በተለያዩ ምክንያቶች መነሻነት ክልሎቹ ከተቀመጠላቸው መብት በማለፍ በየፊናቸው የሚሰጡት መግለጫ ሆነ የሚያከናውኑት ተግባር አንድ ሀገር ውስጥ ያሉ አያስመስላቸውም። ይህ ሁኔታ ከሕገ መንግስቱና ከዘላቂ የፌደራል ስርዓት ግንባታው አንፃር ወዴት ይወስደናል?
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ረዳት ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ተክለኃይማኖት ወርቁ እንደሚገልፁት ክልሎች አንዱ ሌላውን የሚያስፈራራ መግለጫ የመስጠታቸው አካሄድ ህገመንግሥታዊ ስርዓቱን ይፃረራል። ምክንያቱም፤ በክልሎች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ጣልቃ ገብቶ ችግሩን የመፍታት ስልጣንም ሆነ ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥት ነው።
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ስልጣን አወቃቀር በፌዴራልና በክልሎች መካከል የተከፋፈለ ነው። የፌዴራል መንግሥትም የተዋቀረው በክልሎች አማካኝነት ነው። ህገመንግሥቱን የሚጻረር ማንኛውም የክልል ተግባር ኢ- ህገ መንግሥታዊ ነው። በመሆኑም እየተሰጡ ያሉት መግለጫዎች ከግል ፍላጎት የመነጩ ተደርገው ይወሰዳሉ።›› ብለዋል አቶ ተክለኃይማኖት።
‹‹መሬት የእኔ ነው›› የሚሉ መግለጫዎችም ህገመንግሥታዊ አይደሉም የሚሉት ረዳት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በኢትዮጵያ ደረጃ መሬት የእገሌ ነው ተብሎ አልተሠጠም። በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 ላይ በግልጽ የሰፈረውም ይሄው ነው፤ ለአስተዳደር መዋቅር እንዲመች የፌዴራል መንግሥት በመመሪያና በደንብ ኃላፊነትን አሳልፎ ካልሰጠ በስተቀር የተፈጥሮ ሀብትና ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የማስተዳደር ስልጣን ጭምር የፌዴራል መንግሥት ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ፌዴራል መንግሥት ክልሎች ላይ ግንባታ ማከናወን የመቻል ስልጣን ተችሮታል ሲሉም አፅንኦት ይሰጣሉ።
የፌዴራል መንግሥት የሀገሪቱን የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ አውጥቶ የመተግበር ያልተገደበ ስልጣን አለው፤ ይሄን ስልጣኑን ክልሎች የሚገድቡ ከሆነ ኢ-ህገመንግሥታዊ ነው፤ ክልሎችም የፌዴራል መንግሥቱን ፖሊሲና ስትራቴጂ መሰረት አድርገው መተግበር ይጠበቅባቸዋል እንጂ ማፈንገጥ እንደማይችሉ አመልክተዋል። ይህ ካልሆነ የክልል መንግስታት ከዚህ ውጭ ለመንቀሳቀስ ህገመንግሥት እስከመቀየር መዝለቅ ይጠበቅባቸዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዘርፍ ግጭትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘላቂ መፍትሄ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ንጋቱ አብዲ ተመሳሳይ ሀሳብ ያነሳሉ፤ የህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ህገ መንግሥቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው። የፌዴራል መንግሥትና የክልል አስተዳደሮች በህገመንግሥቱ የተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት አለ። ይህንኑ መሰረት አድርገው ህገመንግሥቱን ሳይጋፉ እንደየ አካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታና የሀገራቸውን ደህንነትና ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ መግለጫው ትኩረት ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።
‹‹በድንበር፣በግጦሽና በተለያዩ ምክንያቶች ሲፈጠሩ የነበሩ ግጭቶች በሳይንሳዊ መንገድ ሲፈቱ ቆይተዋል። እነዚህ ምክንያቶች ዛሬ የማንነትና የብሄር መልክ መያዛቸው በክልል እና በፌደራል መንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ከማበላሸት ባለፈ አሳሳቢ አድርጎታል፤›› ሲሉ አቶ ንጋቱ ገልፀዋል።
የአቶ ንጋቱን ሀሳብ የሚጋሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ግንኑነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ገብሩ ገብረሥላሴ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የማንነት፣ የመሬትና ሌሎች ጥያቄዎች የሚፈቱበት ሥርኣትም ሕገ መንግስታዊ ሆኖ ተቀምጧል። በመሆኑም ክልሎቹ የሚሰጡት መግለጫም ሆነ ሌሎች ተግባራት ሕገ መንግስቱን መሰረት ሊያደርግ ይገባል። በክልሎች እየተሰጠ ያለው መግለጫ የፌዴራል ሥርዓቱንና ህገመንግሥቱን እያጋጠሙት ካሉ ችግሮች አንዱ ማሳያ ነው ብለው የፌደራል ስርዓቱ በውድድር ሳይሆን በጋራ የሚገነባ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም ባይ ናቸው፤ አቶ ገብሩ።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት አጠቃ ላይ የፌዴራል ሥርአቱ ባጋጠመው ችግር ዙሪያ በጥናት የተደገፈ ውይይት በማካሄድ ችግሮችን የመፍታት ሥራ እየተሰራ ነው የሚሉት አቶ ገብሩ በቅርቡ በመቀሌ ከተማ የተደረገውን ውይይት ለአብነት በመጥቀስ ሁሉም የየራሱን ድርሻ እንዲወስድ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል።
