«መብራት ኃይል ቆጣሪዎቹን ሲተክል በፈጸመው ስህተት ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው» – ህንጻው ሲገነባ በኤሌክትሪክ ዝርጋታ የተሳተፉ ባለሙያዎች
«እርምጃ እንወስዳለን፤ቆጣሪዎቹ ሲገጠሙ ለተፈጠረው ክፍተትም ኃላፊነት ወስደን ቆጣሪዎቹን እናስተካክላለን» -የምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት
የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት መርሃግብር በ2005 ዓ.ም. ይፋ ከተደረገ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለነዋሪዎች ከተላለፉት 972 ቤቶች ውስጥ ከፊሎቹ የተገነቡት በሰንጋ ተራ ነው። ቤቶቹ ለነዋሪዎች የተላለፉበት ወቅት ቆየት ያለ ቢሆንም አብዛኞቹ በቤቶቹ ውስጥ መኖር ከጀመሩ ከአንድ ዓመት የበለጠ ጊዜ አላስቆጠሩም።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ በሰንጋ ተራ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት በሚገኙ አምስት ህንጻዎች ላይ ባደረገው ፍተሻ ህገወጥ በሆነ መንገድ ቀጥታ ኃይል በመጠቀም ስርቆት ሲፈጽሙ አገኘኋቸው ባላቸው 51 ደንበኞች ላይ እርምጃ ወስዷል። እየተወሰደ ያለውን እርምጃ አስመልክተው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
በህንጻ ቁጥር ሶስት ላይ የቤት ባለቤት የሆኑት አቶ መልቾ ሌንጮ «ከቆጣሪ ውጪ ቀጥታ ኃይል ስትጠቀሙ ተገኝታችኋል ብለው መብራት ቆርጠውብን ሄደዋል። እኛ ግን አስራ ሁለት ወራት በካርድ ነው እየተጠቀምን ያለነው። እንዴት ሊሆን ይችላል?»« በማለት የተወሰደው እርምጃ ግራ እንዳጋባቸው ይገልጻሉ። አያይዘውም ቤቱን ከተከራዩ ጀምሮ ተከራዩ ለስምንት ወራት የአንድ ሺ ሶስት መቶ ብር ካርድ ሞልተዋል።
ከዚያ በፊት ቤቱ ዝግ ሆኖ በቆየባቸው አራት ወራት የአራት መቶ ብር ካርድ ሞልቻለሁ ብለዋል። እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው ቅጣት ተገቢ አለመሆኑን ሲገልጹም «ከማብሰያ፤ ፍሪጅና ቴሌቪዥን ውጪ ጥቅም ላይ የዋለ ነገር ሳይኖር 44 ሺ ብር ክፈል ተብያለሁ። በተጠቀምነው ልክ ክፈሉ ብንባል እንኳን እንዴት 44 ሺ ብር ይመጣል? ቤቱን ከተረከባችሁ ጀምሮ እስካሁን ያለውን አልከፈላችሁም በሚል ነው ሂሳቡ የተሰላው» ብለዋል።
አቶ መልቾ ሌንጮ «ይህ በፍጹም ፍትሃዊ አይደለም፤ ጉዳዩ ቢመረመር የመብራት ኃይል ችግር እንጂ የተጠቃሚው ችግር አይደለም። ሰው እስከ 40 ሺ ብር ድረስ እየተጠየቀ ነው። በምን አቅሙ ነው የሚከፍለው? ስለዚህ ትክክል አይደለም። እናንተ ለሚመለከተው አካል እንድታደርሱልን አደራ እላለሁ» ሲሉ የተወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።
