ማንበብ ለአንድ አገር ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ የማያውቅ አለ ብዬ አላስብም። ትውልድ ከሚገነባባቸው መልካም እሴቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ጠንካራ የንባብ ባህል ነው። የእያንዳንዳችን ነገ ለመጽሐፍ በሰጠነው ክብርና ዋጋ ልክ ይመዘናል። ከትላንት እስከዛሬ ስለመጽሐፍና ንባብ ብዙ ተብሏል። ዓለም በሚያነቡ ሰዎች እንደተለወጠችም የምናውቅም ብዙዎች ነን። ታዲያ ለምንድነው የማናነበው? ለብዙ ነገር ጊዜ ሲኖረን እንዴት ለማንበብ የሚሆን ጊዜ አጣን? ይሄን ጥያቄ ሁላችንም እንድንመልሰው የሚገባ ነው።
አሁን ላይ ብዙዎቻችን ከእውቀት ሽሽት ላይ ነን። ለሕይወታችን ብሎም ለወጣትነታችን እሴት የሚጨምሩልን መልካም ነገሮች እያሉ በሚጎዱን ነገሮች ላይ የተጠመድን ነን። በሕይወት ውስጥ አብዛኞቹ አደጋዎች ከእውቀት ማነስ የሚመጡ ናቸው። በዛው ልክ በቁጥጥራችን ስር ያደረግናቸው ችግሮቻችን ሁሉ በእውቀታችን ታግለን የጣልናቸውም ናቸው።
እኔን ጨምሮ አብዛኞቻችን ለብዙ ነገር ጊዜ ሲኖረን ለመልካም ነገር ግን ጊዜና ቦታ የሚጠበን ነን። ዛሬ ላይ በብዙ ነገር ጎለን የምንገኘው የሚጠቅመን እያለ በማይጠቅመን ላይ ስለምንለፋ ነው። እስኪ ስልጣኔ ለእናንተ ምንድነው? የአገርና የማህበረሰብ እድገትና ስልጣኔ በምን የሚለካ ይመስላችኋል?
የእናንተን መልስ በውስጣችሁ ያዙትና ዓለም የተስማማበትን እናውራ፦ ስልጣኔ የእውቀት የመጨረሻው ጥግ ነው። ስልጣኔ እውቀትን መሰረት ያደረገ የድንቅ አስተሳሰብና የድንቅ ተግባር ውጤት ነው። ስልጣኔ በእውቀት በሚመሩ፣ እውቀትን በሚናፍቁ፣ ለእውቀት በሚተጉ ማህበረሰብ የሚፈጠር የመልካም እሳቤ ነጸብራቅ ነው። ስልጣኔ በእውቀት የተጉ የንቁ ማህበረሰቦች አሻራ ነው።
ከጥንት እስከዛሬ ዓለም ሰንኮፏን ጥላ ዛሬ ላይ ተውባ የቆመችው በእውቀት ተመርታ ነው። በሌላ አገላለጽ የትኛውም ስልጣኔ እውቀትን መሰረት ያደረገ ነው። ራሳችንን የምንፈልግበት ፈልገንም የምናገኝበት አንድ ጥበብ እውቀት ነው። ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን መልካም የምንሆንበት ቅዱስ ስፍራችን ነው።
አገርና ማህበረሰብ የግለሰቦች ጥርቅም እንደመሆኑ መጠን የአገርና ህዝብ ስልጣኔ ከግለሰብ ስልጣኔ የሚጀምር ነው። ግለሰብ ሳይሰለጥን የሚሰለጥን አገርና ህዝብ የለም። እኔና እናንተ ለእውቀትና ለስልጣኔ ባለን ጉጉት ልክ የአገራችን እድገትና ስልጣኔ ይለካል። አገር ስትሰለጥን እኛ የምንሰለጥን የሚመስለን አለን ይሄ አመለካከት መስተካከል አለበት። የአገር ስልጣኔ ከግለሰብ ስልጣኔ የሚነሳ ነው። የትውልድ ስልጣኔ ከማህበረሰብ ስልጣኔ የሚቀዳ ነው።
