ ሥራቸውን ጀምረው ደመወዝ ወሰዱ፤ ወዲያውም ቤተሰቦቻቸውን ከአዲስ አበባ ወደ ታንዛኒያ አመጡ።በወቅቱ ደመወዙም ቤተሰብ ለማስተዳደር በቂ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ሲጀምሩም ሆነ ወደ ሥደት ሲያመሩ ደመወዙ ብዙም ማራኪ እንዳልነበረም ያስታውሳሉ፡፡
አሁን ግን ኑሮን ለመምራት መንገዱ ቀና እየሆነላቸው መጣ። በሥራቸውም ላይ ሆነው ብዙ ዓይነት አውሮፕላኖችን መብረር ጀመሩ።ለረጅም ዓመትም ድርጅቱን ሳይቀይሩ ሠሩ፤ ልምድ ቀሰሙ፤ ሥም አፈሩ። ይሰሩበት የነበረው ድርጅት ትንንሽ የጉብኝት አውሮፕላኖች ነበሩት። በአንድ ቀን ሦስት የተለያዩ አውሮፕላኖችን የሚበሩበት አጋጣሚዎች ስለነበር በዕድሜም ገና በሠላሳዎቹ መጀመሪያ ስለነበሩ በትጋትና ያለመታከት ይሠሩ ነበር።
አራት ዓመት ከሰሩ በኋላ፤ በታንዛኒያ በሚገኝና የምስራቅ አፍሪካ አገራት አባል የሆኑበት የበረሃ አንበጣ መከላከያ ትራንስፖርት ሴክተር ላይ ገቡ።ይህ ድርጅት ለትራንስፖርት የሚሆን አንድ አውሮፕላን ገዝቶ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይበር ነበር።ካፒቴን ነስሩ ከማል በዚህ አውሮፕላን ላይም ሰርተዋል፡፡
አውሮፕላን የመግዛት ፍላጎት
ካፒቴን ነስሩ ከማል በሂደት ገንዘብ እየሰሩ በፈረንጆቹ አቆጣጣር 2008 አነስተኛ አውሮፕላን ገዙ።በእርግጥ ይህ ህልማቸው ገና ልጅ ሆነው ስደትን ሳያስቡት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ ነበር።ለዚህም እንደመነሻ የሆናቸው ሙሳ የሚባል ጅቡቲ ውስጥ የግል አውሮፕላን ሥራ የጀመረ ሰው ነበር።ሌላኛው ካፒቴን አስራት የሚባሉና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ እየሰሩ በግል አውሮፕላን ገዝተው ስራ ጀምረው ስለነበር እነዚህ ግለሰቦች ለካፒቴን ነስሩ ሥራ እንደ ዓይን ገላጭ አድርገው ሳሏቸው፡፡
አውሮፕላን ካምፓኒ ለመክፈት ምን ማድረግ አለብኝ፤ መስፈርቶቹስ ምንድን ናቸው? ሲሉ በወቅቱ የነበሩትን የኢትዮጵያ ጀነራል ዋና ኦዲተር አቶ ለማ አርጋው ጠየቁ።ከእርሳቸውም ጥሩ መረጃን አገኙ።ወደ አቬሽን መስሪያ ቤትም ሄደው
መረጃ ሰበሰቡ።ዳሩ ግን ገንዘብ ስላልነበራቸውና ሐሳባቸውን የሚጋራ ባለሃብት በመጥፋቱ በወቅቱ ሥራውን አልጀመሩም፡፡
ይህ ሁሉ ሳይሆን ቀርቶ በስደት ዓለም ለመኖር ተገደዱ።ታዲያ በስደት ታንዛኒያ እያሉም አንድ በደንብ ይተዋወቁት የነበረ ህንዳዊ ካፒቴን ለምን አውሮፐላን አንገዛም? ብሎ ያማክራቸዋል።እርሳቸው በወቅቱ ለአውሮፕላን መግዣ ገንዘብ ስለሌላቸው “በጭራሽ አልችልም ገንዘብ የለኝም” ይሉታል።በዚህን ጊዜ እኔ አለሁ ለገንዘቡ ብሎ አግባባቸው።ታዲያ በመጨረሻ ተግባብተው አራት ሰው የምትይዝ አውሮፕላን ገዙ፤ 35 በመቶ ድርሻም የካፒቴን ነስሩ ሆነ።ይህ ሁሉ ሲሆን ለአለቃቸው አልተናገሩም ነበር፡፡
