በጋምቤላ ክልል 11 የግል ከፍተና ትምህርት ተቋማት ያለ እውቅና የማስተማር ስራ ላይ መሰማራታቸውን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
ኤጀንሲው በግል ከፍተና ትምህርት ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ግድፈቶችን አስመልክቶ በተከናወነ የዳሰሳ ጥናት ላይ እና የዘርፉን ችግር ለመፍታት በሚያስችል የስነስርኣት መመሪያ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ወቅት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱአለም አድማሴ እንደተናገሩት፤ በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚስተዋሉ ችግሮች አንዱ ያለእውቅና መስራት ነው፡፡
በዚህም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ በተደረገ የዳሰሳ ጥናትና ድንገተኛ ፍተሸ 27 ተቋማት ከኤጀንሲው እውቅናና ፈቃድ ሳያገኙ ሲሰሩ ተገኝተዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ይህ ችግር በአዲስ አበባና አከባቢዋ ብቻ ሳይሆን በክልሎችም እየተስተዋለ ሲሆን፤ ለአብነት በጋምቤላ ክልል ሁለት ለሚሆኑ የርቀት ትምህርት እውቅናን ከመስጠት ባለፈ አንድም እውቅና የተሰጠው የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የለም፡፡
ሆኖም 11 ተቋማት በማስተማር ስራ ላይ ተሰማሩ ሲሆን፤ ከአጎራባች አገሮች ሳይቀር በተቋማቱ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መንግስት ችግሩን ለመፍታት እየሰራ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም ከእንደዚህ አይነት ችግሮች ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል፡፡
በወንድወሰን ሽመልስ