ሰላም ልጆች! እንዴት ሰነበታችሁ፤ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ጥሩ ነበር አይደል? መቼም አዎ እንዳላችሁኝ አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም ቀናችሁን ሁሉ ደስተኛ ሆናችሁ ከቤተሰባችሁ ጋር እያሳለፋችሁ እንደሆነ ስለምገምት ነው፡፡ በተለይ ይህ ወቅት ደግሞ ለልጆች ልዩ ወር እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ወር በርካታ ልጆችን የሚያስደስቱ ክንዋኔዎች የሚደረግበት ነው፡፡ አንዱ የቡሔ በዓል የሚከበርበት ጊዜ መሆኑ ሲሆን፤ በዓሉን ለማክበር የተለያዩ ዝግጅቶችን ስታደርጉ እንደሰነበታችሁ አምናለሁ፡፡
በቡሔ ጊዜ ጅራፍ ማጮህ የሚፈቀድበት እለት በመሆኑ አዲስ ጅራፍ መስራታችሁ አይቀርም፡፡ እናንተ ባትችሉበት እንኳን ሌሎች ልጆች እንዲሰሩላችሁ ታደርጋላችሁ፡ ፡ ይህ ደግሞ ልምድን መካፈል ጭምር ያስተምራችኋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቡሔ እለት በየሰው ቤት እየሄዳችሁ የምትጨፍሩበት በመሆኑ ልዩ ቀናችሁ ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህን ጊዜ ብዙ ነገር ታገኛላችሁ፡፡ አንዱ ስጦታችሁን መለየታችሁ ሲሆን፤ በጊዜው ለጭፈራው ቡድን ስትመሰርቱ እከሌ ይህንን አድርግ ትባባላላችሁ ትመዳደባላችሁ፡፡ እናም እናንተ የሚደርሳችሁ ሥራ ተሰጥኦአችሁ እንደሆነ ትረዳላችሁ፡፡ ለምሳሌ፡- ገንዘብ ያዥ ከሆናችሁ ታማኝ መሆናችሁን፤ መዝፈን ከሆነ ድርሻችሁ ደግሞ ድምጻዊ መሆናችሁን ታረጋግጣላችሁ፡፡ በተመሳሳይ ማስተባበር ላይ ከሆነ ምድባችሁ የአለቅነት ቦታ ይዋጣላችኋል ማለት ነው፡፡
ልጆች እዚህ ላይ ልብ ልትሉት የሚገባው አንድ ነገር አለ፡፡ ለምን ለእኔ ምንም ሥራ አልተሰጠኝም ማለት የለባችሁም፡፡ ምክንያቱም በቡድን ውስጥ ሁሉም አለቃ መሆን አይችልም፡፡ ሁሉም ገንዘብ ያዥና ሌላም ሌላም ሊሆን አይችልም፡፡ መሳተፍና ለሌሎች ድምቀት መሆንም አንዱ የሥራ ድርሻ ነው፡፡ ስለዚህም በዚያ ቡድን ውስጥ ምንም ኃላፊነት ያልተሰጠው ሰው ቦታው ስለማይበቃ እንጂ ምንም ተሰጥኦ ስለሌው እንዳልሆነ መረዳት አለባችሁ፡፡ በዚያ ላይ እናንተ ባትኖሩ ኖሮ ጭፈራው አይከናወንም፡ ፡ ምክንያቱም ማን ሊያጨበጭምና ሊያጅብ ይችላል? ስለሆነም ይህንን ኃላፊነት በማግኘታችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል፡፡
ሌላው በቡሔ ቀን ደስ የሚያሰኘው ነገር ብዙዎች ጋር በልጅ ልክ የሚመጣው የሙልሙል ዳቦ ጉዳይ ነው፡ ፡ ያው ቀደም ባለው ጊዜ ልጆች በየቤቱ ሲጨፍሩ ጭምር ሙልሙል ዳቦ ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ነገሮች ተገልብጠው ብር ካልሆነ አንቀበልም አሉ እንጂ፡፡ ነገር ግን በየቤቱ የቡሔ ተብሎ የሚሄደው ጥንትም ነበር፡፡ እናም ያንን እየገመጡ መጨፈር ልዩ ደስታን ከሚሰጠው መካከል ነው፡፡
ልጆች ሌላው የቡሔ ጥቅም ነጻነታችሁን የምታገኙበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ የዚያን ጊዜ አባቶች ይመርቋችኋል እንጂ አይቆጧችሁም፡፡ እንደውም በቡሔ ጨዋታ ምን እንደሚባል ታውቃላችሁ? ‹‹ በቡሔ ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› ነው፡፡ ስለሆነም ጨፍራችሁ ሳይሰጣችሁ ሲቀር በግጥማችሁ ስትሸነቁጧቸው የማይቆጧችሁ ለዚህ ነው፡፡
