በአቡዳቢ እና በኢትዮጵያ መካከል በጋራ ጉዳይ ላይ ውይይት መካሄዱን ከአቡዳቢ የተለቀቀው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና በአቡዳቢ አልጋ ወራሽ ሼህ ሙሃመድ ቢን ዛይድ አል ናይን መካከል ከትናንት በስቲያ ውይይት መካሄዱን ከአቡዳቢ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሁለቱ መሪዎች በሁለቱ አገሮች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት የተወያዩ ሲሆን፤ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል። በተለይም በልማት፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ላይ የሁለቱንም አገራት ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ ተባብረው ሊሰሯቸው በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይም ተነጋግረዋል።
መሪዎቹ በሁለቱም በኩል ባሉ ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ልማቶች ላይም ትኩረት ሰጥተው የተወያዩ ሲሆን፤ አልጋ ወራሹ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአቡዳቢ ግንኙነት ማዕከል የሚያደርገው በእውነተኛነት፣ በመከባበር፣ በማረጋጋት እና በሰላማዊነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረው ግንኙነትም የሁለቱንም አገራት እና ህዝቦች በሚጠቅም እና ስኬታማ በሚያደርግ መልኩ መሆኑን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፤ አገሪቷን በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀው፤ ያላቸውን ግንኙነት አገራቸው ማጠናከር እንደምትፈልግ ጠቁመዋል። በንግድ፣ በኢንቨስትመንትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ያላቸው ግንኙነት ጠንካራ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የሁለቱ መሪዎች ውይይት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር አንዋር ቢን ሙሃመድ ጋርጋሽ፣ የኢነርጂ ሚኒስትሩ ሱሃይል ቢን ሙሃመድ ፋራጅ ፋሪስ፣ የአቡዳቢ ፍርድ ቤት ዋና ፀሐፊ ሙሃመድ ሙባረክ በተገኙበት መካሄዱ ታውቋል።
የአቡዳቢ አልጋ ወራሽ ሼህ ሙሃመድ ቢን ዛይድ አቡዳቢ አል ባተን አየር ማረፊያ ተገኝተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እንደተቀበሏቸው ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
ምህረት ሞገስ