ዳሩ ግን በታንዛኒያ ህግ መሰረት የአውሮፕላን ኦፕሬተር ፈቃድ ሲወጣ በግልጽ መታወቅ ስላለበት፤ ጉዳዩ የአውሮፕላን ኦፕሬተር ፈቃድ ቦርድ ላይ ቀረበ።በዚህን ጊዜ አለቃቸው የነበረ ሰው ከስብሰባው መልስ ወደ ካፒቴን ነስሩ ከማል በመሄድ እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? ብሎ አፈጠጠባቸው።በዚህን ጊዜ ሁለት አማራጭ ሰጣቸው።አንደኛው ጠቅልለህ የአውሮፕላን ኦፕሬተር ፈቃድ አውጥተህ ትሰራለህ፤ ወይስ ከእኔ ድርጅት ጋር ትቀጥላለህ ሲል ጠየቃቸው።ታዲያ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ስለነበሩና የሚቋቋመው ድርጅት አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ ባለመሆኑ ካፒቴን ነስሩ ከማል የአውሮፕላን ኦፕሬተር ፈቃድ ትቻለሁ ብለው የቀድሞ ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ገና በታንዛኒያ አንድ ብለው ሥራ የጀመሩበት ድርጅት አውሮፕላን እንደሚሸጥ ሰሙ። ሰዎችን አማከሩ በርታ አሏቸው፤ ጨረታውን ቢሞክሩትም አልተሳካም።ግን አሁንም ልባቸው አውሮፕላን መግዛት ላይ ነው።ሌላ ጨረታ ሞከሩና አሸነፉ።ዳሩ ግን አብረን እንሰራለን በርታ ሲሉ የነበሩ ካፒቴኖች ሸርተት አሉ።ካፒቴን ነስሩ ደግሞ ብዙ ስለተጓዙና ገንዘብም በብዙ ስላወጡ ወደ ኋላ መመለስ የማይችሉበት ደረጃ ደረሱ።113ሺ ዶላር አውጥተው ከአብራሪው ጋር ስድስት ሰዎችን የምትይዝ አውሮፕላን የራሳቸው አደረጓት።
እርሳቸው እዚያው የበረሃ አንበጣ መከላከል ውስጥ እየሰሩ፤ አንድ ሲውድናዊ አብራሪ ቀጥረው መሥራት ጀመሩ።በሂደት ግን የበረሃ አንበጣ መከላከል ውስጥ ያሉ ሰዎችም ልክ እንደ ቀድሞ ድርጅት ወይ እኛን ወይንም የግል ስራህን ምረጥ የሚል ሐሳብ ቀረበላቸው።የጥቅም ግጭት አለው የሚልም አንዱ ምክንያት ነበር። ካፒቴን ነስሩ ከማል የሚሰሩትና የተባለው አይጋጭም ነበር።ዋናው ነገር ለምን አደገ የሚል የቅናት መንፈስ ነበር።በዚህን ጊዜ ካፒቴን ነስሩ ወሰኑ፤ የራሴ ሥራ ይሻለኛል ብለው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2009 ወደ ራሳቸው ሥራ ጠቅልለው ገቡ ።
ወደ ሱዳን
ታንዛኒያ እየሰሩ ሳለ ደቡብ ሱዳን ጥሩ የገበያ ዕድል መኖሩን በሰሙ ጊዜ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2014 14 ሰው የሚይዝ ከራቫን የሚባል አውሮፕላን በሊዝ ግዥ በ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገዝተው ደቡብ ሱዳን ገቡ።በአሁኑ ወቅትም ድርጅታቸው በዚያው እየሰራ ነው፡፡
