የኢሬቻ በዓል በነገው እለት ይከበራል። በመሆኑም ከወዲሁ፤
ኢሬቻ የአንድነትና የአብሮነት ዓርማ ነው!
ኢሬቻ ለሰላም፤ ኢሬቻ ለፍቅር!
Irreechi nageenyaaf Irreechi jaalalaaf
Irreechi Falaasama Dhugeeffannaa Oromooti!
የሚሉ ድምፆች ከፍ ብለው በመሰማት ላይ ናቸው።
በነገው እለት የሚከበረውን የኢሬቻ በአል አስመልክቶ በርካታ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ ”ኢሬቻ ለሰላም፤ ኢሬቻ ለፍቅር”፤”ኢሬቻ የሰላምና የወንድማማችነት/የእህትማማችነት ተምሳሌት ”ኢሬቻ የፍቅርና የወንድማማችነት መገለጫ ነው! ኢሬቻ የምስጋናና የእርቅ ተምሳሌት ነው!” በሚሉ መሪ ቃላት የተለያዩ ዝግጅቶች በመከናወን ላይ ነው።በኃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች ምርቃት (ኤባ) የተጀመሩ የፓናል ውይይቶች ሲካሄዱ ሰንብተዋል። በተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ውይይቶች ተደርገዋል። በየፓናሎቹ (ሕዝባዊ ውይይቶቹ)ም ከከተማ አስተዳደሮቹ አመራሮች ጀምሮ በተዋረድ እስከታች የሚገኙት አመራሮች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄ፣ ቄሮ፣ ቀሬ እና የአካባቢው ነዋሪዎችም መገኘታቸው ታውቋል።
ሕዝባዊ ውይይቶች ከተካሄደባቸው ክፍለ ከተሞች አንዱ በሆነው፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አስተዳደር የተካሄደውና ከአለባበስ ጀምሮ ሕብረ-ብሔራዊነት የታየበት መሆኑ የተነገረለት የፓናል ውይይት “ኦሮሞ” ማለት በአጭሩ ውሃ ጠይቀህ ማርና ወተት የሚሰጥ፣ እናትና አባት የሌላቸውን ተቀብሎ በጉዲፈቻ መልክ ለወግ ማዕረግ የሚያበቃ፣ የቅንነት፣ የመቻቻል እና የአብሮነት ዕሴት በእጅጉ የሚታይበት፤ የሀገር ካስማ (ዋልታና ማገር) ነው።” የሚለው ሀሳብ ጎልቶ የወጣበት ፓናል መሆኑን እዚህ ላይ በማሳያነት ጠቅሶ ማለፍ ተገቢ ነው።
ባለፈው ዓመት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴክተር ተቋማት ማስተባበሪያ ያዘጋጀው የ2014 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል አከባበር በተመለከተ ከ700 (የተወሰኑት እንኳን ለትውልድ ይተላለፉ ዘንድ በመጽሐፍ መልክ ቢዘጋጁ መልካም ነበር) በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዶ የነበረ መሆኑ፤ በውይይቱ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ከሁሉም ብሔር የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ የነበሩ መሆናቸውን በወቅቱ ተነግሮናል። የዘንድሮዎችን በቁጥር ባናውቅም በጥናትና ምርምር ሥራዎች የተደገፉ ፓናሎች መካሄዳቸውን አውቀናል።
እነዛ ሰነዶች እንደተስማሙበትም ሆነ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል አስመልክተው እየወጡ ካሉ መረጃዎች፣ እየተላለፉ ካሉ መልዕክቶችና እየተሰጡ ካሉ መግለጫዎች መረዳት እንደሚቻለው፤ ”ኢሬቻ” እና ”የኢሬቻ በዓል”፤ እንዲሁም ”የኢሬቻ በዓል አከባበር ሥነሥርዓት” የሚከተለውን ብያኔ ይዘው እናገኛቸዋለን።
በመጀመሪያ ደረጃ ኢሬቻ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ በመገንዘብ ወደ ርዕሰ ጉዳያችን እንሂድ።
ኢሬቻ