እኛ ሰለጠንን ማለት አገራችን ሰለጠነች ማለት ነው። ይሄን እውነት በመሳት የምንማረው ለራሳችን ብቻ የሚመስለን ብዙዎች ነን። በዋናነት እኛ እንጠቀም እንጂ እያንዳንዱ በጎም ሆነ መጥፎ አሻራችን አገርና ህዝብ ላይ የሚያርፍ ነው። ዛሬ ላይ የእያንዳንዳችን እንቢተኝነት አገራችንን እየጎዳት ነው። ዛሬ ላይ እውቀት ያለመሻት ችግር አገራችንንም ሆነ ህዝባችንን ኋላ አስቀርቷል። በየትኛውም እውቀትና መመዘኛ ቢታይ የምንፈልገው ነገር ሁሉ በእውቀታችን ውስጥ የሚገኝ ነው። እውቀት ከተለያዩ ቦታዎች ሊገኝ ይችላል። ቤተሰብ፣ አካባቢ፣ ጓደኛ፣ ትምህርት ቤት እውቀት የምናገኝባቸው ቦታዎች ናቸው። በጥረትና በተፈጥሮም የምናገኘው እውቀቶች አሉ። ከዚህ በተጨማሪም በእያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴያችን ከምናየው፣ ከምንሰማው፣ ከደረሰብን አጋጣሚ የምንማራቸው ብዙ እውቀቶች አሉ።
ዓለም ራሷ ትምህርት ቤት ናት። ተፈጥሮ ራሱ መምህር ነው። ራሳችንን ለመማር ካዘጋጀን እውቀት የትም አለ። የእውቀት ምንጭ ናቸው ተብለው በብዙዎች ዘንድ ከታመነባቸው ውስጥ አንዱና ዋነኛው ግን ማንበብ ነው። ብዙዎቻችን ማንበብ ትልቅ ሰው ያደርጋል፣ አንባቢዎች መሪዎቻችን ናቸው እየተባልን ያደግን ቢሆንም ጆሮ ዳባ ብለን ከንባብ ተኳርፈን የምንኖር ነን። አብዛኞቻችን እያወቅን የምንሳሳት ነን። አብዛኞቻችን ለመቃም ለማጨስ፣ አልባሌ ነገሮችን ለማድረግ ጊዜ ሲኖረን የእውቀት ሁሉ መሰረት የሆነውን መጽሐፍ ለማንበብ ግን ጊዜ የምናጣ ነን።
የሚጠቅመን ነገር እያለ፣ ሕይወታችንን የሚቀይር መልካም ነገር እያለ ለማይጠቅመንና በሚጎዳን ነገር ላይ የተጠመድን ነን። ሰው እንዴት እያወቀ ይሳሳታል? የምንፈልገው ማንኛውም ነገር እውቀታችን ውስጥ ያለ ነው። ሳናነብና ራሳችንን ለእውቀት ሳናዘጋጅ የምንለውጠው አንዳች ነገር የለም። እውቀት እኮ ሕይወትን ቀላል ማድረግ ነው። እውቀት እኮ ለችግሮቻችን መፍትሄ የምንሰጥበት ነው። እውቀት እኮ ነገን የተሻለ ማድረግ ነው። ማንበብ እኮ ራስን ማሳደግ፣ አእምሮን ማበልጸግ ነው። ይሄ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ የሚኖረን መልካም ነገር የለም።
ዓለምን የለወጧት የትላንትናዎቹ ጠበብቶች አንባቢዎች ነበሩ። የዛሬዎቹ የእኔና የእናንተ ትውልድም የዓለምን አዳፋ መልክ በንባባቸው የቀየሩ ናቸው። ፍላጎታችን ምንም ይሁን እውቀት ያስፈልገናል። እውቀት ሀሳባችንን የምናክምበት፣ አእምሯችንን የምናንጽበት ፍቱን መድኃኒታችን ነው። ውስጣችን ያለው ጽኑ ፍላጎት ይቀጣጠል ዘንድ እውቀት ግድ ይለናል። ካለእውቀት የምንሄድበት ጎዳና በእንቅፋት የተሞላ ነው።
አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ለመገንባት ያለጥርጥር እውቀትና ከዚህ የሚመነጭ መልካም አስተሳሰብ ያስፈልገናል። እውቀትና መልካም አስተሳሰብ የሚገኘው ደግሞ ከማንበብና ራስን ለእውቀት ዝግጁ በማድረግ ነው። ዛሬ ላይ ብዙ ነገሮች እየተበላሹብንና እየፈረሱብን ያሉት ካለ እውቀት በዘልማድ ስለምናደርጋቸው ነው። ካለ እውቀት የሚሳካ ግለሰባዊም ሆነ አገራዊ ህልም የለንም።
ይሄን እውነት በመረዳት ራሳችንን በእውቀት እንክበብ። እናብብ። ማንበብ ብቻ አይደለም ባህላችንም እናድርገው። በመቃምና በማጨስ ከመክሰር ባለፈ የምናተርፈው ትርፍ የለም። በመስከርና በየምሽት ቤቱ በመዞር ህልማችን ይጨልማል እንጂ አይሳካም። አሁን ላይ በብዙ ነገራቸው ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን በእውቀት የከበቡ ናቸው። ዓለምን በቢሊየነርነት የሚመሯት የምድራችን ባለጸጋዎች ሁሉም አንባቢዎች ናቸው።
