የብዙ ሀገራት መንግሥታት የሥልጣን ወንበራቸውን አላጋሯቸውም፤ ነገር ግን አራተኛ የመንግሥታቸው ተጋሪ እንደሆኑ በአፍ ብቻ ሲሸነግሏቸው ዘመን አሸብተዋል:: የየሀገራቸውን መንግሥታት እንደ ምሰሶ አጽንተው ካቆሙ ሦስቱ አእማድ እኩልም ተገቢው ክብርና ቦታ ስላልተሰጣቸው በመንግሥታቱ የሥልጣን መንበር ዙሪያ ቢፈለጉም አይገኙም:: እንዲያም ሆኖ ግን እስኪያሰለች ድረስ እንደ አራተኛ የመንግሥት አካል ቆጥረናችኋል እየተባሉ የአደባባይ ሙገሳ ይዥጎደጎድላቸዋል::
አንዳንድ የከፉ መንግሥታትም በአፍ የአራተኛ መንግሥትነት ስልጣን እንዳላቸው እየነገሯቸው እውነት መስሏቸው «ሉዓላዊ ሥልጣናቸውን» መተቸት ሲዳዳቸው «በለፈለፉ ባፍ ይጠፉ!» በማለት በሰንሰለት ካቴና እጃቸውን ከወንጀለኛ መቅጫ ሰነዳቸው ጋር አቆራኝተው ከርቸሌ ይወረውሯቸዋል:: «ኧረ የፍትህ ያለ!» እያሉ ቢማጠኑም «ይልቅስ የከፋ ሳይገጥማችሁ አርፋችሁ የዓለም በቃኝ ኑሯችሁን ግፉ» እያሉ በመሳለቅ «ቀድሞውንስ ውሻን ምን አገባው ከእርሻ»ን ተረት እየተረቱ ይሳለቁባቸዋል:: በሥልጣናቸው የተደላደሉት ሦስቱ «የምር የመንግሥታቱ ባለድርሻዎች::»
እነሆ ላመሳጠርኩት የመንደርደሪያ ዕንቆቅልሼ ሀገርህን አብነት አድርገህ መልሱን ስጠን ለሚለው አንባቢ «ሀገሬን ካላችሁማ ምን አጥቼ፤ ሁሉ በእጄ፣ ሁሉ በደጄ» እያልኩ በብዕረ መንገዴ ሃሳቤን ወደ ማጋራት አቀናለሁ:: ቀጥዬ የምጠቅሰውን አባባል የተናገረው በርካታ ሀገራትን በጦርነት ድል በማድረግ አንቀጥቅጦ እንዳስገበረ የሚተረክለት የፈረንሳዩ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ናፖሊዮን ቦናፓርቴ (1769-1821) ነበር ይባላል::
እርሱ ባይናገረውም አባባሉ መልካም ስለሆነ የኮፒ ራይቱ መብት ለጊዜው ለገናናው ንጉሥ ይሁንና አባባሉ እንዲህ የሚል ነው፤ «ከሦስት ባታሊዮን ጦር ይልቅ አንድ የብዕር ሰው እፈራለሁ» «ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ንገስ አቦ!» እንዴት ዓይነት ድንቅ አባባል ነው ጎበዝ::
ከሁለት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ይህንን ዘመን አይሽሬ አባባል የተናገረው «ለእኛ ነው» የሚሉ የሁለት ተፋላሚ ኃይላት ጠብና ንጥቂያ እስከዛሬ ያልሰከነ መሆኑ ቢገባኝም «የተናገረው ለእነ እከሌ ነው» ብዬ ምስክርነት ከመስጠት ይልቅ በመልዕክቱ ላይ ትኩረት ማድረጉን መርጫለሁ:: የሁለቱ ተፋላሚ ኃይላትን ማንነት ግለጥ ካላችሁኝ ግን ደራስያንና ጋዜጠኞች መሆናቸውን አሳውቄ ጉዞዬን እቀጥላለሁ::
