አዲስ አበባ፡- ከሁለት ወይም ከሦስት ዓመት በፊት ከነበረው ዛሬ የተሻለ የነጻነት አየር መኖሩንና ይህንን ያመጣው ደግሞ አዲሱ የለውጥ ኃይል መሆኑን የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ተናገሩ። አሁን ላይ በአገሪቱ ያሉ አለመረጋጋቶች በዚሁ ከቀጠሉ መቆጣጠር ወደማንችለው ችግር ውስጥ እንገባለን ብለዋል።
አቶ በቀለ ገርባ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት፣ በውጭ አገር በስደት የነበሩ በርካታ ሰዎች ወደ አገራቸው ለመመለስ ችለዋል፤ በሌላ በኩል ግን በቶሎ የእርምት እርምጃ ሊወሰድባቸው ሲገባ ያልተወሰደባቸው፤ መሻሻል ሲገባቸው ያልተሻሻሉ ጉዳዮች አሉ ።በዚሁ ከቀጠሉ መቆጣጠር ወደማንችለው ችግር ውስጥ እንገባለን ሲሉም አሳስበዋል።
ኢህአዴግ ውስጥ ስልጣን ላይ የነበሩ በብዙ ሙስናና ኢ-ፍትሀዊ ድርጊቶች ሲጠረጠሩ የነበሩ ግለሰቦች እስከ አሁን ያለመያዛቸውና አሁንም የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ወደፊት ለመንግሥት ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የህዝቦች መፈናቀልና እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶች ትኩረት ባለማግኘታቸው አሁንም ቀጥለዋል፡፡ ከሚገባው በላይ ዝም ማለት አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ለትልቅ ችግር የሚዳርገን በመሆኑ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ቶሎ ማስተካከል እንዳለበት አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
እፀገነት አክሊሉ