ታዲያ አሁን ላይ የደረሱበትን ሁኔታ የኋሊት ሲመለከቱ፤ “እውነቱን ለመናገር የሚያስደስተኝ ያፈራሁት ንብረት ሳይሆን ተገፍቼ ወጥቼ ጎዳና ላይ ይወድቃል ጫማው አልቆ፣ ሸሚዙ ተጨማዶ፣ ውስጡ ነዶ መንገድ ላይ እናገኘዋለን ብለው ሲያስቡኝ በሃሳባቸው ተስፋ ይቆርጣል ብለው ሲመኙ በፈጣሪ እርዳታ እዚህ መድረሴ ነው።በወቅቱ በጣም ተከፍቼ ነበር።ከዚያ ወጥቼ እዚህ መድረሴ ትልቅ ነው።ኔልሰን ማንዴላ ያሉት አባባል አለ።‹የሚያስደስተኝ ያገኘሁት ስኬት ሳይሆን ስንቴ ወድቄ ስንቴ እንደተነሳሁ ነው› “ይላሉ፡፡
የበረሃ አንበጣ መከላከል ላይ እየሰራሁ ሳለም ብዙ በድለውኛል የሚሉት ካፒቴን ነስሩ ግን ሁሉም ነገር ለበጎ ነውና አልፌዋለሁ ባይ ናቸው፡፡
“አሁን በወቅቱ እነሱ ቀጥረውኝ ሳበራቸው የነበሩት ዓይነት ሦስት አውሮፕላኖች አሉኝ።ሁለቱ እየሰሩ ነው።በቀጣይ ሁለት ተጨማሪ የመግዛት እቅድ አለኝ።በደቡብ ሱዳን ውስጥም በፋይናንስ ስም በደንበኛም ጥሩ እየሄድኩ ነው” ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውለታ
“እውነቱን ለመናገር አየር መንገዳችን በጣም የምንኮራበት ነው።ለእኔም እዚህ መድረስ ተጠቃሽ ባለ ውለታ ነውⵆ አየር መንገድ ያገኘነው ዲፕሎማ በጣም ዋጋ ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ነው የሰለጠንኩት ብዬ ስናገር ኦ! በጣም አሪፍ ነው ብለው ያደንቁታል።አየር መንገዳችን ጥሩ ሥም ስላለው እዚያ መሰልጠኔ ለእኔ ረድቶኛል።በዚህ አጋጣሚ አየር መንገዱን አመሰግናለሁ፤ በጣምም እኮራበታለሁ “ይላሉ፣
ኢትዮጵያ በአቬሽን ጎልታ የወጣችበትና ቀዳሚ ከሚባሉ አየር መንገዶችም አንዱ የሆነችበት አፍሪካኖቹ በቀኝ ግዛት ውስጥ ሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ ላይ የነበረና በጣም ዝነኛ ነበር።ያኔ! እኔም በአየር መንገዱ ውስጥ ስሰለጥን አውሮፕላን ለማስጠገን ከብዙ አገር ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ ነበር።ከደቡብ አፍሪካ ካለው የአፓርታይድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ከተጣለው ክልከላ ውጭ በርካቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።ለምሳሌ የግብጽ፣ የመን ሌሎችም የአፍሪካ አገራት አውሮፕላኖች ለጥገና ኢትዮጵያ ይመጡ ነበር ።ፓይለቶችም ለስልጠና ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ መጥተዋል በማለት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።
አገራችን ያለው ዕድል
ታንዛኒያ ውስጥ ብንሄድ ለሌላ አገር ዜጋ ምቹ አይደለም።ከኢትዮጵያ ፓይለት ጨምሮ ብዙ ባለሙያ መውሰድ እፈልግ ነበር፤ ግን ህጋቸው በጣም ጥብቅ ነው።እኔ አሁን እዚያ ቢሮ አለኝ።ወደ ደቡብ ሱዳን የሄድኩትም የስራ አማራጭ ፍለጋ ነው።