«ሚዲያ የአንድ ሀገር አራተኛ የመንግሥት አካል ነው» የሚለው ተለምዷዊ አገላለጽ በሰለጠኑት ሀገራት ዘንድ በርግጥም «የአራተኝነት መንግሥታዊ በትረ ሥልጣኑን ጨብጦ ወንበር ባይጋራም» «ሦስት ባታሊዮን ጦርን በሚያስከነዳ ብርታቱ» አንቱ መባል ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል:: «ሚዲያ ብቻውን ምን ስለሆነ ነው መንግሥታዊ የሩብ ድርሻ ሊጋራ የቻለው?» አንድን መንግሥት መንግሥት ያሰኙት ቀዳሚው፣ ዳግማዊውና ሣልሳዊው ወንበረተኞችስ እነማን ናቸው?» ብሎ ለሚጠይቅ ዕውቀት ወዳድ አንባቢ ሦስቱ የመንግሥት ምሰሶዎችማ ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚ የሚባሉት ናቸው በማለት አጭር መልስ መስጠት ይቻላል:: ዝርዝር ትንታኔ የሚያሻው ከሆነም በሚቀጥሉት የጋዜጣው ዕትሞች በስፋት መተንተኑ አይገድም::
በአራተኛ የመንግሥት መሠረታዊ አካልነት ተጠቃለው የተቧደኑት የሚዲያ ዓይነቶች ራሳቸውም ቢሆን የሚከፈሉት በአራት ዋና መደቦች ነው:: እነርሱም፤ የህትመት ሚዲያ (ጋዜጣና መጽሔት)፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ዘመን አመጣሹ የማኅበራዊ ሚዲያ ጭፍሮች መሆናቸውን በጥቅል ብያኔ ማስታወስ ይቻላል:: ትንተናው ብዙ አድማሶችን ስለሚዳስስ ጥቅሉንና አብዛኛውን ሕዝብ በጋራ በሚያግባቡ ሃሳቦች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉ የተሻለ ስለመሰለኝ ለመንደርደሪያና ለመነሻ ያህል ይበቃ ይመስለኛል:: በዋነኛነት «አራተኛ የመንግሥት አካል» ተብለው የሚንቆለጳጰሱት እነዚህ የሚዲያ ዘርፎች ናቸው::
በዚህ ግዙፍ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም:: «ኪነ ጥበባትን ከመሰሉ ኃያል ዘርፎች ተለይቶ እንደምን ሚዲያ ብቻ አራተኛ የመንግሥት ሥልጣን ተጋሪ እንደሆነ ሊቆጠር ቻለ?» ጥያቄው እጅግ በርካታ ምላሾችን ያረገዘ መሆኑ ቢታመንም በአጭሩ ዋና ዋና ነጥቦችን ብቻ ነካክቶ ማለፉ ይበጃል:: ሚዲያ (በእኛ ቋንቋ መገናኛ ብዙኃን) ዋነኛ ትኩረቱ የሕዝብ ወቅታዊ ጉዳይ ነው:: ተልዕኮውም መንግሥትን መንግሥት ባሰኙ መዋቅሮች ላይ አነጣጥሮ መሄስ ነው:: ሲያለሙ አመስግኖ ሲያጠፉም ገስጾና አጋልጦ ለሕዝብ ማሳወቅ:: በባህሪውም መረጃ ሲሰጥ፣ ሲያዝናና ወይንም ሲያስተምር ዕለታዊና ሰሞናዊ ባህርይ ተላብሶ ነው:: የእኛ ሀገር ጋዜጠኞች «የዜና ቋንጣ የለውም» ማለታቸው ከዚሁ ባህሪይው የተነሳ ይመስላል::
