የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ማክሰኞ ዕለት ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሸፋን አግኝቷል፡፡
ዋና ቢሮውን በኳታር ዶሃ ያደረገው አልጀዚራ ስለውይይቱ ባስነበበው ዘገባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርሳቸው በሊቀመንበርነት በሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ ስር ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ጋር እንደተወያዩ ዘግቧል፡፡ በ2012 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በሚያስችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከ81 የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮችና ተወካዮች ጋር ውይይት መደረጉን ጣቢያው በዘገባው አመልክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ) ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ስልጣን ላይ እንዳለና ከአጋር ፓርቲዎች ጋር በመሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን ጣቢያው ጠቁሟል፡፡
ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ወዲህ እየወሰዷቸው ያሉትን ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የለውጥ ዕርምጃዎች ያስታወሰው ጣቢያው፣ ከምርጫ 1997 በኋላ በተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ለእስር ተዳርገው የነበሩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸው የዕርምጃ አካል እንደሆነ በዘገባው አስፍሯል፡፡
የናይጀሪያው የድረ-ገፅ ጋዜጣ ‹‹ሱንዲያታ ፖስት (Sundiata Post)››፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርቲዎቹ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት የፖለቲካ ምኅዳሩን የበለጠ ለማስፋት ፓርቲያቸው ጥረት እንደሚያደርግ ቃል ስለመግባታቸው ጽፏል፡፡ ውይይቱ በ2012 የሚካሄደው ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን በሚያስችሉ የለውጥ ዕርምጃዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጋዜጣው ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ወዲህ እየወሰዷቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ዕርምጃዎችን ጠቅሷል፡፡
አንጋፋው የዜና ተቋም ‹‹ሮይተርስ (Reuters)›› በበኩሉ፣ የምርጫ ስርዓቱን በማሻሻል ምርጫው ታማኝ እንዲሆን የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ዘግቧል፡፡ የዜና ተቋሙ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን የለውጥ ዕርምጃዎች ጠቅሶ፣ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸው የዕርምጃው አካል እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ትኩረቱን በጋና ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ አድርጎ የሚሠራው ‹‹ጋናያን ኒውስ (Ghanaian News)›› የተባለ ድረ-ገፅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2012 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ እንደሚሆን ቃል ስለመግባታቸው ጽፏል፡፡ እንደ ድረ-ገፁ ዘገባ፣ ውይይቱ ቀጣዩን ምርጫ አስመልክቶ በመጪዎቹ ጊዜያት ለሚደረጉ ድርድሮች መሰረት የተጣለበት መድረክ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ድረ-ገፁ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ ዕርምጃዎችን በዘገባው ጠቅሷል፡፡
‹‹ሲ.ጂ.ቲ.ኤን (CGTN)›› የምርጫ ስርዓቱን ለማሻሻል ውይይት መደረጉን በጠቀሰበት ዘገባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት ስለመናገራቸውም ዘግቧል፡፡
‹‹አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP)›› ደግሞ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከያዙ ወዲህ እየወሰዷቸው የሚገኙት ፈጣን የለውጥ ዕርምጃዎች አካል ነው›› ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት እርሳቸው በሚመሩት ፓርቲ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ያለበትን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት ቃል ገብተዋል›› ብሎ የዘገበው ደግሞ ‹‹ቮይስ ኦፍ ፒፕል ቱዴይ» (Voice of People Today) የተባለው መገናኛ ብዙኃን ነው፡፡
አንተነህ ቸሬ