ኢሬቻ የምስጋና (ዋቃ) በዓል ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት ታላቅ በዓል ነው። ይሄን ስላደረግህልኝ፣ ከክረምት ወደ በጋ (ብራ) ስላሸጋገርከኝ አመሠግናለሁ እየተባለ ፈጣሪ የሚመሰገንበት የአደባባይ በዓል ነው።እሬቻ የዘመን መለወጫ በዓልም ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በማለፉ በኢሬቻ ቀን ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል።
ማኅበራዊ ደረጃ እና የእድሜ ልዩነት ሳይፈጠር፤ እስልምና፣ ክርስትና፣ ዋቄፈታ ሳይባል የኦሮሞ ሕዝብ በጋራ የሚያከብረው በዓል ነው። ለክርስቲያንና ለሙስሊም፤ እንዲሁም ለዋቄፈታዎች የእኩልነትና የአንድነት በዓል ነው።ምናልባትም ሁሉም ሃይማኖቶች በተናጠል ከነበራቸው የምስጋና ጊዜና እለት በአንድነት የሚገናኙበት ባህላዊ የምስጋና ሥርዓት ኢሬቻ ብቻ ነው።
“‘ፈጣሪያችን ሆይ አንተ ያጸደቅከው ነው አብቦ ፍሬ ያፈራው፤ ለዚህም እናመሰግንሃለን” በማለት እርጥብ ተይዞ ይወጣል፤ ፈጣሪም ላደረገውም ሁሉ ይመሰገናል።
ኢሬቻ የኦሮሞ ማኅበረሰብ የይቅርታና የመልካም ምኞት መገለጫ እሴት ነው። ኢሬቻ ትልቅ የወንድማማችነት መሠረት የሚጣልበት፣ የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት በዓል ነው። የተጣላ ታርቆ፣ ቂሙን ትቶ በነጻ ልቦና ፈጣሪ ንጹሕ ወዳደረገው የውሃ አካል ይሄዳል። ኢሬቻ ቀልብ የሚነጻበት ቦታ ነው።
የመስቀል /ጉባ/ በዓልን ተከትሎ የሚከበረው ኢሬቻ በፈጣሪና በፍጥረት መካከል ያለውን መስተጋብር የሚያጠናክር የገዳ ሥርዓት ፍልስፍና አካል ሲሆን፤ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ሀብት፤ የጋራ እሴት፤ የጋራ ቅርስ ነው።
አከባበር
የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር መቆየቱን ጥናቶቹ ያሳያሉ።
ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች መስፋፋትን ተከትሎ የገዳ ሥርዓትም ሆነ የኢሬቻ ክብረ በዓል እየተቀዛቀዘ መጥቶ ነበር ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ግን እየተጠናከረ ከኢትዮጵያ ባሻገር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የኦሮሞ ብሔር አባላት እያከበሩት ይገኛሉ።
በዋናነት ግን በኢትዮጵያ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፤ በቢሾፍቱ ከተማ ደግሞ የሆራ ሃር-ሰዲ ከመስቀል በዓል በኋላ ባሉት ቅዳሜ እና እሁድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በታደመበት በዓሉ ይከበራል።
የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ዋቃ ምስጋናውን ለማድረስ፤ ለመላው የሰው ልጅ ሰላምና ደኅንነት ፈጣሪውን ለመለመን የኢሬቻ በዓልን ያከብራል። ዋቃንም ያመሰግናል።
ቂምና በቀል፣ አለመግባባትና ጥላቻ ያለው ማንኛውም ግለሰብ ጥላቻውን ሳይሽር፣ እርቅ ሳያወርድ፣ የገደለ ሳይክስ፣ እጁ ንፁህ ያልሆነ ግለሰብ ወደ ኢሬቻ ክብረ በዓል አይሄድም።
… ኢሬቻ ከመድረሱ በፊት አባ ገዳዎች በየአካባቢያቸው፤ በየደረጃው ባለው መዋቅር ያሉትን ችግሮች ይፈታሉ። የተጣላውን ያስታርቃሉ፤ የገደለ እንዲክስ ያደርጋሉ።ይህም የሚሆነው ኢሬቻ ካለው እሴት መካከል ሠላምና እርቅ አንዱ ስለሆነ ነው።ስለዚህ የኢሬቻ ዕለት ሠላም ይታወጃል፤ ይወደሳል።በኢሬቻ በዓል ስለሠላም ይሰበካል።ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት፣ ከሰፊው ሕዝብ፣ ከፈጣሪና ከፍጡር ጋር በሠላም አብሮ መኖር እንደሚገባ ይታወጃል።