እኛ አገር ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ ካመቻቸን ትልቅ ገቢ ይኖረናል ።አየር መንገዳችን አዳዲስ አሰራር ቢዘረጋ መልካም ነው።ለምሳሌ ወደ ባሌ በረራ በቀን አንድ ጊዜ ከሆነ ከዚህ ሰዓት ውጭ የሚመጣ ቱሪስት ማስተናገድ አይቻልም ስለዚህ ትንንሽ ካምፓኒዎች ዕድሉ ቢሰጣቸው በተፈለገው ሰዓትና ቦታ ሌላው ቀርቶ መንደር ውስጥ ገብተን እንሠራለን፡፡
የማዕድን አካባቢ ሥራዎች አንድ ማሽን ቢበላሽ ወይንም ተለዋጭ ዕቃ ቢፈልጉ ትልልቅ አውሮፕላኖች በዚያ ስፍራ አያርፉም። ለአርኮሎጂስቶች፣ ኢን ቨስተሮች፣ ለውጭ ጉዞ አስቸኳይ ህክምና፣ ጎብኚዎች ለማንቀሳቀስና ለመሳሰሉት አመቺ ሁኔታ መዘርጋት ያስፈልጋል። ትልልቅ ፕሮጀክቶችን መጎብኘት ቢያስፈልግ መሰል በረራዎች አስፈላጊ ናቸው። ስለዚህ ትንንሽ አውሮፕላኖችን ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል። ይህ ቢሰራበት ለአገሪቱ ትልቅ ጥቅም ያመጣል። ታንዛኒያ እያለሁ ለቱሪዝም፣ ለማዕድን ሥራዎች፣ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ስበር ነበር።በጣም አዋጭና አገርን የሚጠቅም በመሆኑ በእኛ አገርም ቢጀመር ለኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ አገሪቱ ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
እኔም ለአገሬ
ከአገሬ ተገፍቼ ወደ አገሬ የተመለስኩት ‹‹ዞሮ ዞሮ ከቤት፤ ኖሮ ኖሮ ከሞት›› አይቀርምና እትብቴ ወደተቀበረባት ኢትዮጵያ ተመልሻለሁ።በመሆኑም በአገር ውስጥ ለመሥራት ‹‹ኤር ኤክስፕረስ አፍሪካ›› (Air Express Africa›) በሚል ድርጅት ፈቃድ አውጥቼ በሙያዬ ተሰማርቻለሁ።ህጋዊ ሂደቶችንና መስፈርቶችን አልፌ ፈቃድ አውጥቼ ሰዎችንም እየቀጠርኩ ነው።
“እንደ ድርጅት ብዙ መሥራት አለብን ብለን ነው የተነሳነው። ቱሪዝም ላይ መሥራት ያስፈልጋል።የጸረ ተባይ መድሃኒት በአውሮፕላን ለመርጨት እናስባለን፤ ግን አርሶ አደሩን ማላመድ ያለብን ነገር ደግሞ አለ። ትልልቅ ባለሃብቶች፣ በጣም የተከበሩ ሰዎችንና ሥራ ኃላፊዎችን ለማጓጓዝ የምንሠራ መሆናችንን ማሳወቅ እንፈልጋለን። በዘርፉ ላይም የአብራሪ (ፓይለት) ማሰልጠኛ ላይ እንሰራለን።አፋጣኝ የውጭና በአገር ውስጥ መታከም የሚፈልጉ አገልግሎት መስጠት፣ የአውሮፕላን ካርጎ አገልግሎት፣ ወደ ውጭ ምርት ለሚልኩ ነጋዴዎች አገልግሎት እንሰጣለን። በአጠቃላይ የግብርና፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ሕክምና ዘርፍ ለመደገፍ ነው የምንቀሳቀሰው። በይበልጥ ደግሞ ማዕድንና ቱሪዝም ላይ በመሰማራት የአገሪቱን ልማት የማገዝ ፍላጎትና ምኞት አለን” ይላሉ፡፡
በዚህ ሁሉ ስራ ውስጥ መግባታችን ግን የኢትዮጵያን አየር መንገድ ጥቅም በሚፃረር መልኩ ሳይሆን ሥራዎችን በመደገፍ ነውም ይላሉ፡፡
ቤተሰብ፣ ትምህርትና፣ እውቅና
