የዛሬው ርእሰ ጉዳያችን አጠቃላይ አገር በቀል እውቀቶቻችን፣ አገራዊ እሴቶቻችን በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ፤ ለአገራዊ ችግሮች ምን አይነት መፍትሄዎችን እንካችሁ እያሉን እንደሆነ … እንመለከታለን። ከሁሉም በፊት ግን መሰረቱ “አገር በቀል እውቀት” የሚለው ነውና እሱን እንበይን።
አገር በቀል እውቀት ማለት በውስን አካባቢዎች ላይ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ገጽታዎች ዙሪያ ላሉ ክፍተቶች መፍትሄ ይሆኑ ዘንድ ባህላዊ በሆነ መንገድ በአንድ ወይም በተወሰኑ ሰዎች የሚመነጭና የሚተገበር እውቀት ነው፡፡ በእንግሊዝኛው በዋናነት “Indigenous knowledge” የሚለው የሚገልፀው ሲሆን “Traditional knowledge“ ወይም “Local knowledge” የሚሉትም ሊተኩት ይችላሉ። የማህበረሰብ እውቀት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ የሕይወት ገፅታዎች የሚዳሰሱበትና መፍትሄ የሚሰጥበት የተገለፀና ያልተገለፀ እውቀትና ልምድን ያጠቃለለ ነው፡፡
በብዙ ዘመናት ልምድ የዳበረና በባህል ውስጥ ሰርፆ ከትውልድ ትውልድ በታሪክ፣ በዘፈን፣ በአባባል፣ በእምነት እና በሌሎች መንገዶች በአካባቢው ቋንቋ የሚተላለፍ እውቀት ነው፡፡ እውቀቶቹ በተገኙበት ቦታ ምንጭ ለሆኑት ግለሰብና ቤተሰብ የተሰጠ ልዩ ጥበብ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን በአብዛኛው ግን በጊዜ ሂደት በአካባቢው ማህበረሰብ እየተለመደና እየሰፋ ሲመጣ የማህበረሰቡ የጋራ ንብረት ይሆናል፡፡ እንደ አገራችን ባሉ በተፈጥሮ ሀብት በበለፀጉ አገራት በተለይ በግብርና፣ በጤና እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች የአገር በቀል እውቀቶች እና ቴክኖሎጂዎች ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪም በትራንስፖርት ዘርፉ የአገር በቀል እውቀቶች እና ቴክኖሎጂዎች ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ በግብርናው ዘርፍ የእፅዋትና አዝርእት ተከላ፣ መረጣና አሰባሰብ ሂደት፣ በእንስሳት እርባታና አያያዝ ስርዓት እና ለመሳሰሉት ተግባራት መሠረት የሚሆን በግለሰብና በማህብረሰብ ውስጥ የዳበሩ ብዙ እውቀቶች አሉ፡፡ (hawassa online.com)
ለጠቅላላ ግንዛቤ ይህንን ከያዝን፤ በአገር በቀል እውቀት እነማ ተጠቃሚ ሆኑ፤ ምንስ አተረፉ የሚለውን ከመቃኘታችን በፊት፤ ከአገር በቀል እውቀት ክፍሎች፣ በተለይም በማይዳሰስ ቅርስነት የሚታወቀው ስነቃል መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ ወደ ሆነው ጥንታዊ ፍትህ አሰጣጥ ስርአት እንሂድ።
የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር (2009) ለንባብን ባበቃው ጥራዝ ውስጥ ተገልፆ እንደሚገኘው ከሆነ ”ጥንታዊ ፍትህ አሰጣጥ ስርአት” ምድቡ ከ”የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ” ሲሆን፤ ”ባህላዊ የዳኝነትና የእርቅ ስርአቶች፤ ግጭቶችና አለመግባባቶች የሚፈቱበት ባህላዊ የእርቅ መንገድ ነው።” ፋይዳውም ማህበራዊ፣ አላማውም የፍትህ ስርአትን በማንገስ ግጭቶችን በማስወገድ፣ በሰላማዊ መንገድ በመፍታት አካባቢያዊና አገራዊ ሰላምን ማስፈን … ወዘተ ነው።