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን ተናገሩ እንደሚባለው፤ አንድ ሚዲያ በቀዳሚነት «መንግሥት የሕዝብ፣ በሕዝብ፣ ለሕዝብ» ሆኖ መቆም ያለመቆሙን የሚፈትሸው ኤክስሬያዊ ባህርይ ተላብሶ መሆን አለበት:: ሚዲያ አራተኛ መንግሥታዊ ሥልጣን አለው እየተባለ መሸንገሉም በዚሁ የተለየ ባህሪይው ምክንያት እንጂ «ምልዑ በኩለሄ የሆነ አራተኛ የመንግሥት ሥልጣን» ኖሮት አይደለም::
«አሰስ ገሰሱን ኮሲ (ፍግ) በሕዝብ ላይ የሚጭኑ ሚዲያዎችስ በርግጡ የአራተኛ መንግሥትነት ሥልጣን ይገባቸዋልን?» ሌላው በአንባቢ ሊጠየቅ ይችል ይሆናል ብዬ የጠረጠርኩት ጥያቄ ነው:: አጭሩ የግሌ አስተያየት «ከንግሥና» ይልቅ በዘመን ነፋስ የሚከንፉ ናቸው የሚል ይሆናል::
አሁን ወደ ራሳችን ጉዳይ እንመለስና ላይ ላዩን ቢሆንም የሀገራችንን መገናኛ ብዙኃን ለመዳሰስ እንዳፈር:: ለመሆኑ ግብሩ እንኳ ቢቀር በጋራ፣ በይሁንታና በስምምነት ዓለም የአራተኛ መንግሥትነት መብት እንደሰጣቸው እንደ ሰለጠኑት ሀገራት የእኛን ሀገር ሚዲያዎች ስንፈትሽ ምን ይመስላሉ? ደረጃቸውስ ምን ላይ ነው?
ልብ ያለው ልብ እንዲል አንድ አባባል ደግሜ ልጥቀስ:: «መንግሥት ኖሮ ሚዲያ ከሚጠፋ፤ ሚዲያ ኖሮ መንግሥት ባይኖር እመርጣለሁ» እንዳሉት አንድ ልባም መሪ፤ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚዲያ ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ማለዳ ከቤት ስንወጣ ፊታችንንና አለባበሳችንን በመስታወት ፊት ቆመን እንደምናስፈትሸው ሁሉ አንድ መንግሥትም ራሱን የሚያይበትና ጉድፉን የሚያብስበት መስታወቱ ሚዲያ ነው::
ዓይነ ስውርነት ለሰው ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ሦስቱ አካላትም የዓይናቸው ብርሃን በአምባገነናዊ ባህርይ የሚጠፋባቸው ወቅቶች እንደነበሩና እንዳሉ ታሪካችንንም ሆነ ተሞክሯችንን ለምስክርነት መጥራት አይገድም:: የሀገራችን የሚዲያ ተቋማት ከነባሮቹ እስከ ዘመን አመጣሾቹ ድረስ ዕድሜያቸውን እናስላ ብንል እጅግም ለሽበት አልታደሉም:: ብዙዎቹ ዋግ እንደመታው አዝመራ የሚጠወልጉት ገና በውልደታቸው ማግሥት ነው:: እንኳን በአራተኛነት የመንግሥት ሥልጣን ሥር ሊፈረጁ ቀርቶ ስማቸውን እንደያዙ መኖራቸውም በራሱ ተዓምር የሚሰኝ ነው፤ «ፅድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ» እንዲሉ::