የኢሬቻ ስፍራ እርቅ የሚታወጅበት ስፍራ ነው።የኢሬቻ በዓል የፈጣሪና የፍጡር እርቅ የሚለመንበት ስፍራ ነው።የኢሬቻ ስፍራ ማኅበረሰቡ ስለጥፋቱና ስለበደሉ ፈጣሪውን ይቅርታ የሚጠይቅበት የእርቅ ስፍራ ነው።ሳያስቡ የተጋጩ ሰዎች እንኳን እርቅ የሚያወርዱበት ነው።ስለዚህ እሬቻ የእርቅና የአምላክ ምህረት የሚወርድበት ስፍራ ነው።ኦሮሞ በአባባሉ ‹‹Yoo namni walitti araarame, Waaqnis namaaf araarama›› ‹‹ሰው እርስ በርሱ ከታረቀ እግዚአብሔርም ይታረቃል›› የሚለው ለዚህ ነው።
ሥነሥርዓቱ
በነገው እለት ከማለዳው ጀምሮ ለዚሁ ክብረ በዓል ሲባል በተዘጋጀው አነስተኛ የተከተረ ውሃ ወይም ሆራ ፊንፊኔ በአባ ገዳዎች ምርቃትና የደስታ መልዕክት ተጀምሮ በድምቀት ይከበራል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፤ ከተለያየ የኦሮሚያ አካባቢዎችና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰበ የበዓሉ እድምተኛ ልዩ ልዩ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳትን በመልበስ፣ ኅብረ-ዝማሬዎችን በማሰማትና በመጨፈር ሥርዓተ በዓሉን በደስታ ለማክበር ወደ አዲስ አበባ ይገባል።
የአከባበር ሥነሥርዓቱን በተመለከተ ያሉት ጥናቶች እንደሚያሳዩት “በዚህ የምስጋና ቀን፤ ወደ ኢሬቻ ሲኬድ ለምለም ሳር እና አደይ አበባ ተይዞ ነው።እነዚህ የራሳቸው ትርጉም ሲኖራቸው፤ ለምለም ሳሩ ዋቃ (አምላክ) የለገሰውን ልምላሜ ተምሳሌት ሲሆን፤ የአደይ አበባው ደግሞ፤ አብቦ ያለውን የእህል አበባንና የፍካት ተምሳሌትነት ይኖራቸዋል።በነዚህም ፈጣሪውን ወይም ዋቃን እንደ ለምለም ሳሩ ልምላሜን ስጠን፤ ያንተ የፍካት ኃይል ከኛ ጋር ይሁን ብለው፤ ይለምኑታል፤ ያመሰግኑታል።
ወደ ሐይቅም በመውረድ በእጅ የያዙትን ሳር በመንከር ግንባር እያስነኩ ሁለት ነገር ይደረጋል።አንደኛው ምስጋና ማቅረብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ለቀጣዩ ፀሎት ማቅረብ ነው።በዚህ ሥርዓትም ከጨለማው ክረምት ወደ ብርሃን በሠላም ላሸጋገረ አምላክ (ዋቃ) ምስጋና ይቀርባል።የዘራውን እህል ስላበቀለለት ያመሰግናል።ዛሬን በሰላም እና በጤንነት ለመድረሱ ካመሰገነ በኋላ፤ ዓመቱ የሠላም፤ የብልፅግና፤ የጥጋብ እና የስኬት፤ እንዲሆንለትም ይለምናል።የጠፋን ፈልግልን፤ የታመመን ማርልን፤ የታሰረን ፍታልን … በማለት ዋቃን ይለምናል፤ ይመርቃል፡፡”
ዝግጅቱን አስመልክተው እየተለቀቁ ያሉት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በበዓሉ ላይ የተለያዩ ብሔረሰብ ተወካዮችም የሚታደሙ ሲሆን፤ ይህም በከፍተኛ ደረጃ የሥነ ሥርዓቱ ድምቀት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከአዲስ አበባው ቀጥሎ ኢሬቻ በሆራ ቢሾፍቱ የሚከበር ሲሆን፤ በዛ በኩልም አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ መጠናቀቁን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።
የቢሾፍቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱልሰላም መሐመድ፣ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ እንደገለፁት በዓሉን ለመቀበል በሁሉም ዘርፍ በቂ ዝግጅት ተደርጓል። ኅብረተሰቡን በማስተባበር ከተማውን ውብና ጽዱ የማድረግ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። ሰላምና ፀጥታን በተመለከተ የፎሌና የጸጥታ አካላት በቂ ዝግጅት እንዳለ ሆኖ ሕዝቡም ሰላሙን ለማስጠበቅ የተለመደውንና አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ሲሆን፤ ኅብረተሰቡን ለማገዝም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ ይገኛል።
