ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ቡሔ እንዴት ነበር ደስ በሚል ሁኔታ አሳለፋችሁ አይደል? ጎበዞች! ለመሆኑ በቡሔ ጨዋታ ምን ያህል ገንዘብ ሰበሰባችሁ፤ ምንስ ልታደርጉበት አቀዳችሁ? መቼም በልተንበታል አትሉኝም። ምክንያቱም ይህ ገንዘብ ብዙ ጥቅም አለው። የመጀመሪያው ለራሳችሁ የሚሆንና ቤተሰባችሁን ሊያግዝ የሚችል ተግባር ላይ ማዋል ነው። ምክንያቱም ቀጣይ አዲሱ የትምህርት ዘመን ስለሚጀመር ሁሉን ነገር ቤተሰባችሁ መሸፈን የለበትም። ስለዚህም የድርሻዬን አድርጌያለሁ ለማለት ያግዛችኋልና ደብተርና እስክሪብቶ እንደገዛችሁበት አምናለሁ።
ሌላውና ሁለተኛው ሁሉ ነገር ቀድሞ ከተዘጋጀላችሁ ምንም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስን ለመግዛት እንዲጠቀሙበት ማበርከት አለባችሁ። ለዚህ ደግሞ እንደ አዲስ አበባ በየወረዳው የተጀመሩ ሥራዎች አሉና ወደዚያ በመሄድ ማበርከት ትችላላችሁ። ይህንን ስታደርጉ ምን አይነት ጥቅም እንደምታገኙ የዛሬ 15 ቀን ያስነበብናችሁ ጽሁፍ ግንዛቤ የፈጠረላችሁ ይመስለኛል። ከጽሁፉ በኋላም ሆነ በፊት በጎ የምታደርጉ ልጆች እንዳላችሁ ደግሞ እርግጠኛ የሆንኩበት ነገር አለ። እንዴት ካላችሁ ለዚህ ምስክር የሚሆነኝን ልጅ ዛሬ እንግዳ አድርጌ አቀርቤላችኋለሁ።
አማኑኤል ዮሐንስ ይባላል። የአቡነጎርጎሪዎስ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። በትምህርቱ በጣም ጎበዝና ለሰው በጎ ማድረግ የሚያስደስተው ልጅ ነው። ትምህርት ትልቅ ዋጋ እንዳለው ያውቃል። ምክንያቱም እርሱ መሆን የሚፈልገውን የጠፈር ተመራማሪነት ማግኘት የሚችለው ከተማረ ብቻ እንደሆነ ይረዳል። ስለዚህም ትምህርትን በሚመለከት ለተጠየቀው ሁሉ ምላሽ ለመስጠት ይታትራል። ሰሞኑን የደረሰው ደብዳቤ ደግሞ ይህንን ተግባሩን በጉልህ የሚያወጣበት እንደሆነ ተሰምቶታል።
ደብዳቤው በወረዳ ደረጃ አዲሱን የትምህርት ዘመን ለመጀመር ደብተርና እስክሪብቶ ለሌላቸው ልጆች ድጋፍ ማሰባሰብን ይመለከታል። በዚህም በቻለው ሁሉ ለመደገፍ ቆረጠ። ጅማሮውንም ከቤቱ አደረገ። ጊዜው የእህቱን ልደት የሚያከብርበት ነበር። ሰው እየተቸገረ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል አለና ለልደቱ የተባለውን ሁሉ አሳምኖ ለልጆቹ ደብተር መግዢያ አደረገው። ከዚያም አለፍ አለና ማህተም በማስደረግ ጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ጋር በመሄድ ገንዘብ ማሰባሰቡን ተያያዘው። አንዳንድ መሰናክሎች ቢያጋጥሙትም በትዕግስትና ታማኝነቱን የሚያረጋግጥለትን ማህተም በማሳየት በብዙ መልኩ አሳክቶታል። ምክንያቱም በጎ ማድረግ ያለውን ጥቅም በደንብ ያውቀዋል። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ቤተሰቦቹ እንደሆኑ ይናገራል።
ልጆች በመስጠት ውስጥ ምን አለኝ እንደማይባል ነግሬያችኋለሁ አይደል? አማኑኤል ምን አለኝ ሳይል ለተቸገሩ ልጆች ለመድረስ ዝቅ ብሎ የሚያውቃቸውን ጎረቤቶቹን ለምኗል። ስጦታ ገንዘብ ብቻ እንዳልሆነ ቢያውቅም አሁን በገንዘቡ መግዛት ያለበት ነገር እንዳለ ተረድቷልና ገንዘብ እንዲያዋጡለት አድርጓል። ለዚህ ደግሞ ራሱን በፍቅር አነሳስቷል። በፍቅር መነሳት አንዱ ስጦታው እንደሆነም ያምናልና።