በግል ግልብ ዳሰሳዬ የንጉሡ ዘመን ውሱን የሀገራችን የሚዲያ ነፃነትና ብስለት በቅርጽም ሆነ በይዘት በእጅጉ ይሻላል ብዬ እከራከራለሁ:: የሚረታኝ ከመጣ «አፉ በሉኝ» ብዬ ንስሃ እገባለሁ:: በንጉሡ ዘመን አዲስ ዘመን ጋዜጣ «የጧትና የማታ» ዕትም እየተባለ በቀን ሁለቴ የታተመበት ወቅት ነበር:: ዛሬ ግን ይህቺ «የፕሬሱን ሪፎርም አመላካች የሆነችው» የቅዳሚት አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንኳ ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የህትመት ምጣድ ላይ በዕለቱና በሰዓቷ ተጋግራ መውጣት ተስኗት ያለፉት ሳምንታት ዕትሞች ሦስትና አራት ቀናት እየዘለሉ ታትመው ሲወጡ ስንመለከት «አጀብ!» እየተሰኘን ተገርመናል::
በንጉሡ ዘመን ከእንግሊዘኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች ታላላቅ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ይዘታቸውና ጥራታቸው ተጠብቆ ይታተሙ የነበሩ ተነባቢ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ለመፈተሽ ዕድሜውን ያላደለን አንባቢያን ቤተ መዘክሮች ገብተን አርካይቫቸውን ብንፈትሽ ፍርዱን በቀላሉ መስጠት እንችላለን::
ትናንትን ከዛሬ ጋር ለማወዳደር መሞከር አዳጋችም፣ አስተችም እንደሆነ ይገባኛል:: ነባሮቹንና ዕድሜ ጠገቦቹን የሚዲያ ዘርፎች ከዛሬው ዘመነ ሶሻል ሚዲያ ጋር እንደማይወዳደሩም እረዳለሁ:: የሰለጠንኩበት የኮሚዩኒኬሽን የዕውቀት ዘርፍም ለምሰጠው አስተያየቶች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብኝ ይመክረኛል:: የሆኖ ሆኖ ግን ነበርን ከዛሬ ጋር ማወዳደሩ በጭራሽ መሞከር የለበትም የሚለው አስተያየት እጅግም አይመቸኝም:: ለምን ቢሉ፤ ትናንት የቆመው በዛሬ መሠረት ላይ ሲሆን የነገ መሠረቱ ደግሞ ትናንትም ዛሬም ነው::
በግሌ የሀገሬ የሚዲያ ተቋማት እንኳንስ «የአራተኛ የመንግሥትነት ሥልጣን» ሊቀዳጁ ቀርቶ የራሳቸው ጉተናም የጠና አይመስለኝም:: ነገሩ «ራስ ሳይጠና ጉተና» እንዲሉ መሆኑ ነው:: ችግሩ የሚዲያው «ጉተና» ያለመጥናቱ ብቻ ሳይሆን የሚዲያ ባለሙያዎቻችንም ገና «በጋሜ» ዕድሜ ላይ መገኘታቸው ላይ ነው::
የእስራኤላዊያኑ መሪ ሙሴ ባህር የሚከፍል ተዓምራዊ በትር በእጁ ይዞ ቀይ ባህርን ለሁለት መክፈልና ሕዝቡን ማሻገር እየቻለ ግራ በተጋባ ስሜት «ወዮልን ብሎ እንደቆዘመ» ሁሉ፤ የእኛም በርካታ የሚዲያ «ኤክስፐርቶች» ዲግሪውም ሆነ ልምዱ ሳይጎላቸው ለምን ብዕራቸውን እንዳዶሎዶሙ ሳስብ ግራ ይገባኛል::