አገር በቀል፤ የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ቅርስ የሆነው «ጥንታዊ ፍትህ አሰጣጥ ስርአት» በድሮው ዘመን በችግር ፈቺነቱ የታወቀ ሲሆን፤ በተለይ በ«በላ ልበልሃ» የፍርድ ሂደት (የከሳሽና ተከሳሽ ምልልስ) መደበኛውን ፍርድ ቤት ተክቶ ይሰራ እንደ ነበር ይታወቃል።
ለዚህም፤
በላ ልበለሃ
የአፄ ሥርዓቱን፣
የመሠረቱን፣
የአብርሃም ራቱን፣
አልናገርም ሐሰቱን፣ ሁል ጊዜ እውነት እውነቱን።
የሚለውንና ተደጋግሞ የሚመጣውን አዝማች ማስታወሱ በራሱ በቂ ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ሳይቋቋሙና የወንጀለኛ መቅጫ እና የፍታብሄር ህግ ተረቆና በአዋጅ ፀድቆ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ህዝቡ ለፍትህና ርትእ ስፍነት ሲጠቀምበት የኖረ፤ በአገር ሽማግሌዎች የሚዳኝበት ባህላዊ የፍርድ ሂደት ነው።
እንደ አጠቃላይ ብያኔም፤
“በላ ልበልሃ” እስካሁንም በተለይ ከከተሞች ርቀው በሚኖሩ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች እየተጠቀሙባቸው ከሚገኙት ባሕላዊ ሽምግልናዎች የተለየ የሚያደርገው መሰረታዊ ልዮነት ያለው የዳኝነት ስርዓት አለው፡፡ ይኸውም በዳይና ተበዳይ /ከሳሽና ተከሳሽ/ ዳኞች ፊት ቀርበው ክርክር የሚያደርጉት በስነ ግጥምና በቅኔ መሆኑ ነው፡፡ ህዝቡም ዙሪያቸውን በመታደም የፍርድ ሂደቱንና ክርክሩን የሚከታተል ሲሆን፤ በተለይ “በበላ ልበልሃ” ክርክር አሸናፊ የሆነ ሰው በሙግት አዋቂነቱና በግጥም ችሎታው ከህብረተሰቡ ከፍተኛ አድናቆትንና ከበሬታን ያገኛል፡፡
የሚለውን ብያኔ በጋራ መግባቢያነት መውሰድ ይቻላል። (ከ”በላ ልበልሃ” ጋር በተያያዘ የስለሺ ለማን ”በላ ልበልሀ” መጽሐፍ መመልከት ተገቢ ይሆናል።)
ይህ መደበኛውን ፍርድ ቤት ተክቶ (ወይም በሌለበት) ሲያገለግል የኖረው ነባሩ «በላ ልበልሀ» የፍርድ ሂደት እንደ አገር በቀልነቱ ዘመናዊውን የፍርድ ሂደት ሲያግዝ አልታየም። እንደውም እንደ ኋላ ቀር አሰራር ተቆጥሮ ተወረወረ እንጂ ለፍትህና ርትእ አገልግሎት አልታጨም። ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ሰአት በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች ይህ «ጥንታዊ ፍትህ አሰጣጥ ስርአት» የህዳሴ ዘመኑ የመጣ ይመስላል። ወደዛ ከመሄዳችን በፊት ግን የአገራትንን ልምድ እንቃኝ።
አገር በቀል እውቀትን በተገቢው መጠን መጠቀም የቻሉ አገራት በርካቶች እንደሚሆኑ መጠራጠር አይቻልም። ይሁን እንጂ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ አገራት ደግሞ አሉ።
እንደ አገር ስንመለከተው ጃፓን የብዙዎችን ምስክርነትና እውቅናን አግኝታለች። ባህሏን ሳታስነካ፣ ማንነቷን አስከብራ ማደግ በመቻሏ በምሳሌነት እየተጠቀሰች ትገኛለች። ታይላንድና ጃፓን የመሳሰሉት አገራት በሳይንስና ምርምር አሁን ለደረሱበት የእድገት ደረጃ መሰረታቸው አገር በቀል እውቀት መሆኑን በርካታ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የቻይናን የተመለከትን እንደሆን ጉዳዩ ወደ ላይ ከፍ ብሎ እናገኘዋለን።
ቻይና አገር በቀል እውቀትን እንዲሁ እንደ ዋዛ የምትመለከት አይደለችም። አጥብቃ እንደ ያዘችው የኮንፊሺየስ አስተምህሮ ሁሉ አገር በቀል እውቀት ያፈራቸውን እሴቶች ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ተግባር በመቀየር፤ በተቋማት ደረጃ በማደራጀት ከራሷም አልፋ ወደ ሌሎች አገራት በማዛመት በከፍተኛ ደረጃ የጂዲፒዋ መደጎሚያ አድርጋዋለች።