አንዳንድ ስራዎች ስላልተጠናቀቁ ዝግ ሆኖ የቆየው ቤታቸው ከተከራየ ገና አንድ ወሩ መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ ገነት ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው ከሳምንት በፊት መጥተው በህገ ወጥ መንገድ እየተጠቀማችሁ ነው ብለው መብራት ቆርጠውብን ሄደዋል። በኋላም ቤት ውስጥ ያሉትን የኤሌክትሪክ መጠቀሚያዎች ቆጥረው 45 ሺ ብር ክፈሉ ብለውናል።ለመጀመሪያ ጊዜ ካርድ የሞላነው ቤቱን ማስተካከል ስንጀምር ነው። ቤቱን ለማስዋብ የተጠቀምነው የኃይል ፍጆታ አነስተኛ ነው። ለመብራት ኃይል ቅሬታ አቅርበን ማመልከቻ አስገቡ ተብለን ማመልከቻ አስገብተናል። እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልተሰጠንም ብለዋል።
16,130 ብር የፍጆታና የቅጣት ሂሳብ ተተምኖባቸው ክፍያውን የፈጸሙት አቶ ሸዊት ገብረጽዮን ቀጥታ ተጠቅመህ ስርቆት ፈጽመሃል አሉኝ። እኔ መጀመሪያ ካርድ ሞልቼ ቤቱን አከራይቻለሁ። በቤቱ ውስጥ ኑሮ ከተጀመረ ስምንት ወራት ተቆጥሯል። ቤት ውስጥ የምትጠቀሙበትን የኃይል መጠን አስልተናል አሉኝ። ተከራዩ አራት ቀን ያለመብራት ስለተቀመጠ ከፍያለሁ ሲሉ ይናገራሉ። ፍትህ አገኛለሁ ብለው ተስፋ እንደማያደርጉ ሲገልጹም፣ ምን አማራጭ አለኝ ዝም ብዬ ብከራከር ምን አመጣለሁ የምታሸንፈውን ሰው እኮ ነው የምትከራከረው። መጋቢት ሁለት ሰኞ እለት አቋረጡብን አርብ ዕለት ክፍያውን ፈጸምኩ፤ ቅዳሜ መጥተው ቀጥለውልኛል። ቅሬታ ለማቅረብ አልሞከርኩም ምክንያቱም ይህ ቤት ሲሰጠኝ ጀምሮ ብዙ ቅሬታ አቅርቤ ነበር የሰማኝ የለም ብለዋል።
አቶ ሰለሞን እሸቱ በህንጻ ቁጥር ሶስት ላይ ከመጀመሪያ ጀምሮ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ተስፋለም ኤርሚያስ በሚል ማህበር በኤሌክትሪክ ሙያ ተሰማርተው የመስመር ዝርጋታውን መስራታቸውን ይናገራሉ። እርሳቸው ሲያሰረዱም በህንጻው በሚገኙት ቆጣሪዎች ላይ ያሉት ገመዶች እንደሌሎች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወይም በሌሎች መኖሪያ ቤቶች እንዳለው አይነት አይደሉም። ከቆጣሪው ውጪ ቀጥታ የሚመጣው የመብራት ኃይል መስመርና በቆጣሪው አልፎ ወደ ቤት የሚገባው መስመር አጠገብ ለአጠገብ ያሉ ናቸው። ይህን ነገር የሚያውቁት ደግሞ በአብዛኛው በመስመር ዝርጋታው የተሳተፉ እርሳቸውን የመሰሉ ሰዎች ናቸው። ከሌላ ቦታ አንድ ባለሙያ መጥቶ ኤሌክትሪክ ለማስተካከል ሲጥር ቀጥታ የሚፈልገው ኃይል ያለውን ገመድ ነው። ስለዚህ ኃይል መኖሩን ሲፈትሽ ቀጥታ ከመጣው መስመር ያገኛል፤ በዚህ ጊዜ ባለማወቅ ያገኘውን የኃይል መስመር ይዞ ወደ ቤት ያስገባል።