ካፒቴን ነስሩ ከማል አራት ልጆችን አፍርተዋል።ልጆቹ እንደ አባታቸው ታታሪና ሥራ ወዳድ ናቸው። በሥራ ይተጋገዛሉ፤ በትምህርታ ቸውም ስኬታማ የሚባሉ ናቸው።እርሳቸው ያለፉበትን ውጣ ውረድ እንደ ምሳሌ እያነሱ ያስተ ምሯቸዋል፤ ለቤተሰቦቻቸው የጥንካሬ መሠረት እንዲሆናቸው፤ በፈተና ውስጥ ማለፍና ለስኬት መብቃት እንደሚቻል የእርሳቸው ህይወት ምሳሌ እንዲሆናቸው፤ በአጋጣሚዎች ሁሉ ያወጓቸዋል። ለስኬታቸውም የቤተሰባቸው ድጋፍ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድም ይናገራሉ፡፡
በእርግጥ ህይወት ወደ ብዙ መንገድ ብትወ ስዳቸውም እርሳቸውም በትምህርታቸው የዋዛ ሰው አይደሉም። ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በዲፕሎማ፣ ከአሜሪካ አገር በበረራ ደህንነት ሰርተፍኬት፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ድግሪያ ቸውን ከታንዛኒያ አግኝተዋል።መስፈርቶች በሙሉ አሟልተው በመገኘታቸው ከኢትዮጵያ፣ ኬኒያ እና ታንዛኒያ የንግድ አውሮፕላን ፈቃድ አግኝተዋል። በአገር ውስጥ ደግሞ በጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ ለማህበረሰቡ በጎ የሰሩ፣ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈው ወደ ስኬት የመጡ ሰው በመሆናቸው በየዓመቱ በሚሰጠው ‹‹ኬር አዋርድ›› ላይ ምስጋና እውቅና ተችረዋል፡፡
መልዕክት አለኝ
በኢትዮጵያ ውስጥ የግል ቻርተር አውሮፕላኖች አለመስፋፋት ጎድቶናል።በቅርቡ ፈቃድ ስወስድ እኔ 12ኛ ሰው ነኝ።ወደ ሌላ አገር ስንሄድ የምንመለከተው የአገራችንን ቱሪዝም አለመጠቀማችንን እንረዳለን፡፡
ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አጋጣሚውን አግኝቼ መናገር የምፈልገው፤ በጣም! በጣም! መሥራት ይጠበቅብናል የሚለውን ነው። ኬኒያና ታንዛኒያ ትልቁ ገቢያቸው ቱሪዝም ነው። ቱሪዝም ትልቅ አቅም አለው። በመሠረተ ልማትም ብዙ ይቀረናል። ሆቴሎች፣ ቴክኖሎጂ፣ ኤርፖርቶች በበቂ ሁኔታ አለመገንባታቸው፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ጎድቶናል፡፡
አውሮፕላኖች በብዛት ማረፊያቸው አዲስ አበባ ነው። ትንንሽ ኦፕሬተሮች በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት በሚገባ እየሰሩ አይደለም ብየ አስባለሁ። ስለዚህ እነዚህ ትንንሽ አቅም ያላቸው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በሌላ ቦታ ቢስተናገዱ ለአገርም ለባለሃብቱም ይጠቅማል። የደህንነት ሁኔታውንም ለማስጠበቅ መንግስት አሰራርና ፖሊሲዎችን መቅረጽ ይችላል። ኬኒያ ውስጥ ይህ ተሞክሮ አለ።በመሆኑም ለአነስተኛ አውሮፕላኖች ራሱን የቻለ ኤርፖርት ያስፈልጋል። በአውሮፕላኖች የሚጠገኑበትንም ‹‹ሃንጋር›› ያስፈ ልገናል። በአሁኑ ወቅት ትንንሽ ብልሽቶች ሲገጥሙን ከአገር ውጭ እየሄድን ነው ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የምናሰራው።