የመስጠትን ልብ መያዝ ካልተቻለ ገንዘብ ማሰባሰብ አይቻልም። ገንዘቡ ካልተገኘ ደግሞ እገዘዋለሁና እንደ ስጦታ አቀርብላቸዋለሁ ያልነውን አናገኘውም። ስለሆነም መጠን ሳይወስን መልካም ልብ መቅደም አለበትና አማኑኤልም ይህንኑ ነው ያደረገው። ልቡ ሀሴትን እያደረገ የእያንዳንዱን ቤት አንኳኩቶ ያሰበውን አድርጓል። ከሰዎችም 3000 ብር ሰብስቧል።
‹‹ድጋፍ አድርጉ ተብሎ እየተጠራ የእህቴን ልደት ማክበር ጭካኔ ነው። ትምህርት ለመማር ደብተርና እስክሪብቶ እንደሚያስፈልግ ተማሪ ስለሆንኩ አውቀዋለሁ። ይህ ከሌለኝ ግን ትምህርትም መዋያም አይኖረኝም። በዚህም አልባሌ ቦታ መዋያም ማደሪያም ይሆናል። በዚህ ውስጥ ደግሞ የማይፈለጉ ልምዶችን ላዳብር እችላለሁ። አንዱ ሱስ ነው። ›› የሚለው አማኑኤል፤ ለእነዚህ ልጆች ከአሁኑ ጀምረን ካልደረስንላቸው ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፤ ወደ ልመና ይገባሉ። ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ መዋያ ስለማይኖራቸው ሌባና አጭበርባሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለሆነም እኛን መልሰው የሚያጠቁና የሚደበድቡ እንዳይሆኑ ዛሬ ልንደርስላቸው ይገባልም ሲል ያሳስባል።
እርሱና ጓደኞቹ ማለትም ፍኖት ተስፉና ፍቅር ተስፉ የሚባሉት ልጆች ይህንን ሥራ ተጋግዘው ሲያደርጉት ለልጆች ልጆችም ድርሻ አላቸው ለማለት ያህል ነው። ይህንን ሥራቸውን አይተው ሌሎችም እንደሚከተሏቸው ስለሚያውቁ ያደረጉት ነው። ይህንን ተግባራቸውን ሁሉም ስለደገፈላቸው ደግሞ ደስተኛ ነው። በቀጣይም የራሱ እቅድ አለው። ምክንያቱም ልጆች የሚቸገሩት ደብተርና እስክሪብቶ ብቻ አይደለም። የሚለብሱት የደንብ ልብስን ጨምሮ የሌላቸው ብዙ ናቸው። የሚያደርጉት ጫማ የሌላቸውም እንዲሁ። ስለዚህም ቀጣይ ላይ ይህንን ለማድረግ አስቧል። ሰዎች ባይገፋፉንም የጠበበን፤ በቀጣይ አዲስ አሰፍተን የማንለብሰው ልብስና የማናደርገው ጫማ ካለን በቅርባችን ላሉ ልንሰጣቸው ይገባልም ይላል።
ሌላው አማኑኤል ያነሳው ነገር ልጆች የማስተባበር ሥራ ሲሰሩ ታማኝ መሆን እንዳለባቸው ነው። ምክንያቱም አሁን ገንዘብ ሲያሰባስብ ብዙ ነገሮች ገጥመውታል። አንዱ አለመታመን ነው። ለከረሜላ መግዢያህ ነው የሚሉት ሰዎች ጥቂት አልነበሩም። ለዚህ ንግግራቸው ደግሞ መነሻው ቀድመው ያዩት ነገር እንደሆነ ያምናል። ስለዚህም ታማኝ ሆነን ለለምንለት አካል ማድረስ ይገባናልም ባይ ነው። እርሱ ያደረገውም ይህንኑ ነው። የሚመዘግብበትን እስክሪብቶ ሳይቀር ከራሱ አድርጓል፤ ሰዎች ላይ ጥርጣሬ ላለመፍጠርም ከወረዳው ማህተም አስመትቶ እያሳየ ሰብስቧል። ስለዚህም ሰብሳቢ ሲሆኑ ከቻሉና ከተፈቀደላቸው ይህንን ቢያደርጉ መልካም እንደሆነ ይመክራል።
ልጆች አማኑኤል በጣም ጎበዝ ነው አይደል? ያደረገውን ነገር እንዴት ተመለከታችሁት? እርግጠኛ ነኝ ከእርሱ ሥራ ተምራችሁ እናንተም የምታደርጓቸው በርካታ ነገሮች ይኖሯችኋል። እስካሁንም እያደረጋችሁ ያላችሁ ትኖራላችሁ። በርቱ እሺ። ምክንያቱም በሰጠነው ውስጥ ያለውን እርካታ እየሰበሰብን ለውስጣችን ሰላም እንሰጠዋለን። በየቀኑ ብሩህ ቀን እንድናሳልፍም እንሆናለን። ነጋችንን ጭምር ለማሳመርም ይጠቅመናል። በተለይ በተለይ ጤናማ እንድንሆን ትልቅ አቅም ይሰጠናልና ሁልጊዜ ሰጪ እንሁን። ወላጆች ደግሞ ልጆቻችሁን በበጎ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ አድርጓቸው። በሉ ለዛሬ ይህንን ያህል ካነሳን እናብቃ። በሚቀጥለው ሳምንት በሌላ ጉዳይ እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22 /2014