አዲስ አበባ:- የፓርቲዎቹ ቁጥር 107 መድረስ ህዝቡ ምን አይነት ርዕዮት ዓለም ያለውን ፓርቲ መምረጥ እንዳለበት እንዳይለይ ከማድረጉም ባሻገር ለአሰራር ምቹ አለመሆኑ ተገለጸ።
በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጎልተው ሲታዩ የነበሩ አሁን ግን ከፓርቲ ተሳትፎ ራሳቸውን ያገለሉት አቶ ሙሼ ሰሙ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ፓርቲ ሊብራል፣ ለዘብተኛ ሊብራል ወይም አክራሪ ሊብራል በሚል ሦስት ሊሆን ይችላል። ይህ ባደጉት አገርም የተለመደ ነው። ሊበራል ዴሞክራት ነኝ የሚሉ ሦስት ፓርቲዎች ለምን ይኖራሉ? ተቀምጠው መነጋገር እና ወደ አንድ አደረጃጀት መምጣት አለባቸው።
ሌላው ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርቲን በብሔር ማደራጀት በመፈቀዱ የብሔርን ጥቅም ለማስከበር የሚደራጁ ፓርቲዎች መኖራቸው ቁጥሩ እንዲበዛ ማድረጉን የገለጹት አቶ ሙሼ፣ መሰረታቸው የየራሳቸው ብሔር በመሆኑና የሌሎቹን ጥቅም ስለማያስከብሩ ከሌላው ጋር መደራጀት አይችሉም። ስለዚህ ችግሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ አቶ ሙሼ ገለጻ፣ መስፈርቱን አሟልተው የተመዘገቡት 107 ሳይሆኑ 66 ፓርቲዎች ናቸው፤ ቀሪዎቹ በሂደት ላይ ይገኛሉ ቢባልም የፓርቲዎች ማቋቋሚያ በሚያዘው መሰረት ሁሉንም ነገር አሟልተው ተደራጅተው የሚሠሩ አምስት ፓርቲዎች እንኳ መኖራቸውን እርግጠኛ አይደሉም።
በወቅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ፣ በምርጫ መሳተፍ፤ አመራር መለወጥ፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ኦዲት ማድረግን ሁሉ የሚጨምረውን መስፈርት አሟልተው የሚሠሩት እጅግ ውስን ፓርቲዎች ናቸው ያሉት አቶ ሙሼ፣ ፓርቲዎች በትክክል ሂሳባቸውን ኦዲት አድርገው ያውቃሉ? ህዝባዊ ውይይት ያካሂዳሉ? ቢባል በተግባር ቢፈተሽ የሚገኘው ጥቂት ነው። ስለዚህ ህዝብን ያላወያዩና በመስፈርቱ መሰረት ያልሠሩ ውክልና የሌላቸው በመሆኑ እንደ ፓርቲ ሊጠሩ እንደማይገባም አመልክተዋል።
የፓርቲ መብዛት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር ውስጥ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። አገሪቷ ያላትን ውስን ሀብት፣ የሰው ኃይል እና አቅርቦት ለብዙ መከፋፈል ጠንካራ ፓርቲ እንዳይፈጠር ስለሚያደርግ ቁጥራቸው የሚቀንስበትን መንገድ መፈለግ አለበት ብለዋል።
አቶ ሙሼ፣ ምርጫ ቦርድ ፕሮግራማቸውን የሚያውቅ በመሆኑ አሁን ያሉትን ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ አጋዥነት አደረጃጀታቸው ቅርፅ እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል። ቦርዱ ተቀራራቢ ፕሮግራም ያላቸውን ሰብሰብ በማድረግ አብረው እንዲሠሩ መድረክ ቢያመቻች ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ሙሼ ገለፃ፤ አንዳንዱ ፓርቲ አባል የለውም፣ ገንዘብ የለውም፣ ሥራ አስፈፃሚ የለውም፣ ማዕከላዊ ምክር ቤት የለውም፣ መድረክ መፍጠር አይችልም ነገር ግን ማህተም እና ያልታደሰ ሰርተፍኬት ይዞ ቁጭ ብሏል። ይህንን ፓርቲ ነው ለማለት ያዳግታል።
ምርጫ ቦርድ ፓርቲ ያልሆኑትን ሰብስቦ ፓርቲ ናቸው ከማለት የፓርቲ መስፈርት የማያሟሉትን ማስወገድ አለበት። መስፈርቱንም አሁን ካለውም በላይ ማጠንከር እንደሚጠበቅበትም ያሳስባሉ። በትክክል በተግባር የሚሠሩትን ብቻ መያዝ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው ‹‹107 ፓርቲ አለ ማለት አይቻልም፤ በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡት 66 ናቸው›› እነዚህም በዝተዋል ከተባለ ለመብዛታቸው መንስኤው ፖለቲካው በብሔረሰብ ላይ የሚያጠነጥን በመሆኑ ነው በማለት በአቶ ሙሼ ሃሳብ ይስማማሉ።
‹‹አሁን 107 ፓርቲ አለ ይባላል። ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ ውጤታማ ሥራን የሚሠሩት እና ጠንካራ አማራጭ ለህዝብ በማቅረብ ጥሩ ተፎካካሪ የሚሆኑት በሂደት ይታያሉ። አብዛኞቹ የማይቀጥሉ ናቸው። ጎበዞቹም ዓላማቸው ማሸነፍ በመሆኑ ‹‹እርስ በርሳቸው መገናኘታቸው አይቀርም›› ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ ፓርቲዎቹ እንዲሰባሰቡ ለ28 ዓመታት ከታገሉ ሰዎች መሃል መሆናቸውን አስታውሰው፣ የአንዳንድ ፓርቲዎቹ መነሻ መርህና ርዕዮት ዓለም ሳይሆን ብሶት መሆኑ እና አንዳንዶች ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ መተዳደሪያቸው መሆኑ ቁጥራቸው እንዳይቀንስ ማድረጉን አመልክተዋል።
እንደ ፕሮፌሰር በየነ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመርህ ተደራጅተውና በዓላማ ዙሪያ ተሰባስበው አመራሮቹም ይህን አውቀው ርዕዮት ዓለምን መሰረት በማድረግ አገራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የነበረው ጥረት በፓርቲዎቹም ጭምር አለመሳካቱን አስታውሰው፤ ወደፊትም ከፓርቲዎች ብቃት ጋር ተያይዞም ጭምር መሰብሰብ እንደሚያዳግት ተናግረዋል። መሰባሰቡ አስፈላጊ በመሆኑ ‹‹ጥረታችንን እንቀጥላለን›› ሲሉ አሳውቀዋል።
ቀጣዩን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እና የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚገዛ የአሰራር ሥርዓት የቃል ኪዳን ሰነድን 107 ፓርቲዎች ሰሞኑን መፈረማቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
ምህረት ሞገስ