የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶችን በጽህፈት ቤታቸው አዳራሽ ተቀብለው ባለፈው ሳምንት አወያይተዋል። ወጣቶቹ በሀገራዊ፣ ቀጣናዊና በራሳቸው ጉዳይ ላይ ላነሷቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
ወጣቶቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችና መልሶ ለማቋቋምና የተቋረጡ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ከማሟላት አንፃር ምን ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠር ምን አይነት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ይገኙበታል።
በትግራይ ያለውን ድህነት ለማጥፋትና አሁን ላይ በህዝቡ ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ እንዲያበቃ ለማድረግ መንግስት ምን እየሰራ እንደሚገኝና ከለውጡ ጋር በተያያዘ የወጣቱ ቀጣይ ሚና ምን መሆን እንዳለበትም ከወጣቶቹ ጥያቄ ቀርቧል።
በሃረሪ ክልል ያለውን የቱሪዝም መሰረተ ልማት ችግር ከመፍታት አንፃር ምን አይነት ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉና በከተማዋ የሚታየውን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ በመንግስት በኩል ምን እየተሰራ እንደሚገኝም በወጣቶቹ ተጠይቋል።
ሸኔ በኦሮሚያና በሌሎች ብሄር ተወላጆች ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያ ለማስቆምና ሸኔ ያለባቸውን አካባቢዎች ለማፅዳት ምን እንደታሰበ ከዚህ አኳያ የወጣቶችስ ሚና ምን መሆን እንዳለበትም ወጣቶቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት አንፃርም በመንግስት በኩል ምን እየተሰራ እንዳለም ተጠይቋል።
በሱማሌ ክልል ሩዝን በስፋት ለማልማትና የእንስሳት ሀብትን ለማዘምን ምን ታስቧል የሚል ጥያቄም በወጣቶቹ የተነሳ ሲሆን፤ ድሬዳዋን በሚመለከትም የድሬዳዋን ህዝብ ኑሮን ለማሻሻል መንግስት ምን እየሰራ እንደሚገኝ ተጠይቋል።
አዲሱን የደቡብ ምእራብ ክልልን ሀብት በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋልና ክልሉንም ለማጠናከር በመንግስት በኩል ምን እንደታሰበ፣ በቤኒሻንጉል ክልል ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት መንግስት ምን እየሰራ እንደሚገኝ፣ በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ረገድስ በመንግስት በኩል ምን እንደታቀደም ወጣቶቹ ያነሱት ሌላው ጥያቄ ነው።
የስራ እድል ፈጠራና የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስት በኩል ምን አይነት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ከወጣቶቹ ጥያቄዎች ተነስተዋል። በነዚህና በሌሎች ጥያቄዎች ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ኢትዮጵያን እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እኛም አውቀን አልጨረስናትም። ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች አሏት ግን አውቀን አልጨረስነውም። የአፍሪካ 50 ከመቶው ተራራ በኢትዮጵያ የሚገኝ ቢሆንም ተራራን ማልማት፣ በተራራ ውስጥ መጓዝና የተራራን ጥቅም ለማወቅ ብዙ መንገድ ይቀረናል። ከዚህ አኳያ ሀገራችንን ለማወቅ ብዙ መጣር አለብን።
