
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ለንብ ማነብ የሚያስችል ሰፊ ምቹ ሁኔታና ዕምቅ ሀብት ቢኖርም ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው በዝቅተኛ ደረጃ መሆኑ የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ትናንት በንብ ማነብ ተግባር ላይ ለመምከር የተጀመረውን ጉባዔ በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በርካታ የንብ ዝርያዎችና አምራቾች እንዲሁም ለሺ ዓመት የዘለቀ የንብ ማነብ ልምድ ቢኖርም ጥቅም ላይ የዋለው ካለው እምቅ ሀብትና ሊሰራ ከሚችለው አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለዚህ ደግሞ ዘርፉ በዘመናዊና ሳይንሳዊ መንገድ አለመደገፉ ዋናው ምክንያት ነው።
ጉባዔው የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮና ለረጅም ዓመታት ምርምር ያካሄዱ ሳይንቲስቶች ግኝቶቻቸውን የሚያቀርቡበት በመሆኑ እነዚህን በመጠቀም የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግና ጥራቱን ለማስጠበቅ ግብዓት የሚገኝበት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በግዮን ሆቴል የተዘጋጀው ኤግዚብሽንም የግልና የማህበር አንቢዎችን ከላኪዎች ጋር በማገናኘት ያለውን የገበያና የዋጋ ችግር ለመቅረፍ እንደሚረዳ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ያለው የንብ ማነብ ስርዓት ወደ ዘመናዊ መንገድ እንዲገባ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው በመግለጽ ሚኒስቴሩ የሚጠበቅበ ትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሊድ ባምቡ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ንብ አንቢና ከ10 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት እንደሚመረት በመጠቆም ከፍተኛው ቁጥር የሚመረተው በባህላዊ መንገድ መሆኑ ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል እንዳያድግ እንዳደረገው አስታውቀዋል። ዘርፉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለሌሎች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚያስችልም በመግለጽ ለዚህም የንብ እርባታ ኢንዱስትሪ መፍጠር፣ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት፣ የአካባቢ ጥበቃ ማካሄድና፣ ትንንሽ አምራቾችን መደገፍ ይጠበቃል ብለዋል።
«በኢትዮጵያ ንብ ማንባት ከሚቻለው የንብ ሀብት ጥቅም ላይ የዋለው አስር በመቶ ብቻ ነው» ያሉት የዓለም አቀፍ የንብ እርባታ ፌዴሬሽን (አፒሞንዲያ) ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፒተር ኩዝሙዝ ዘጠና በመቶ የሚሆነውን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ንቦች በምግብ ምርትና በአጠቃላይ የሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ ።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ፣ የንብ በሽታና የገበያ ሁኔታ አለመመቻቸት ዘርፉን እየተፈታተነው እንደሆነ በመግለጽ በኢትዮጵያም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በጉባኤው የተገኙ ሳይንቲስቶች የሚያቀርቧቸውን የጥናት ግኝቶችና ምክረ ሀሳቦች መጠቀም፤እንዲሁም በአንቢዎች መካከል የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥና የእውቀት ሽግግር ማካ ሄድ እንደሚገባ ብሎም በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው በሽማግሌዎች የተያዘውን የንብ ማነብ ሥራ ወጣቶች እንዲሳተፉበት ማድረግ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ሲምፖዚየሙ «በምግብ ምርት ሂደት ውስጥ የንቦች ልዩ ሚና» በሚል መሪቃል የሚካሄድ ሲሆን ከህዳር 21 እስከ 25 በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ በውይይትና በግዮን ሆቴል በኤግዚብሽን እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