በቡሔ እለትና ከዚያ በኋላ ሰማይ ከጭጋግአማነት ወደ ብሩህነት ይለወጣል፡፡ የክረምቱ አፈና ተወግዶ የብርሃን ወገግታም ይመጣል፡፡ የዚህን ጊዜ ወንዙ ይጎላል፡፡ ዝናብም አይከብድም፡፡ እናም ለመጫወት ምቹ ጊዜ ይፈጥርላችኋልና እንደልባችሁ ችግር ሳገጥማችሁ ትቦርቃላችሁ፡፡ ስለዚህም ይህ የብራ ጊዜ የልጆች የነጻነት ወቅት እንደሆነም ይነገራል፡፡
ልጆች ለመሆኑ የቡሔን ትርጉም ታውቃላችሁ? ትንሽ ነገር ልበላችሁና ሃሳቤን ልቋጭ፡፡ እናንተ ደግሞ ትርጉሙን መሰረት በማድረግ የምታገኙትን ጥቅም እያሰባችሁ በዓሉን አክብሩ፡፡ ሌሎች ልጆችም በባህሉና በወጉ መሰረት እንዲያከብሩ ምክራችሁን ለግሱ፡፡ ምክንያቱም ባህሉን ባለማወቅ በጭፈራ ግጥሞቻቸው ጭምር እየተበላሹ ስለሆነ ማስተካከል አለባችሁ፡፡
የቡሔ በዓል መሠረቱ የክርስቲያን እምነት ተከታዮች ሲሆን፣ ደብረ ታቦር እየተባለም ይጠራል፡፡ በግዕዝ የታቦር ተራራ ማለት ነው፡፡ ደብረ ታቦር ወይንም የታቦር ተራራ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደፀሐይ የበራበት ልብሱም እንደብርሃን ነጭ የሆነበት ቦታ ነው፡፡ ይህ ቦታ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነውም ይባላል። በአገራችን ደግሞ ሁሉም እንዲያከብረው ተደርጎ በባህል ጭምር የታሰረ በዓል ነው፡ ፡ ምክንያቱም ይህ በዓል የክረምቱ አፈና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት ጊዜን የሚነግረን ነው፡፡
ቡሄ ማለት ከትርጉሙ ብንነሳ ገላጣ፣ ብራ ማለት ነው፡፡ እንደውም በጨዋታው ሳይቀር እንለዋለን፡፡ ‹‹ ቡሔ መጣ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ›› ይህ ማለት ደግሞ በሚገላለጥበት ጊዜ አቧራ እንዳይጠጣ ለምለሙን አልብሱት እንደማለት እንደሆነም ይነገራል፡፡ ልጆች ይህ በዓል ከላይ እንዳልኳችሁ በገጠር አካባቢ በስፋት ይከበራል፡፡ በየከተማም ቢሆን ይከበራል፡፡ ነገር ግን ከገጠሩ አንዳንድ ነገሮች ይለያያሉ፡፡
አንዱ እንደገጠር ልጆች ጅራፍ አለመግመዳቸው ሲሆን፤ በዚያ ፋንታ ርቺት ማጮሃቸው ነው፡፡ በየቤቱ እየሄዱ ሲጨፍሩ ግጥሞቻቸውም ቢሆኑ ባህሉን የጠበቁ አይደሉም፡፡ በዚህ ወቅት እናቶች ሳይቀሩ ለበዓሉ ልዩ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ምክንያቱም «ቡሔ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ መስጠት ግድ ነው፡፡ በከተማ አካባቢ ግን ይህ አይፈጸምም፡፡ ምክንያቱም ልጆች ሲጨፍሩ የሚፈልጉት ብር እንጂ ዳቦ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ ገጠሩ ልጅ በአንድነት ተሰባስበው ችቦ እያበሩ ይጨፍራሉ፡፡ አያችሁ ልጆች የገጠርና የከተማ የቡሔ አከባበር ልዩነቶችን የሚያስተናግድ ነው፡፡ እናም እናንተ ማወቅ ያለባችሁ ባህሉን አለመልቀቁን ነው፡፡ ከባህሉ ውጪ የሚያደርጉ ልጆችን መምከር አለባችሁ፡፡ ከላይ አደራ ያልኳችሁም ለዚህ ነው፡፡ በሉ ለዛሬ በዚህ እንሰነባበት በቀጣይ ሳምንት ሌላ ጉዳይ ይዤላችሁ እንደምቀርብ ቃል በመግባት መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ ተመኘሁ፡፡ ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15 /2014