ሁሉም ባለጸጋና ስኬታማ ሰዎች ራሳቸውን ለማሳደግ በወር ሁለትና ከዚያ በላይ መጽሐፍት የሚያነቡ ናቸው። ለምሳሌ በሀብት መጠኑ ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፈው ሽማግሌው ዋሬት ቡፌት የእድሜውን ሰማኒያ ፐርሰንት ያህሉን ያሳለፈው በማንበብ ነበር። በጣም የሚገርመው ደግሞ የመጨረሻው የስኬት ጥግ ላይ ደርሶ ዛሬም ድረስ ማንበቡ ነበር።
‹ሀብታም እንደምሆን ቀድሜ አውቅ ነበር፣ መቼም ቢሆን ለደቂቃ እንኳን ስኬታማ እንደምሆን ተጠራጥሬ አላውቅም የሚለው ሽማግሌው ቡፌት መጽሐፍ ማንበቤ የዛሬውን በሁሉ ነገሩ የተሳካለትን እኔን ፈጠሮኛል ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።
የብልጌትና የቱጃሩን ቤዞስ እንዲሁም የምድራችንን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የአለን መስክን ጀርባ ብታጠኑ የስኬታቸው ምስጢር ማንበብ እንደሆነ ትደርሱበታላችሁ። ዓለም ላይ የሁሉም ስኬታማ ሰዎች የስኬት መነሻ እውቀት ነው። ንባብ ነው። ለሚጠቅማቸው ነገር መለፋታቸው ነው። አብዛኞቹ ስኬታማ ሰዎች ከማንበብ ጋር የተያያዘ ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ናቸው። ስኬታማ ሆኖ እውቀት የሌለውና ማንበብን ባህል ያላደረገ ግለሰብ አይገኝም።
አለማንበብ ከስልጣኔ መራቅ ነው። ህልምንና ራዕይን ማጨንገፍ ነው። ይሄ ደግሞ የመጨረሻው የሰውነት ዝቅጠት ነው። አለማንበብ ድንቁርናን መምረጥ ነው። የድንቁርና መነሻውም መድረሻውም ደግሞ ድህነት ነው። የድህነትን ያክል አስከፊ ገመና ደግሞ ዓለም የላትም። በእውቀታችን ልናሸንፋቸው እየተገባን ግን ደግሞ ባለማወቅ ተላምደናቸው እየጎዱን ያሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ከነጉድፋቸው በጉያችን ውስጥ የታቀፍናቸው፣ ከመጸየፍ አልፈን ያከበርናቸው፣ ከመናቅም እውቅና የሰጠናቸው ብዙ ነውሮች አሉብን።
የማንም ያልሆኑ የእኛ የኢትዮጵያዊያን ብቻ የሆኑ እልፍ ጉድፎች ሰለባዎች ነን። ይሄ ጉድፋችን የሚስተካከለው በእውቀት ነው። የሚጠራው አንባቢ ትውልድ ስንፈጥር ነው። ይሄ ሁሉ መደነቃቀፋችን እልባት የሚያገኘው በእኔና በእናንተ ምክንያታዊ እሳቤ ነው።
በየሰፈሩ ግሮሰሪና መቃሚያ ቤት፤ ጭፈራ ቤት እና ማሳጅ ቤት ስንሰራ ለአንድ ላይብረሪ ሲሆን ቦታ የምናጣ ነን። በክልልና በዋና ከተሞች ትላልቅ ፎቆችን ስንገነባ ለህዝብ ላይብረሪ ሲሆን አቅም የማይኖረን ነን። በየቤታችን መደርደሪያ ላይ ብዙ አይነት ውስኪና ሻፓኝ ስናስቀምጥ አንድ መጽሐፍ ግን የለም።
የንባብ ባህል ባልተፈጠረበት የተሻለ ትውልድ ለመፍጠርም ሆነ አገር ለመገንባት የምንሮጠው ሩጫ ፍሪያማነቱ በጥያቄዎች የሚታጀብ ነው። ከሁሉ በፊት እውቀት ያለው ምክንያታዊ ትውልድ መፍጠር አለብን። በእኛና ባደጉት አገራት መካከል የተፈጠረው የኢኮኖሚና የስልጣኔ ልዩነት በእውቀት እንጂ በሌላ በምንም የመጣ አይደለም።