በቀጣይ የሚታሰበውም አንድ ወጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ካጠናቀቀ በኋላ ወደዩኒቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት ለጥቂት ወራት ብሄራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ነው የሚፈለገው። ይህን አገልግሎት ወጣቱ ከአካባቢውና ከክልሉ ውጪ ያለውን ሀገራዊ ሁኔታ ለማየት ይጠቀምበታል። ይህም በፍቃደኝነት ነው የሚሆነው። ነገር ግን ደግሞ ሀገሩን የማያውቅ ወጣት ስራ አይቀጠርም።ለስራ ቅጥር አንዱ መመዘኛም ሀገርን ማወቅ ይሆናል።
ኢትዮጵያ የሆነ ጊዜ ላይ ጠንካራና ሃያል ሀገር ነበረች። ኢትዮጵያ ልክ እንደ ንስር አሞራ ሶስት ነገሮችን አጥታለች። አንዱ ያጣችው ነገር ሰው ነው። ዜጎቿን በፍቅርና በአንድነት ማቆየት አልቻለችም። ያጣቸው አንድነትን ቢሆንም ታዲያ አንድነት ሲባል ግን አንድ አይነት ማለት አይደለም። በፆታ፣ በቋንቋና በእምነት ልዩነት አለ። ስለሆነም እንደ ንስር አሞራ ዳግም ራስን ለማደስ እንደሀገር አንድ ሀገራዊ ማንነት ይዞ ለመቆም የሚያስችልና የሀገርን ማስጠበቂያ አውድ መመለስ አለበት። ለዚህም የራሱ ሂደት ይጠይቃል። ይህን ካደረግን የውጪ ተፅእኖ ይቀንሳል። ይህ እንዲሆን ደሞ ከአቧራ ፖለቲካ ወደ አሻራ ፖለቲካ መቀየር አለበት።
ሁለተኛው ኢትዮጵያ ያጣችው ነገር የተፈጥሮ ሀብቷን ነው። ተፈጥሮ የሰጣትን አውድ ተገንዝባ መጠበቅ አለመቻል ነው። የተፈጥሮ ሀብቷም ተረስቷል። ሶስተኛው የኢትዮጵያ ሃይልና ጉልበት የነበረውና ሀገሪቱ ያጣችው ነገር ደግሞ ከመሬት ተነስቶ ፈጣሪን ማናናቅና መጥላት ነው። ይህም በመንግስትም በኩል የሚታይ ነው።
ስለሆነም እንደ ንስር አሞራ ዳግም ራስን ለማደስና ወደነበርንበት ለመመለስ በተፈጥሮ ሀብትና በአንድነት ላይ መስራት ፈጣሪን መክዳት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው መረዳት ይገባል። እነዚህ ሶስት ጉዳዮችን መመለስ ሲቻል ኢትዮጵያ ወደነባር ከፍታዋ ትመለሳለች። ከዚህ አንፃር እናንተ ወጣቶች ኢትዮጵያ የጎደሏትን ሦስት ነገሮች መመለስ አለባችሁ።
ለዚህም ወዷኋላ መለስ ብሎ የነበሩ ለውጦችን መቃኘት ያስፈልጋል። ለምን በፍጥነት እንደወደቅን ማጤን ይገባል። ምን ብናደርግስ ነው ከውደቀት አገግመን ልንድን የምንችለው የሚለውን ማሰብ ይኖርብናል። ቀደም ሲል ከነበሩት መንግስታት በወታደራዊ ሀይል መምጣት ጥቅም አልባ ስለመሆኑ ትምህርት መውሰድ ይገባናል። ከዚህ አኳያ ቅድሚያ ሰጥተን የሰራነው የዲሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር ነበር። ለዚህም ምርጫ ቦርድን፣ እምባ ጠባቂን፣ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን፣ ፍርድ ቤትን፣ ሲቪክ ማህበራትን የሚያጠናክሩ ህጎች ላይ ተሰርቷል፤ ተቋማቱ ከፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ በሆኑ ሰዎች እንዲመሩ ተደርጓል። የሚዲያ ነፃነት እንዲመጣም ተደርጓል።
ከዚህ በኋላ ደግሞ ሕወሓትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር አብረው እንዲሰሩና እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። ምርጫ ካሸነፍን በኋላም ብቻችንን እንምራ አላልንም። ሌሎች ፓርቲዎችም ከኛ ጋር ይሁኑ ብለን መንግስት ይሁኑ ብለናል።
ይህ ብቻ በቂ ስላልነበረ ሶሻል ካፒታል እናጠናክር ብለን አንደኛ ሁለት የነበረውን የኦርቶዶከክስ ሲኖዶስ አንድ አደረግን። ሁለተኛ ሙስሊሙ ውስጥ የነበረውን ኩርፊያና ሌሎች ጥያቄዎችን መለስን። በተመሳሳይ ፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን በማወያየት ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ጥረት አድርገናል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ትርክት ከፋፋይ ስለነበር የሚያሳስብ ነገር ላይ ማተኮር ያስፈልጋል በሚል ሁሉንም የሚያስተሳስርና አንድ የሚያደርግ ብልፅግና ፓርቲ እንዲወለድ ተደርጓል። ሂደቱ ግን ቀላል አልነበረም።