በዓሉ በሰላም ተከብሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ሁሉ ተደርጓል። እንግዶች እንዳይጉላሉ የሚያደርጉ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም በሙሉ ተሠርተዋል።
ከላይ እየተመለከትን እንደመጣነው፣ የኢሬቻ ስፍራ የሚለቀስበት፣ የሚረጋገሙበት፣ የሁካታ ስፍራ ሳይሆን በንጹሕ ልቦና፣ ከቂምና ጥላቻ ውጭ ፈጣሪ የሚለመንበት ወይም የሚመሰገንበት ስፍራ ነው።ኢሬቻ ያጡትን ነገር ወይም የተቸገሩበትንና የተጨነቁበትን የሚለምኑበት፤ ላገኙት ወይም ለተደረገላቸው ደግሞ አንዱ ፈጣሪ (WAKKA)ን የሚያመሰግኑበት ስፍራ ነው።ባጭሩ፣ የምስጋና እና ምልጃ ስፍራ ነው።በመሆኑም ሥነሥርዓቱ ሙሉ ሰላምን ይፈልጋል።
ሰላምና ፀጥታ
የኢሬቻ በዓላት ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ እና ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበርም ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ፤ በበዓሉ ላይ ያልተገቡ ከትውፊቱ ያፈነገጡ ተግባራት እንዳይፈፀሙ፤ እንዲሁም የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ የሚያራምዱ ሰዎችን ለመከላከል በከፍተኛ ደረጃ እየተሠራ ሲሆን፤ ልክ እንደ መስቀል (ደመራ) በዓል ሁሉ፣ የኢሬቻ በዓልም በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ (እንዲከበር) ሁሉም ኅብረተሰብ መረባረብ፣ መተባበርና ሰርጎ ገቦች እንዳይኖሩ መሠራት ያለበት መሆኑ በተለያዩ መድረኮችና መገናኛ ብዙኃን እየተነገረ ይገኛል።
የኢሬቻ በዓል ባህላዊ ትውፊትን ፣ የአብሮነትና የኢትዮጵያዊነት ስሜትን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ማኅበረሰቡ በመስቀል በዓል ላይ ያሳየውን ትብብር በድጋሚ ሊያሳይ ይገባል።የኢሬቻ በዓል እንግዳ ተቀባይነታችንን የምናሳይበት መሆን ይጠበቅበታል።
የደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የኅብረተሰቡ አስተዋጽኦ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን የኢሬቻ በዓልም በሰላም እንዲከበር እና ኅብረተሰቡ የተለያዩ ተልእኮዎችን ይዘው የሚመጡ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ዓላማቸውን ለማክሸፍ አንድ ሆኖ በአንድነት መቆም አለበት።
በአካባቢያችን ላይ የሚከሰቱ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት በመከታተል በተለይም በዓሉ የኔ ነው በሚል መንፈስ ከሰላም ሠራዊት፣ ከጸጥታና ሌሎች ኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በጋራ በመሆን በመስቀል በዓል ላይ የተገኘው ድል በኢሬቻ በዓል ላይም መደገም ይገባል፡፡
አባገዳዎች፣ ስንቄዎች እና ሌሎች ኅብረተሰብ ክፍሎች በሚገኙበት የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል መስከረም 21 በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፤ መስከረም 22 በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ የሚከበር መሆኑ ታውቋል።
መልካም የኢሬቻ በአል!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2015 ዓ.ም