እንግሊዝ በመንግስት ደረጃ አንድ ጠብሰቅ ያለ ስለ ባህላዊ ህክምና የሚያስተምር መጽሐፍ (ከኢትዮጵያ የዘረፈችውን ተርጉማ ነው የሚሉ አሉ) አሳትማ ለዜጎች አሰራጭታለች። እንዲህ እንዲህ እያልን ከሄድን የብዙ አገራትን ተሞክሮ ማየት እንችላለን።
አሁን ወደራሳችን እንምጣና አገር በቀል እውቀታችን ያለበትን ወቅታዊ ይዞታ እንመልከት።
ዛሬ ዛሬ አገር በቀል እውቀቶች እንዳይጠፉ መጠበቅ፣ እውቀትን ለትውልዱ በሚገባ በማስተማር ተጠቃሚ ማድረግ፣ የግብረግብ ትምህርትን በስፋት ማስተማር፣ ስለ እፅዋት ጥበቃና እንክብካቤ፣ ስለ መድኃኒት እጽዋት፣ ስለ ጥንታዊ ሥዕሎች አሳሳል፣ ስለ ቀለማት አቀማመም እና ስለ ጂኦሎጂ የድንጋይ ጥበብ ማስተማር አገራችን የተያያዘችውን የብልጽግና ጎዳና የሰመረ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑ በብዛት እየተነገረ ነው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይቀር ጉዳዩ የብዙዎች ርእሰ ጉዳይ እየሆነ ነው። በርካታ ጥናቶች እየቀረቡ መደረግ ያለበትን መደረግ ከሌለበት እየለዩ እያመለከቱ ይገኛሉ። ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም እየተነቃቃ ያለ ይመስላል።
ባለፈው አመት በወሎ ዩኒቨርሲቲ አገር በቀል እውቀት ላይ ያተኮረ 6ኛው ዓለም አቀፍ አውደ “ወረሽኝን ለመከላከልና ለአገር ሰላም ግንባታ” በሚል 19 የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ነበር፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የአገር በቀል ዕውቀቶች ለአገር ያላቸውን ፋይዳ የሚመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡ መንግስትም ለአገር በቀል ዕውቀቶች ትኩረት መስጠቱም ተመላክቷል፡፡
ከአርት አኳያም አያልነህ ሙላት በአንድ ወቅት ከአርትስ ቲቪ ጋር ባደረጉት ተከታታይ ውይይት ”ለችግሮቻችን መፍትሄው አገር በቀል እውቀት ነው” ሲሉ መደመጣቸውም ይህንኑ የአገር በቀል እውቀትን አስፈላጊነት የሚያሰርፅ ሆኖ ነው የምናገኘው።
ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ስናመራ የምናገኘው ተመሳሳይ ሲሆን፤ መጋቢት 2011 «አገር በቀል እውቀትና ትምህርት በኢትዮጵያ፤ ፋይዳው፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት አቅጣጫው” በሚል ርዕስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት ፋካልቲ ያዘጋጀው አገር አቀፍ ዐውደ ጥናት ተካሂደ።» በሚለው የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ “በዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ አገር በቀል እውቀትንና ትምህርትን በማካተት ሞራልና ግብረገብ ያለው ትውልድ መቅረጽ እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ፡፡” የሚል ተካትቶ ማንበባችን አይዘነጋም።