ዘመነ ሳንሱር ቢያከትምም ከጋዜጠኞቻችን አእምሮ ፍርሃቱ ገና የተፋቀ አይመስለኝም:: መቼም የዘመኑ ሶሻል ሚዲያ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የሀገሬን ሕዝበ አዳም እያሳበደና እያከነፈ መሆኑ ይገባኛል:: የዋናዎቹ የሚዲያ ተቋማት የመረጃ ምንጭም ይሄው ጣጠኛ ፌስ ቡክ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል:: በነባር ሚዲያዎችም ሳይቀር ያልተጣሩና ከነፋስ እየተዘገኑ የሚሠራጩት መረጃዎች ከግለሰብም አልፎ ለሀገር ነቀርሳ እየሆኑ ስለ መሆናቸው የአደ ባባይ ምሥጢር ነው::
ይህንን ቱማታ የሚመክት ጋዜጠኛ በሀገራችን ለማግኘት «ስዕለት» ከማድረስ አልፈን ፈጣሪን መሞገት ሊኖረብን ነው:: አንዳንድ ተስፋ የጣልንባቸው የየሚዲያው ታታሪዎችም ገና ስማቸውን እየጠራን ስለ መልካም ጥረታቸው ማመስገን ስንጀምር የሙያቸውን ሥነ ምግባር እየጣሱ ለቃለ መጠየቅ የጋበዟቸውን እንግዶች ሲያሽቆጠቁጡ እያደመጥንም እየተመለከተንም ነው::
እርሷ ብቻ የምትፈልገውን መልስ አልሰጥ ብለው ወዲያ ወዲህ ሲጠማዘዙባት ያስተዋለችው ጋዜጠኛ «እርሶ አስቸጋሪ ፍጡር ነዎት!» ብላ የሚሊዮኖች ዓይኖች ባፈጠጡበት ፕሮግራሟ ላይ ስታዋርዳቸው ተመልክተን ስለ እሷ ድፍረት እኛም ተሸማቀናል:: የጋዜጠኞቻችን የቋንቋ አጠቃቀም ጉዳይ ብዙ ያስብላል::
ስለ ምርመራ ጋዜጠኝነት ሲታሰብ የዘመነ ደርጉ የብሔራዊ ሬዲዮኑ «ከምናየውና ከምንሰማው» ፕሮግራም እና አዘጋጁ ንጉሴ ተፈራ (ዶ/ር) ሊዘነጉ አይችሉም:: ፕሮግራሙ ልክ ሲጀመር ትንሽ ትልቁ ሬዲዮ ፍለጋ እንደሚሮጥ ያልመሸበት ታሪካችን ትዝታ አልደበዘዘም:: ምነው ያ ዘመን ለዛሬ እውነታችን ትምህርት ሆኖ ባባነን እላለሁ::
ምንም ማጋነን ሳይታከልበት አብዛኞቹ የሀገራችን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መመሳሰል ብቻ ሳይሆን በአንድ ዕቅድ፣ በአንድ ክብ ጠረጴዛና በአንድ የፕሮግራም አዘጋጅ የሚሰናዱ እስከሚመስል ድረስ ከፕሮግራም እስከ ዜና፣ ከመዝናኛ እስከ ውይይት በእጅጉ የመንታ ያህል ተመሳስሏቸው ስለሚገዝፍ ግራ ወደማጋባቱ እያቃረቡን ነው::
አንዳንድ የግል መጽሔቶችና ጋዜጦችም በርዕስም ሆነ በይዘት እንደ ጅራፍ ስለሚጋረፉ መለብለቡ የሚጀምረው ገና ሽፋናቸውን ስንመለከት ነው:: በተለይም ጽንፍ ረገጥ የሆኑ ብዕሮች የሚጭሩት የእሳት ነበልባል «ትንሽ ምላጭ ሀገር ትላጭ» እንዲሉ የሚያደርሱት ጉዳት ከዛሬም ዘሎ ለነገው ትውልድ የቂም ዕባጭ እንዳይሆን በግሌ ስጋት ከገባኝ ሰንብቻለሁ:: ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን የሚዲያ ባለሙያዎችን ሰብስበው «የአራተኛ የመንግሥት ሥልጣኑን ክብር ተለማመዱ» ብለው የሰጧቸው ምክር በእውነትም ተግባራዊ ቢሆን «የመንግሥቱን መንበር» በአግባቡ ተጠቅመውበት ሕዝብ ያገለግሉ ይሆን ወይ ብዬ በግሌ እጠይቃለሁ::