የመደመር፣ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ጉዳይ በህፃናት ጭንቅላቶች ውስጥ ተቀርፀዋል። እነሱ ሲያድጉ ቋንቋቸው የሚሆነው መደመር፣ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ነው።
ዲሞክራሲ ላይ ቢሰራ፣ የሃይማኖት ተቋማት ቢገነቡ፣ ፓርቲዎች አንድ ቢደረጉ ነገሩን ባፋጣኝ መልክ ማስያዝ ስለማይቻል የህግ የበላይነት እንደሚያስፈልግና ለዚህ ደግሞ የህግ አስፈፃሚ አካላት ማለትም መከላከያ፣ የደህንነት ተቋማት እንዲጠናከሩ ተሞክሯል። መከላከያም ሆነ ደህንነት ተቋማት ኢትዮጵያዊ መስለው እንዲገነቡ ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያትም ከዚህ ቀደም የነበረውን ስህተት ላለመድገም ነው።
ተቋማት እንዴት እየተገነቡ እንደሆነ ሳናውቅና በውስጣቸው ሳናልፍ ግን እንዲሁ ስም ከሰጠን መልሰን የነበርንበት ጥፋት ውስጥ ከመግባት ውጪ ጥቅም የለውም። ሀገር እንድታድግ የሚፈልገው ሰው የተጀመረውን ሳያፈርስና ሳያበላሽ ከላዩ ላይ እየገነባ የሚሄድ መሆን አለበት።
ዲሞክራሲ፣ እምነት ተቋማት፣ ፓርቲዎችና የህግ የበላይነት ላይ ቢሰራም ቴክኖሎጂ ከሌለ ዋጋ ስለማይኖረው በእያንዳንዱ መስሪያ ቤት ቴክኖሎጂን ለማረጋገጥ ጥረት ተደርጓል። ቴክኖሎጂን በስርአቱ ውስጥ ለማካተትና ለወጣቱ የሚመጥን ተቋም ለመገንባት ተሞክሯል።
ኢኮኖሚን በሚመለከትም የንግድ ብድር ተኮር የነበረውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት አራት አመታት የንግድ ብድርን ለማቆም ወስናለች። እስካሁንም ምንም አልተበደረችም። በሌላ በኩል በየቦታው እያረሩ ያሉ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ስራዎች ተሰርተዋል። እነዚህም ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ የተደረገው የመንግስትን በጀት በአግባቡ በመጠቀምና ከአጋዥ ሰዎች ብር በመሰብሰብና በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ነው። እነዚህ ሶስት ነገሮች ሳይቋረጡ ባህል ቢሆኑ የሀገሪቱ እድገት ይፋጠናል።
ለውጥ የሚመጣው ደረጃ በደረጃ ነው። ለውጥ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም ጭምር ነው። ሆኖም ያንን ለውጥ ማባዛትና ባጠረ ጊዜ ውስጥ ሁሉም ጋር ማየት ያስፈልጋል። በጋራ ተቸግረንና ወስነን ካልሰራን እንዲሁ ለውጥ አይመጣም። በሀገራት ያየነውን ልምድ ወስደን፤ ከመልካም ልምዶቻቸውም ልምድ ቀስመን፤ ከትጋታቸውም ትጋት ወስደን አንድ ሆነን ብንሰራ ኢትዮጵያ የምትቀየር ሀገር መሆኗን ያመላክታል። ለዚህ ደግሞ የተዘጋውን ኢኮኖሚ መክፈት ያስፈልጋል።
እድገትን በሚመለከት ግን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሰፊ የወጣት ቁጥር ያላቸው ሀገራት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ወጣቱን አንቀሳቅሶ መስራት ከተቻለ እድገትን ማረጋገጥ ይቻላል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አጠቃላይ የመንግስት ተቋም ህጎችንና ፖሊሲዎችን ለማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከዚህ አኳያ ቀሪ ችግር የሆኑትን ሌብነትንና እለተኝነትን መዋጋት ያስፈልጋል።
በአረንጓዴ አሻራ 20 ቢሊዮን ታቅዶ 25 ቢሊዮን ችግኝ ተተከለ ሲባል እንደዋዛ የሚታይ አይደለም። በሁሉም ሴክተር ያቀድነውን በዚያ ልክ ማሳካት ከቻልን ስደት ይቀራል፤ ህልመኞችም ከነህልማቸው ጥግ ጥጋቸውን ይይዛሉ፤ ወጣቶች ሀገር ተረካቢዎች፣ የተሻለች ሀገር የተሻለ ምድር መረከብ ይችላሉ።
