አዲስአበባ፤ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የዜጎችን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ማስከበር የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር መሆኑ እየተዘነጋ ነው ሲል አስታወቀ። በሀገሪቷ የህግ የበላይነት እንዲያስከብርም ፓርቲው ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ትናንት በቢሮአቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በኢትዮጵያ የዜጎች መፈናቀል ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት አስከትሏል። በአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ እየተነሳ ያለው ጥያቄ ህገ መንግሥታዊ አለመሆኑን፣ በዕጣ የቤት ባለቤት የሆኑ ዘጌች መብታቸው አለመከበሩና ከኃይማኖት ጋር በተያያዘም ፅንፈኛ ኃይሎች መኖራቸው የሀገሪቷን የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ እያስገባው መሆኑን አስታውቀዋል።
መንግሥት የዜጎችን መሰረታዊ ሰብአዊ መብት የማስከበር ተግባሩን እየዘነጋ መሆኑንም ጠቁመዋል። ፕሮፌሰር በየነ መንግሥት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያቸው መመለስ ሲገባው በብሄራቸው፣ በጎሳቸው፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ሙሉ ለሙሉ እንግዳ በሆኑ አካባቢዎች ለማስፈር መሞከሩ አግባብ እንዳልሆነና መቆም እንዳለበትም ገልጸዋል። ከየቦታው ለተፈናቀሉ የከተማ ነዋሪዎችና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች መንግሥት የመኖሪያ ቤት ማዘጋጀት እንዳለበትም አመልክተዋል።
ከህግ አግባብ ውጭ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮችም ተመጣጣኝ የካሳ ክፍያ መፈጸም አለበት ብለው በኮዬፈጬ በተገነባው የጋራ መኖሪያ ቤት ጋር ተያይዞ የተነሳው ጉዳይም መንግሥት ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል። ከኃይማኖት ጋር በተያያዘም ፅንፈኛ ኃይሎች በሀላባዞን አብያተክርስቲያናትን፣በወሎና ጎንደር ደግሞ መስኪዶችን በማቃጠል፣ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ አደጋ እየደረሰ መሆኑን አመልክተዋል። በሀገሪቷ የህግ የበላይነት እውን የሚሆንበትን መንግሥት ባለበሌለ አቅሙ ተግባራዊ ማድረግ አለበት ያሉት ፕሮፌሰር በየነ ሁሉም ለህገመንግሥቱ ተገዥ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011
ለምለም መንግሥቱ