አሜሪካዊያን ቅድሚያ ለአሜሪካ ሲሉ እኛ ቅድሚያ ለእኔ የምንል ነን። ቻይናዎች ቅድሚያ ለቻይና ሲሉ እኛ ቅድሚያ ለእኔ የምንል ነን። በእኔነትና በእኛነት መካከል መጨረሻ የሌለው ልዩነት አለው። እውቀት ሁሌም አገርን የሚያስቀድም ነው። እውቀት ሁሌም ለህዝብ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው። ለኔ ስንልና ለአገር ስንል ሴይጣናዊና መላዕካዊ ልዩነት አለው።
እኔነት ሁሌም አውዳሚ ነው። እኔነት ሁሌም አጥፊ ነው። እውቀት ይሄን ጽንፍ የረገጠ አስተሳሰብ የሚያስተካክል ነው። እውቀት በእኚህ ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች መካከል የቆመ የዳኝነት መስመር ነው። ከአገርና ከህዝብ ልቆ ራሱን ያስቀደመ እውቀት የለም። እውቀት ሁሌም አገርና ህዝብን መሰረት ያደረገ ነው።
በእውቀታችን ድህነታችንን ማሸነፍ አለብን። በእውቀታችን አገርና ህዝብን አስቀምጠን ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት እኔ የምንለውን ራስ ተኮር እሳቤ ማከም አለብን። ባለማንበብ ያጣናቸውን፣ በእውቀት ማነስ ያሸሸናቸውን ጸዳሎቻችንን መመለስ አለብን። ከግሮሰሪ ይልቅ ላይብረሪ በመክፈት፣ ቤታችን መደርደሪያ ላይ ውስኪ ሳይሆን መጽሐፍ በማስቀመጥ፣ ለልጆቻችን ሽጉጥ ሳይሆን የተረት መጽሐፍ በመግዛት አጉል ልማዳችንን ማስተካከል እንችላለን።
እናብብ.. ለውጥ ያለው በማንበብ ውስጥ ነው። ስልጣኔ ፎቅና መንገድ መገንባት አይደለም። ስልጣኔ ስማርት ስልክና በስማርት ጫማና ልብስ መዘነጥ አይደለም። ስልጣኔ በእስማርት አስተሳሰብ መዘነጥ ነው። ስልጣኔ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው። ስልጣኔ በእውቀት የዳበረ ሚዛናዊ እይታ ነው። ለዚህ ደግሞ ማንበብና የማንበብን ባህል ማዳበር ወሳኝ ነው።
ያለማንበብ ልክፍት፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን ያለመሻት፣ እውነትን ያለመፈለግ ታማሚነት ነው። ሕይወትን በመረዳት በእውቀትና በምክንያት ከመኖር ይልቅ እንዳው ዝም ብሎ መሽቶ የሚነጋልን ብዙዎች ነን። ለውጥና ልቀትን፣ ከፍታና ምጥቀትን እንዲሁም ክብርን በማይጨምሩልን ነገሮች ተከበን የምንኖር እንዲህም ነን። በሕይወታችን ያላፈራነው፣ በቅለን ፍሬ አልባ ዛፍ የሆነው ለዛ ነው።
አድገንና ጎልምሰን ከነህልማችን የተቀበርንው ለዛ ነው። እጆቻችን ለልማት፣ አእምሯችን ለለውጥ የሰነፈው በአጉል አመለካከት ነው። በምኞት ብቻ፣ በአምሮት ብቻ የቆምንው በዚህ ነው። ለምንም ነገር እውቀት ያስፈልገናል። ትውልድ እየገደልን የምንፈጥረው ሌላ ትውልድ የለም። ግሮሰሪና ጭፈራ ቤት እየገነባን የምናበቅለው ምርጥ ዘር የለም። ትውልድ የሚፈጠረው በእውቀት ብቻ ነው። ስለዚህም እናብብ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014