አንድ የግል ገጠመኜን ላስታውስ:: የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ለስብሰባ በተገኘበት ሀገር ከዋናው መርሃ ግብር ጎን ለጎን የሀገሪቱን መሪ የጋዜጣ አታሚ ተቋም ለመጎብኘት ዕድል አጋጥሞት ነበር:: አስጎብኚው ባለሙያ የጋዜጣው ዋና ቢሮ የሚገኝበት ህንፃ በውበቱና በግዝፈቱ የዋና ከተማው ዋና መስእብ (Land Mark) መሆኑን በጣፈጠ ቋንቋ አስረዳን:: ስለ ጋዜጣው ዕድሜ፣ የህትመትና የሥርጭት ጉዳይ፣ የተቋሙን ጋዜጠኞች ባህርይና የትምህርት ዝግጅት ወዘተ በተመለከተም በሚገባ ገለጻ ካደረገልን በኋላ ሳንዘጋጅበት አንድ ከቋጥኝ የገዘፈ የጥያቄ ናዳ ወርውሮ ለግምት ዳረገን::
ጥያቄው፤ «ለመሆኑ የሀገራችንን ፖለቲካና መንግሥት እየመራ ያለው ማነው?» የሚል ነበር:: እኛም ተጠያቂዎቹ የፕሬዚዳንቱንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም አጠራር እንዳናበላሽ በመጠንቀቅ ተገቢውን አክብሮት ሳናጓድል ስማቸውን ነገርነው:: ፋታ ሳይሰጠን «ፉርሽ ናችሁ» ብሎ አፋችንን አሲያዘን:: እኛም «ካፈርን አይመልሰን» በሚል ድፍረት ከጉዞ በፊት ሸምድደን ያጠናነውን ማስታወሻ በማስታወስ የሀገሪቱን መንግሥት እየመራ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ስም ጠቀስነለት:: አሁንም መልሳችን ስላልጣመው ኩም አደረገን::
ምላሻችን አላጠግብ ያለው አስጎብኚ በንግግሩ ላይ የአሸናፊነት ፈገግታ አክሎበት እንዲህ አለን:: እርግጥ ነው ሀገራችን መሪ ፓርቲ አላት:: በሦስቱ ዋና መንግሥታዊ መዋቅሮቻችንም ጠንካሮች ነን:: ፕሬዚዳንታችንና ጠቅላይ ሚኒስትራችንም በወንበራቸው ላይ እንደተሰየሙ አሉ:: ይሄ ሁሉ እውነት ነው:: እርግጡን እንነጋገር ካልን ግን በሀገራችን የሚመነጩት ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና ደንቦች የሚተቹትና የሚደገፉት፣ እንዲተገበሩም የሚደረገው፣ ተጠቋሚዎች እንዲመረጡና ኃላፊነታቸውን ካልተወጡም እንዲወርዱ የሚገደዱት በሁለት ኃይላት ብርቱ ትግል ነው::
በእኛ ጋዜጣና ከመላው ሀገሪቱ በተሰባሰቡ ጎምቱ ጡረተኛ ዲፕሎማቶች ባቋቋሙት ቲንክ ታንክ ቡድን ግፊት:: አስጎብኛችን በሁኔታችን ግር እንደተሰኘን ስለገባው ሃሳቡን እየለጠጠና እያብራራ እስኪበቃን ድረስ ጋተን ማለቱ ይቀላል:: ይህ ገጠመኝ እንደገረመኝ ኖሮ እነሆ ቀኑ ሲደርስ የተጋትኩትን እውነታ አገርሽቶብኝ በብዕሬ ለማግሣት በቃሁ:: አሁን ይሄ ጋዜጣ «የአራተኛ መንግሥት ሥልጣን» ቢጎናጸፍ ይበዛበታል?
