አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ መንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ግዥ መፈጸሙን አስታወቀ። ከመንግስት መስሪያ ቤቶች የተወገዱ ንብረቶችን በጨረታ በመሸጥ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 79 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ገቢ አግኝቻለሁ ብሏል። የኤጀንሲው ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ ደፋሊ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት ኤጀንሲው በስድስት ወራት ውስጥ የፈፀመው ግዥ በስትራቴጂና ማዕቀፍ ስምምነት የተፈፀመ ነው። ይህም የዕቅዱን 80 ነጥብ ስምንት በመቶ ማሳካቱን አስታውቀዋል።
ኤጀንሲው ከፈጸማቸው ግዥዎች አብላጫ ውን ወጪ የወሰደው የስትራቴጂ ግዥው እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ለግዥ ከዋለው ብር ውስጥ 355 ሺ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በሁለት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊየን ብር ተገዝቷል ብለዋል። በቀሪው 800 ሚሊየን ብር የግንባታ ግዥዎች እንደተከናወኑ ጠቁመዋል። በመጪዎቹ ስድስት ወራትም የማዕቀፍ ስም ምነትን በተመለከተ ለመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚውሉ አላቂና ቋሚ እቃዎችንና መገልገያዎችን የመግዛት እንቅስቃሴ እየተደረገ እንዳለ ገልፀው የመንግስት ተቋማቱ ጨረታውን ካሸነፉ ድርጅቶች እቃዎችን እንደሚረከቡ አመልክተዋል።
በዘንድሮው ዓመት የማዕቀፍ ግዥው መዘግ የቱን የተናገሩት አቶ መልካሙ ለዚህም ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮችን አንስተዋል። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲገዛላቸው የሚፈልጉትን የዕቃ ዝርዝር በወቅቱ ያለማሳወቃቸው፣ በኤጀንሲው ተቋቁሞ የነበረው የቴክኒክ ግምገማ ቡድን መፍ ረሱ እና የጥራትና የተስማሚነት ደረጃቸውን ለማረጋገጥ የሚደረገው ፍተሻ የሚወስደው ጊዜ እና ሌሎችም በምክንያትነት አስቀምጠዋል።
ተቋሙ ከተረከባቸው ኃላፊነቶች ውስጥ በመንግሰት መስሪያ ቤቶች እንዲወገዱ ውሳኔ የተላ ለፈባቸውን የመንግሥት መሥሪያ ቤት ንብረቶች በጨረታ መሸጥ ሲሆን በመሆኑም በስድስት ወራት ውስጥ 79 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱን አቶ መልካሙ አስታውቀዋል። ኤጀንሲው ከመንግስት ተቋማት በተለያየ ምክንያቶች የሚወገዱትን ንብ ረቶች በተመጣጠነ ዋጋ በመሸጥ እንዲወገዱ ማድረግ ችሏል ብለዋል።
በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 184/2002 ከተቋቋመ ጀምሮ እስከያዝነው ግማሽ ዓመት ድረስ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ግዥዎችን የፈጸመ ሲሆን የተወገዱ ንብረቶችን በመሸጥም ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ አድርጓል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011
ኢያሱ መሰለ