አላማውም “ጠቃሚ አገር በቀል እውቀትና ትምህርትን በጥናት በመለየት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የሚካተቱበትንና ለትውልድ የሚተላላፉበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር” እንደነበርም እንደዛው። (ይህን ስንል ነጋድራስ ገብረ-ሕይወት ባይከደኝ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በአገራችን ስለሚገኙ ብሄራዊ ችግሮች ውስጥ ሙግትን በሚመለከት የፃፉት እንዳለ ሆኑ፤ የጠቀሷቸው ችግሮች እስከተፈቱ ድረስ ነው።)
በውይይቶቹም “አገር በቀል ዕውቀትን በዘመናዊ ሥርዓተ ትምሀርት ውስጥ በይዘትና በማስተማሪያ ዘዴ ማካተት ይገባል፡፡”፤ “የአገር በቀል እውቀትና ትምህርትን ፋይዳ በሚገባ በመረዳት ሞራልና ግብረገብነትን የተላበሰ ኅብረተሰብ መፍጠር ያስፈልጋል፤” እስካሁን በአገሪቱ የተተገበሩት ሥርዓተ ትምህርቶች የአገሪቱን የኋላ ታሪክ ያላካተቱ፤ የወደፊት ጉዞዋን መሠረት ያላደረጉና ከምዕራባውያን የመጣውን በጭፍኑ የተቀበሉ” በመሆናቸው በአገር በቀል እውቀቶቻችን ሊተኩ ይገባል፤ ኢትዮጵያ “በሥነ ፈለክ፣ በሕክምናውና በማዕድን ጥናት ዓለምን የሚያስደምሙ እውቀት ነበሯት” ግን አልተጠቀመችበትም፤” አገር በቀል እውቀት አሁን ባለው ሥርዓተ ትምህርት ባለመካተቱ አገሪቱዋን ወደፊት መራመድ አልቻለም”፤
«የአገሪቱ ሥርዓተ ትምህርት ከመነሻው ለአገር በቀል እውቀት ትኩረት ያልሰጠ» መሆኑ፤ «ዘመናዊው የትምህርት ሥርዓታችን በምዕራባውያን ፍላጎትና ተጽእኖ የተቀረፀ በመሆኑ ከአገር በቀሉ እውቀትና ትምህርት ጋር ማጣመር» እንደሚያስፈልግ፤ «ስኬት አካባቢን በማወቅ የሚመጣ» በመሆኑ «አገር በቀል እውቀትን በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ በማካተት መመርመርና ማጥናት» እንደሚያስፈልግ፤ «በባእዳን የተዘረፉ መጻህፍትና ቅርሶችን ማስመለስ፣ ያሉትን ጥበቃ ማድረግና መመዝገብ እንዲሁም በአገር በቀል ምሁራንና ተመራማሪዎች ጥናት እንዲደረግባቸው በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር እንደሚገባም»፤ «ለአዲሱ ትውልድ ቀደምት የነበረውን የመከባበርና የመረዳዳት ባህል በአገር በቀል እውቀትና ትምህርት ማዳበር» እንደሚያስፈልግ … እና የመሳሰሉት በጥናቶቹ ላይ የተመሰረቱ አስተያየቶች ቀርበው እንደ ነበር ተገንዝበናል።
ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት፣ በኦሮሚያ ክልል የቡሶ ጎኖፋ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገረመው ኦሊቃ እንደሚሉት የክልሉ መንግስት የገዳ ስርአት አካል የሆነውንና ባህላዊውን ቡሶ ጎኖፋ ወደ ዘመናዊነት አሳድጎ፤ በቢሮ ደረጃ አዋቅሮ … ወደ ስራ ይግባ እንጂ፤ እንደ አገር ከታየ አገር በቀል እውቀቶቻችንን ገና አልተጠቀምንባቸውም።
ከላይ ዘመኑ የአገር በቀል እውቀታችን ህዳሴ ነው ስንል ያለ ምክንያት አለመሆኑን እነዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (አምቦና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችንም ጨምሮ) እንቅስቃሴዎች ያሳያሉ ብለን እናስባለን። ይህ ማለት ግን አፍን ሞልቶ ሰርቷል በማስባል እጅና እግርን አጣጥፎ የሚያስቀምጥ ነው ማለት አይደለም። በተለያዩ መድረኮችና ሁኔታዎች «ገና ብዙ ይቀራል» እንደሚባለው አሁንም ገና ብዙ ይቀራል። አገር በቀል እውቀቶቻችን የሁላችንም እስኪሆኑ ድረስ፤ በሁላችንም ተቀባይነት እስኪያገኙ ድረስ፤ ተቋማዊ አደረጃጀቶች እስከኖሯቸው ድረስ፤ ሁላችንም «የ’ኛ» እስክንላቸው ድረስ …. መሰራት አለበት። ከዛ በኋላም እንደዛው፤ ከሁኔታው ጋር በሚሄድ መልኩ ጥናትና ምርምሩ ይቀጥላል ማለት ነው።