መንግስት በአሁኑ ወቅት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድና አየር ኃይል ቅጥር ግቢ የሚገኘውን ደጀን አቬሽን ለግል አውሮፕላን ኩባንያዎች የጥገና አገልግሎት እንዲሰጡ በመፍቀዱ ወደፊት ይህ ችግር ይቃለላል የሚል ተስፋ አለኝ። በዚህም መንገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊያግዘን እየሞከረ ቢሆንም በብዙ ሥራ ስለሚጠመድና በተለያዩ ምክንያቶች ያን ያህል አጥጋቢ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም። በእኔ እይታ ደጀን አቬሽን ከሚመለከተውና ከሲቪል አቬሽን ለግል አውሮፕላን ጥገና የሚያበቁዋቸውን ፈቃድ ካገኙ አመርቂ ሥራ ይሰራል የሚል ዕምነት አለኝ።
‹‹በድርጅቴ ኤር አፍሪካ ኤክስፕረስ ውስጥ ያሉ አምስት የቴክኒክ ባለሙያዎች ወደ ደጀን አቬሽን ሄደው ያመጡልኝ ሪፖርት የሚያሳየው በጣም ተስፋ የሚጣልበት ተቋም በመሆኑ ከእነርሱ ጋር ለመሥራት እያቀድን ነው።ሌሎች ኩባንያዎችም ዕድሉን ቢጠቀሙ እመክራሉ›› ሲሉ በኢትዮጵያ ያለውን መፃዒ ተስፋ ይጠቁማሉ፡፡
ሌላው ችግር በአገሪቱ ውስጥ በቂ የአየር ማረፊያ አለመኖሩ ሲሆን ይህንን በመገንዘብ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን የግል አውሮፕላን ባለቤት ሆነ ማንኛውም ባለሃብት አየር ማረፊያ የመገንባት ፍላጎትና አቅሙ ካለው ፈቃድ ለመስጠት ፈቃደኝነቱን በማሳየቱ በጫካውና በቱሪስቶች መዳረሻ ሎጅ መሥራት አለብን።ቱሪስቶች አካባቢዎችን ቀን፣ ማታ፣ ሌሊት፣ ማለዳ እየተነሱ አካባቢውን መቃኘት ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ጥዋት ብቻ የሚታዩ ወፎች ሊኖሩ ይችላሉ። በአገራችን ህጋዊ አደን የሚፈቀድ ከሆነም ይህን ሥራ መሥራት ይገባል፡፡
ታንዛኒያና ኬኒያን የመሳሰሉት አገራት ብንሄድ ብዙ ነገሮች ከእኛ የተሻሉና የተደራጀ ዘመናዊ አሰራር ዘርግተዋል።በአገራችን የሰሜኑ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የአገሪቱ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ከቤተሰቤ ጋር ተጉዘን ነበር።አሁን ጥሩ ነገሮች አሉ፤ ቢሆንም ግን ብዙ ሥራ መሥራት ይገባል ።ጎብኚዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲመጡ ሠላምና መረጋጋት መፈጠር አለበት። መሰረተ ልማቶችንም በተቻለ መጠን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም