• ቴክኖሎጂውን በአማራ ክልል ተግባራዊ ለማድረግ ጠቀሜታውን ማስተማር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል
በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የአሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪዎች የጥፋት ክብረ ወሰን (ሪከርድ) መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ተግባራዊ በመሆኑ ከዕለት ወደ ዕለት የትራፊክ አደጋ እየቀነሰ መምጣቱ ተገለጸ። የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጌታቸው ጥሩነህ፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት በደንብ ቁጥር 208/2009 መሰረት ከህዳር ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ክልሉ የአሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪዎች የጥፋት ሪከርድ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ተግባራዊ አድርጓል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ ከመስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በደንብ ቁጥር 395/2009 መሰረት 8428 የሚል ባለ አራት ዲጂት አጭር የጽሁፍ መልክት ማስተላለፊያ አድራሻን እንደ አዲስ አሻሽሎ በማቅረብ የትራፊክ ህግና ደንቡን ለማስከበር እየሰራ ነው። ፕሮግራሙ በክልሉ መተግበር በጀመረበት 2010 ዓ.ም የመጀመሪያ መንፈቅ አመት 786 የትራፊክ አደጋ የደረሰ ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት 665 አደጋዎች ደርሰዋል።
ካለፈው አመት ተመሳሰይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 15 ነጥብ 39 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። በዚሁ ዓመት አጋማሽ 306 ከባድ የአካል ጉዳት በሰዎች ላይ የተመዘገበ ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ቁጥሩ ወደ 300 ወርዷል። ይህም የ 2 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። በተመሳሳይ በዚሁ መንፈቅ አመት 307 ቀላል የአካል ጉዳት የተመዘገበ ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም 275 ደርሷል። ይሄም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 48 በመቶ አደጋ መቀነሱን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል። ባለሙያው እንደሚሉት በ2010 ዓ.ም የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት 102 አደጋዎች በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት 56 አደጋዎች ደርሰዋል።
ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 48 በመቶ መቀነሱን ጠቁመዋል። ባለሙያው አክለውም የክልሉ ደንብ አስከባሪዎች አጭር የጽሁፍ መላኪያ ፕሮግራሙን በመጠቀም የትራፊክ ህግና ደንብ የተላለፉ 71 ሺ 779 አሽከርካሪዎችን የአጥፊነት ቅጣት በመቅጣት 18 ሚሊዮን 837 ሺ 242 ብር ገቢ አድርገዋል። እንዲሁም በደንብ ቁጥር 395/2009 መሰረት 17 ሺ 632 አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህግና ደንብ በመተላለፋቸው በአጭር የጽሁፍ መልክት አማካኝነት የጥፋት ሪከርዳቸው የተመዘገበ ሲሆን፤ 109 አሽከርካሪዎች በሪከርዳቸው መሰረት ተደጋጋሚ ደንብን መተላለፋቸው ተለይቶ ፤የመንጃ ፍቃዳቸው ታግዶ እንደጥፋታቸው መጠንም ከሶስት ወር እስከ ሁለት አመት ከማሽከርከር ታግደዋል።
ከነዚህ ውስጥ 30 አሽከርካሪዎች የሞት አደጋ ያስከተሉ መሆናቸውንም ባለሙያው ጠቁመዋል። በክልሉ 1ሺ300 የትራፊክ ፖሊሶችና ደንብ አስከባሪዎች የአሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪዎች የጥፋት ሪከርድ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር በመጠቀም ጥፋቶችን በአጭር የጽሁፍ መልዕክት በመመዘገብ የትራፊክ ህግና ደንብን እያስከበሩ ይገኛሉ።
በተመሳሳይም የአሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪዎች የጥፋት ሪከርድ መመዝገቢያ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ቴክኖሎጂ በተያዘው አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጥር አንድ ቀን ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ አቅጣጫ ቢቀመጥም፤ በአማራ ክልል የሚገኙ አሽከርካሪዎች መንጃ ፍቃዳችንን ሊቀሙን ነው፤ የአሽከርካሪዎች ማህበራት ፣ ደንብ አስከባሪዎችና ትራፊክ ፖሊሶች ደግሞ ቴክኖሎጂው ሆን ተብሎ በኛ ክልል ብቻ የሚተገበረው ከስራ ውጭ ሊያደርጉን ነው፤ በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ሥራው እንዳይጀመር እንቢተኝነት አሳይተው እንደነበር የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ታደሰ ገልፀዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ አንዳንዶች ቴክኖሎጂው ተግባራዊ ከሆነ ከስራ ልንቀነስ እንችላለን የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በመያዛቸው የክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስለቴክኖሎጂው ግንዛቤው ኖሯቸው ወደ ስራ መግባት እንደሚያስፈልግ በመታመኑ ቴክኖሎጂው ተግባራዊ አልተደረገም።
ዳይሬክተሩ የቴክኖሎጂውን ፋይዳ ከወረዳ እስከዞን ለሚገኙ አሽከርካሪዎች፣ የአሽከርካሪዎች ማህበራት፣ ለተሽከርካሪ ባለንብረቶች፣ በክልሉ ለሚገኙ ትራፊክ ፖሊስሶች፣ ለመንገድ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች፣ ለአመራሩና ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ በመሆኑ፤ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ሪከርድ አያያዝና አተገባበር ስልጠናው እንደተጠናቀቀ ተግባራዊ ለማድረግ በሂደት ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
ሶሎሞን በየነ