በሌላ በኩል ፕሮጀክት ላይ በተለይ ደግሞ በታላቁ የህዳሴ ግድብ በያዘው ውሃና በተፈጠሩ ሰባ ደሴቶች ላይ በቀጣይ ስራዎች ሲሰሩ ግደቡ ክልል ሳይሆን ሀገር ይሆናል። በተመሳሳይ በኮይሻ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ስኳር፣ መንገድና ትምህርት ላይ በጣም ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል።
እነዚህንና መሰል የተጀመሩና ስራቸው እየተጠናቀቁ ያሉ ፕሮጀክቶች ሙሉ ፍፃሜያቸውን እንዲያገኙ ከወጣቱና ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አስተዋፅኦ ይጠበቃል።
በቀጣይ ዓመት በሚጀመረው በእንቁላል፣ ወተት፣ ስጋ፣ ዶሮና ማር ላይ ስራዎች ይሰራሉ። ከዚህ አኳያ በአረንጓዴ አሻራ የመጣውን ድል በዚህ አዲስ አሻራም መድገም አለብን። ለዚህም በየቦታው እምቅ አቅም አለ። የተሰጠንን አውቆ መጠቀም ያስፈልጋል፤ ሰጪውንም ማመስገን ይገባል።
ወጣቶች የምትፈልጉት ነገር ላይ ማተኮር ሲገባችሁ የማትፈልጉት ነገር ላይ ጊዜያችሁን አታባክኑ። የማትፈልጉትን ነገር አእምሯችሁን አታስተምሩት። ለአብነት ድህነት ድህነት… አትበሉ ምክንያቱም አእምሯችሁ ቃሉን ይለማመደውና ጭንቅላታችሁ ደሃ ይሆናል። ደጋግመን ልማትና ብልፅግና ነው ማሰብ ያለብን።
‹‹እርዳታ ማለት የአይጥ ወጥመድ ላይ የሚቀመጥ ፍርፋሪ›› ማለት ነው። ስንዴ የሚረዱ ሀገራትም እንደፍርፋሪው ናቸው። ይህም በአባቶቻችን ንፁህ ደም የተከበረውን ነፃነት በስንዴ መሳይ ይሸጣል እንደማለት ነው። ይህንንም በፈጠነ ጊዜ ማድረግና ስንዴን ከራስ አልፎ ወደውጪ መላክ ያስፈልጋል። ለዚህም ወጣቶች ተዘጋጁ።
እነዚህን በአራት አመታት ውስጥ የተከናወኑ ስራዎችን ለማደናቀፍ የውጪ ጠላቶች በከፍተኛ ደረጃ መዋእለ ነዋያቸውን አፍስሰዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ባንዳዎችና ሸኔ ሀገሪቷን ለማፍረስና ስራዎችን ለማደናቀፍ ሰርተዋል። አለም አቀፍ ቀውስ በተለይ ደግሞ ኮቪድ-19ም የራሱን አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል። ሀገራዊ ፈተናዎች በተለይ ደግሞ አንበጣ፣ ጎርፍ፣ ኮንትሮባንድና ሀሰተኛ ወሬዎችና ጦርነቶች በአራት አመታት ውስጥ ከገጠሙ ፈተናዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።
ወጣቱ የቀደመ ታሪክ የሰማ ነው። ይህንንም ለውጥ ለማምጣት የታገለ ወጣት ነው። ይህ ወጣት በታሪክ አጋጣሚ የራሱ የሆነ ታሪክና ገድል ያለው ነው። ትናንትን የሰማና ነገን ለመስራት የሚነሳሳ ነው። ከዚህ አንፃር ወጣቶች ጊዜያችሁ አላቂ መሆኑን አውቃችሁ መጠቀም አለባችሁ።
ከውጪ ተፅእኖ አንፃር የኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ፣ ወታደራዊና የቴክኖሎጂ ተፅእኖ አለ። ከዚህ አንፃር በተለይ ቴክኖሎጂ ላይ ወጣቶች ቴክኖሎጂን የምትወዱና የምትፈጥሩ መሆን አለባችሁ። ዲፕሎማሲም በዚህ ይወሰናል።
ይህን የውጪ ተፅእኖ ለመቋቋም እያንዳንዱ ግለሰብ በሽታን ለመከላከል ኢሚዩኒቲውን ማሳደግ እንዳለበት ሁሉ ሀገርም እንደዛው ነው። ከሀገር የሚጠበቀው መከላከል የሚያስችል አቅም መገንባት ነው። ይህን በደም የተከበረ ሀገር በቴክኖሎጂና በእርዳታ ምክንያት እንዳይፈርስ መከላከል ነው። ይህን ማድረግ ከቻልን የምናስበውን እናሳካለን። በሰላምና በብልፅግና አሸናፊ መሆን አለብን።
ግጭትን በሚመለከት ሊበዛ የቻለው ነገሮች በብዛትና በቶሎ ማወቅ ነው። ተዋንያንና ሁሉ ተንታኝ መሆን መብዛትም ለግጭት መብዛት ምክንያት ነው። የሽማግሌ መጥፋትም ግጭቶችን አባብሷል።
ወጣትና የተማረ የሰው ኃይል እየበዛ በመሆኑ ስራ ላይ ሰፊ ስራ ያስፈልጋል። በነፃ ማገልገል በገበታ ለሀገርና በሌሎች ፕሮጀክቶች ሁሉ በርካታ ሰዎች በስራ ይሳተፋሉ። በበጀትም እንደዚሁ። የግል ሴክተሩንም እያጠናከርን ስራ ማስፋት አለበን። ከዚህ አኳያ ወጣቶች ስራ መናቅ ማቆም ይኖርባችኋል። በየአካባቢያችሁ ያለውን እድል ማየት አለባችሁ። በተናጥል ሳይሆን በጋራ መስራትን አስቡ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20 /2014