የክልል አስተዳደሮች ስልጣናቸውን አልፈው ወደ ፌዴራል ስልጣን መጋፋት የመድረሳቸው ጉዳይ ምክንያታቸው ብዙ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ጥናት ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ሙሉዓለም ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት በለውጥ ደጋፊዎችና ተቀዋሚዎች መካከል ያለ የሀሳብ ልዩነት መኖር፤ በሀገሪቷ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ቁጥራቸው መብዛትና ፓርቲዎቹም ደጋፊ ለማግኘት የሚሄዱበት አካሄድ ህዝብ ላይ ጫና መፍጠር፤ እና የክልል መስተዳድሮችም አቅማቸውን እያጎለበቱ መምጣትን ይጠቀሳሉ።
የሀገሪቷ ርዕዮተዓለም አቅጣጫ ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ፣ የሊበራል እና ሶሻል የሚባሉ መጓተቶች ስጋትም ጥሩም የሚመስሉ ነገሮች እንዲፈጠሩ እንዳደረጉ ይጠቅሳሉ። ሀገሪቷ ዴሞክራሲ መለማመድ ላይ መሆኗም የራሱ ተጽዕኖ እንዳለው የሚገልጹት አቶ መላኩ መገናኛ ብዙሃን ኃላፊነት ሳይሰማቸው መረጃዎችን በነፃነት የሚያስተላልፉበት ባህል መፈጠሩም ሌላው ተደማሪ ምክንያት ነው ሲሉ ያስቀምጣሉ።
ክልሎቹ የሚያከናውኑት ተግባር ፖለቲካዊ አንድምታ አለው ሲሉ የሚከራከሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ የክልል አስተዳደሮች እየሰጡ ያለው መግለጫ በለውጥ ውስጥ ባለ ሀገር የሚጠበቅ ነው።
ጉዳቱ ሳይናበቡ ለህዝቡ አጉል መልዕክት ማስተላለፋቸው ነው ሲሉ ያመለክታሉ። አሁን ባለው ሁኔታ የክልል አስተዳደሮቹ በአንድ በኩል የህዝብ ስጋቶችን ለመቀነስና ለማረጋጋት ሲሉ የሚወስዱት እርምጃ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካው ከእጃቸው እንዳይወጣ የሚያደርጉት ጥረት ድምር ውጤት ነው ይላሉ።
የክልል አስተዳደሮቹ ማዕከላዊ መንግሥትን ሳይጠብቁ በየራሳቸው አንዳንድ ነገር ማለትና ማድረግ ካልቻሉ ሰፊውን የህዝብ ግፊት መቋቋም አይችሉም፤ እንከስራለን የሚል ስጋትም ስላላቸው አማራጭ የላቸውም ብለዋል ፕሮፌሰር መረራ። ‹‹ከለውጡ በፊት የተለመደው አሰራር ከአንድ ማዕከላዊ መንግሥት ውሳኔዎች ይተላለፋሉ፤ አስፈጻሚ አካል ደግሞ ተቀብሎ የተላለፈለትን ብቻ ነው የሚፈጽመው፤ የነበረው ማዕከላዊ መንግሥትም ውሳኔዎችን በወቅቱ የሚያስተላልፍበት አሰራር አልነበረም። በመሆኑም መረጃዎችም ለህዝብ በወቅቱ አይደርሱም። ህዝቡም ላይሰማቸው ሚችልባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፤›› ሲሉ ያስታውሳሉ።
እንደ ፕሮፌሰር መረራ ገለፃ በተወሰነ ደረጃ በሀገሪቷ የመጣው ለውጥ የቀድሞውን አሰራር እያስቀረው መምጣቱ፣ በክልል አስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ግፊት መብዛቱ፣ አሁን ለሚታየው ክልሎች በየፊናቸው አቋም ለማንጸባረቅ ምክንያቶች እንደሆኑ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀጽ 50 ቁጥር 8 የፌደራሉ መንግስት እና የክልሎች ስልጣን በዚህ ሕገ መንግሥት ተወስኗል። ለፌዴራል መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት።
ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣንም በፌዴራሉ መንግሥት መከበር አለበት ሲል ደንግጔል። በመጨረሻም አስተያየት ሰጪዎቹ ያስቀመጧቸው ምክረሀሳቦችና ቀጣይ ስጋቶችም አሉ፤ የፌዴራል መንግሥት የተሰጠውን ሕገ መንግስታዊ ስልጣን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚያሰፍን መልኩ መጠቀምና መተግበር ይጠበቅበታል።
የፌደራሉ መንግስት ክልሎች ምን ያደርጋሉ? ብሎ መጠበቅ አያስፈልግም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ይህ ካልሆነ ግን ነገሮች ወዳልተፈለጉ አቅጣጫዎች ሊያመሩ ይችላሉ ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ክልሎቹ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠሉ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ይጣሳል፤ ይህ ደግሞ በሀገሪቷ ስርዓት ያሳጣል፤ ማዕከላዊ መንግሥቱንም በማዳከም ስርዓት አልበኝነት የሚሰፍን ከሆነ የክልል አስተዳደሮች ገዥ የሚሆኑበት፤ ዞኖችና ወረዳዎችም የክልል አስተዳደሮቹን ፈለግ የሚከተሉበት አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011
ለምለም መንግስቱ