እግረ መንገዴን የጋዜጦቻችንን ነገር ሳስብ ሆድ ሆዴን የሚበላኝንና ደጋግሜ ጥያቄ ብጠይቅም ምላሽ ያላገኘሁለትን አንድ እንቆቅልሽ አስታውሼ ልለፍ:: ለመሆኑ እጅግ ተወዳጅና ተነባቢ የሆነውን ታሪካዊውን «የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ» ደብዛ እንዲጠፋ የወሰነውና ያስፈጸመው ግለሰብ ወይንም አካል ማን ነበር? ለምንስ ምክንያት? ምንስ ትርፍ ተገኝቶ? እነዚህን ጥያቄዎች ባሰብኩ ቁጥር የሦስት አስርት ዓመታቱ የብዕር ተፋላሚዎች ትዝታ ፊቴ ድቅን እያለ ስሜታዊ ያደርገኛል::
መቼም ግዙፉን የመወያያ ሃሳብ በነካ ነካ ማለፉ አግባብ ባይሆንም የሀገራችን ሚዲያ ጉዳይ ብዙ የሚያወያይ ይመስለኛል:: በይዘት፣ በቅርጽ፣ በባለሙያዎቹ የትምህርት ዝግጅት፣ ሥነ ምግባርና አለባበስ፣ በተልእኳቸውና በአፈጻጸማቸው ውጤታማነት ወዘተ ጠንከር ብለን ብንፈትሽ ስለ ተቋማቱም ሆነ ስለ ባለሙያዎቹ ብዙ ማለት የምንችል ይመስለኛል::
ሚዲያ በርግጥም «አራተኛው መንግሥት አካል ነው» ብለን የምናምን ከሆነ ተቋማቱም ሆኑ ባለሙያዎቹ በተገቢው መንበራቸው ላይ እንደተሰየሙ ሊያገለግሉን ይገባል ባይ ነኝ:: መንግሥትና የመንግሥት ሹሞች ሲያጠፉና ሲያበላሹ በአግባቡ ተጋፍጦ በመተቸት የሕዝብን ክብር ሊታደጉ ይገባል:: መልካም ሲሰሩም ደፍረው አበጃችሁ የሚሉበት ሞራል ሊገነቡ ግድ ነው::
«አዘውትራ የምታስካካ ዶሮ ዕንቁላል አትጥልም» እንዲሉ የብዕርን ጅራፍ እያጮኹ እኛን አንባቢዎቻቸውንና፣ አድማጭና ተመልካቾቻቸውን አጯጩኹን ማለት የሙያው ሥነ ምግባር የሚፈቅደው አይደለም:: ለሙያቸው የኖሩና የሞቱ በርካታ ምስክሮች እንዳሉን መዘንጋትም አግባብ አይሆንም:: ብዕር ወይንም ማይክራፎን ስለጨበጡ አለያም በቴሌቪዥን መስኮት ስለታዩ ብቻ ግብ አድርገው የሚቆጥሩ ጋዜጠኞች ካሉ እነርሱ ባለሙያዎች ሳይሆኑ የራስ ምስል ሻጭና ለዋጮች ናቸው::
ጋዜጠኝነት የከበረ ዋጋ አለው:: በሕይወት ያሉትን ተመስጋኞች ለጊዜው አቆይቼ ሁሌም ልናስታውሳቸው የሚገቡ ጥቂት ጀግኖቻችንን ዘክሬ ነገሬን ላጠናቅ:: የፕሬስ ዘውገኞቹ ጋዜጠኛ ነጋሽ ገብረ ማርያም፣ ከበደ አኒሳ፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ብርሃኑ ዘርይሁን፣ ጳውሎስ ኞኞ ከብዙ ምርጦች መካከል ትዝ የሚሉኝና በቅርብ የማውቃቸው ናቸው:: ጥቂቶቹን ብቻ መጥቀሴን ልብ ይሏል::
የሬዲዮን አእማድ፤ መምሬ አብራራው፣ አሳምነው ገብረ ወልድ፣ ዳሪዎስ ሞዲ፣ ታደሰ ሙሉነህ፣ አባይነሽና ንጉሤ አክሊሉ፤ በርቀት የሚገኘው አዲሱ አበበ… ከብዙዎች ጥቂቶቹ ናቸው:: ከቴሌቪዥን ጎራም ላስታውስ፤ ሚሊዮን ተረፈ፣ ጌታቸው ኃይለ ማርያም፣ ሉልሰገድ ኩምሳና ተክሉ ታቦር… እነዚህ ጎምቱ ጋዜጠኞች ዘመናቸውን የዋጁ የጊዜያቸውና የሙያቸው መልህቆች ነበሩ:: ካሻም የዘመናቸው «የአራተኛው መንግሥት አካል» ተጠሪዎች ነበሩ ማለትም ይቻላል:: ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011
በጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)