ሚኒስቴሩ በስምንት ወር ውስጥ፡-
• የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን 72ነጥብ7 በመቶ አድርሷል፤
• ከ248ነጥብ46 ሚሊዮን ኪ.ዋ.ሰ በላይ ኃይል ከብክነት ታድጓል፣
• ከኃይል ሽያጭ ከ43ነጥብ17 ሚሊዮን ዶላር በላይ አግኝቷል፤
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ አገራዊ የመጠጥ ውሃ ሽፋንን 72ነጥብ7 በመቶ ማድረስ መቻሉን ሚኒስቴሩ ገለጸ። 248ሚሊዮን 467ሺ 28ነጥብ66 ኪሎ ዋት ሰዓት ኃይል ከብክነት መታደጉን፤ ከኃይል ኤክስፖርትም 43ሚሊዮን 17ሺ 730ነጥብ82 ዶላር ማግኘቱን አስታውቋል።
የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፤ በአገሪቱ የንጹህ መጠጥ ውሃና የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል። በስምንት ወራት ውስጥም የኃይል ብክነትን ለመከላከልና ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭም የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ድረስ (የትግራይ ክልልን ሪፖርት ሳያካትት) 2ሺ264 አዳዲስ የገጠር ውሃ ተቋማት እና ሁለት የከተሞች መጠጥ ውሃ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀው ለአንድ ሚሊዮን 569ሺ 841 ነዋሪዎች በተሻሻለው የአገልግሎት ደረጃ መሰረት የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። በዚሁ መሰረትም አገራዊ የመጠጥ ውሃ ሽፋንን 72ነጥብ7 በመቶ ማድረስ የተቻለ ሲሆን፤ 70ሚሊዮን 136ሺ 398 ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በተመሳሳይ የኃይል አቅርቦትን ከማሳደግ አኳያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ከመዘርጋት ባለፈ የኃይል ብክነትን ለመከላከል እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ 248ሚሊዮን 467ሺ 28ነጥብ66 ኪሎ ዋት ሰዓት ወይም 165ሚሊዮን 846ሺ 858ነጥብ02 ብር ከብክነት ማዳን መቻሉን ገልጸዋል። የኤሌክትሪክ ኃይል ምርትና ሽያጭን በተመለከተም በስምንት ወር ውስጥ 9ሺ606ነጥብ04 ጊጋ ዋት ሰዓት ማመንጨት መቻሉን በመግለጽ፤ ለሱዳንና ጅቡቲ ከተሸጠ 758ነጥብ4 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል 43 ሚሊዮን 17ሺ 730ነጥብ82 ዶላር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
የፕሮጀክቶች ግንባታን በተመለከተም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 66ነጥብ26 መድረሱን፤ 254 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የገናሌ ዳዋ-3 ኃይል ማመንጫ ግንባታም 97ነጥብ74 መድረሱንና ውሃ መያዝ መጀመሩን፤ በአንጻሩ 2ሺ100 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የኮይሻ ፕሮጀክት አፈጻጸም 26ነጥብ25 በመቶ መሆኑና የፋይናንስ እጥረት ያለበት መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።
የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫን በተመለከተም አሁን ያለበትን ችግር መሰረት ያደረገ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በመጠቆም፤ ፕሮጀክቱ እንዲከናወን እየተደረገ የህግ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራው እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በአንዳንድ በተለይም በመስኖ ፕሮጀክቶች በህብረተ ሰቡ ዘንድ የሚታይን የራስ አድርጎ ያለመመልከት ችግር ከማቃለል፤ የአማካሪዎች፣ የዋናና ንዑስ ተቋራጮች ውል ማቋረጥን፤ የፋይናንስ ችግርን እና ሌሎች ተያያዥ ለተቋሙ ሥራ መጓተት ምክንያት የሚሆኑ ነገር ግን ከሚኒስትሩ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮች እንዲፈቱ ከማገዝ አኳያ ምክር ቤቱ የድርሻውን ድጋፍ እንዲያደርግም ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
ወንድወሰን ሽመለስ