ከላይ አትኩረንበት ወደ ነበረው፤ «የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ” ወደ ሆነው፤ እውነትን ወደ አደባባይ የማውጣት ባህልን፤ እንደበተ ርቱዕነትን፤ በራስ የመተማመንና ባህሉንም ከማስተላለፍ አኳያ «የተዋጣ» የተባለለትን፤ «ጥንታዊ ፍትህ አሰጣጥ ስርአት» እንመለስና አሁናዊ ይዞታውን እንመልከት።
ዶናልድ ሌቪን በ‹‹ዋክስ ኤንድ ጎልድ (ሰምና ወርቅ) መጽሐፋቸው «ሙግት በአማራው ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ጉዳት ጠቅሰው አልፈዋል፡፡ ቻይናዊያን ይህንን ባህል አይጠቀሙበትም ነበር፡፡ ወደ ፍርድ ቤት መሄድን እንደጊዜም ሆነ ገንዘብ አባካኝነት ይቆጥሩት ነበር፡፡ በቻይና ባለጉዳዮች በሻይ ቤት ውስጥ ተሰብሰበው በመወያየትና በመደራደር በመካከላቸው ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ይሹ ነበር፡፡» በማለት ማስፈራቸውም ብዙ ጊዜ የሚጠቀስላቸው ሀሳባቸው ነው።
ጄነራል ቨርጂን «እኔ የማውቃት አቢሲኒያ» The Abyssinia I know መጽሐፋቸው በተሟጋቾች መካከል የሚደረገውን ሰርዓት ማራኪ መሆኑን፤ የነበረውን የቃላት አጠቃቀም፣ በተሟጋቾች መካከል የሚደረግ የሰውነት እንቅስቃሴ ሳይቀር እጅግ ውብ እንደነበር መፃፋቸውም በመስኩ አጥኚዎች በኩል ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።
ችግር ባለበት ስፍራ ሁሉ የፍትህና ርትእ ጉዳይ አንገብጋቢ የመሆኑ ጉዳይ የግድ ነው። በመሆኑም የዳኝነት ስርአት ጉዳይ የማይታለፍ ሆኖ ከፊት ድቅን ይላል። በዚህ ጊዜ የተለያዩ አማራጮችን መፈለጉ የማይቀር ይሆናል ማለት ነው።
በዚህ፣ ከዘመናዊው የፍትህ ስርአት ባሻገር አማራጭ ይፈለግ ከተባለ ወደ የትም ሳይሆን የሚኬደው ወደ አገር በቀል እውቀት ያፈራቸው እሴቶቻችን መሆኑ የማይቀር ነው። ይህም የሚወስደን ወደ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ወደ ሆነው ጥንታዊ ፍትህ አሰጣጥ ስርአት ነው። «ለመሆኑ ይህ ስርአት በአሁኑ ሰዓት ነፍሱ አለ?» የሚል ጥያቄ ከተነሳ መልሱ «አዎ፤ አለ»። የመኖሩን ማረጋገጫ እንመልከት።
በሕይወት ስለ መኖሩ ማረጋገጫችን በቅርቡ በማእከላዊ ጎንደር ዞን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከተያዙ ሰዎች (መዝገቦች) ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ አፈፃፀም የተመዘገበው በባህላዊ ፍትህ አሰጣጥ ስርአት አማካኝነት መሆኑን ስንሰማ ነውና፤ ወደ ፊት ከዚህ የበለጠ ይሰራበታል ብለን እንጠብቃለን።
በማጠቃለያችን የአገር በቀል እውቀታችን ወቅታዊ ይዞታ ምን እንደሚመስል በማሳየት መሰናበት ሲሆን፤ የጥንታዊው የፍርድ አሰጣጥ ስርአቱ በተወሰኑ አካባቢዎች እየተሰራበት ይገኛል። በኦሮሚያም ወደ ዘመናዊ አሰራር የተሻገረው ቡሶ ጎኖፋም እንደዚሁ እየተሰራበት ነው። በደቡብ ጎንደር ዞን የሆነውም ከላይ እንዳየነው ነው። በመሆኑም ሌሎችም ከዚህ አፈፃፀም ልምድ ቢወስዱና አገር በቀል እውቀቶቻችንን ብንጠቀምባቸው የተሻለ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20 /2014