እንደ ኤሌክትሪክ ባለሙያው ገለጻ ስህተቱ እየተፈጠረ ያለው ባለማወቅ ነው። አንዳንድ ጊዜ ለስራ በሚዞሩበት ሰዓት ችግሩን ተመልክተው ህገወጥ መሆኑን ሲገልጹ ተጠቃሚዎች ካርድ እየሞሉ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ይናገራሉ። አብዛኞቹ ባለቤቶች ወዲያውኑ እርምጃ ወስደው እንዲስተካከል ሲያደርጉ መመልከታቸውን በመግለጽ የቆጣሪው አተካከል የችግሩ ምንጭ መሆኑን ገልፀዋል።
ሌላኛው የኤሌክትሪክ ባለሙያ አቶ አብዮት ተሰማ፣ በኃይሉና ጓደኞቹ በሚል ማህበር በሕንጻ ቁጥር አንድ ላይ የኤሌክትሪክ ዝርጋታውን መስራታቸውን ይናገራሉ። በነዋሪዎቹና በመብራት ኃይል መካከል ስላለው ክርክር ሀሳባቸውን ሲገልፁ፣ ችግሩ ከተጠቃሚዎቹ አይመስለኝም። መብራት ኃይል የኪሎ ዋት ሀወር የቀጠሉበት አግባብ ነው ችግር እየፈጠረ ያለው። ኪሎ ዋት ሀወር ላይ ሁለት ገመድ ነው መውጣት ያለበት፤ ፌዝና ኒዩትራል የሚባለው አንዳንድ ጊዜ ግራውንድ ኖሮት ሶስት ሊሆን ይችላል። በሰንጋ ተራ በተገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግን አራት ገመዶች ናቸው የሚወጡት፤ ከሌላ አካባቢ የመጣ ባለሙያ ሲያየው በቃ ኃይል ያለው የትኛው ነው ብሎ ፈትሾ አያይዞ ነው የሚሄደው፤ ስለዚህ ችግሩ ሰዎቹ ጋ አይመስለኝም። ተጠቃሚዎቹ ካርድ ይሞላሉ፤ ያልጨረስናቸው አንዳንድ ስራዎች ስላሉን እዚህ ስንመጣ ተቆረጠብን የሚሉ ሰዎች ገጥመውናል ብለዋል።
በምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት የአውቶሜሽንና ቴክኖሎጂ ክፍል ኃላፊ ወይዘሮ ጽጌሬዳ ገበየሁ በሰንጋ ተራ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የደረሳቸውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ በአካባቢው ከሚሰሩ አገልግሎት ማዕከላት ውጪ ያሉ አባላት የተካተቱበት ቡድን በማዋቀር ምርመራው መከናወኑን፤በዚህም በአምስቱ ህንጻዎች 51 ደንበኞች ከቆጣሪ ውጪ ቀጥለው ሲጠቀሙ መገኘታቸውን፤ ግኝቱን ተከትሎም በምዕራብ ዲስትሪክት ልደታና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች ለደንበኞች አሰፋፈር በሚመች መልኩ በተከፈቱት የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በኩል መስመር የማቋረጥ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ኃላፊዋ በቆጣሪዎች አተካከል ላይ ችግር ስለመኖሩ ባለሙያዎች ስለሰጡት ምስክርነት ሀሳባቸውን ሲገልጹ፣ ቆጣሪዎቹ መጀመሪያ ሲገጠሙ የተወሰኑ ክፍተቶች ተፈጥረዋል። አራት ገመዶች በግልጽ ይታያሉ። እነዚህ ተጋላጭ ናቸው። የተወሰኑት ግን አራት ገመዶች ቢሆኑም የተስተካከሉ በመሆናቸው ወጪና ገቢን ለመለየት አያስቸግሩም። የተቀሩት ግን ክፍተቶች አሉባቸው፤ ዛሬ ላይ እርምጃ ብንወስድም በእኛ በኩል ለተፈጠረው ክፍተት ኃላፊነት በመውስድ ቆጣሪዎችን እናስተካክላለን ብለዋል ።
ደንበኞች በተዋዋሉት ውል መሰረት ከቆጣሪ ውጪ መስመር ቀጥሎ መጠቀም ወንጀል መሆኑን የሚጠቅሱት ኃላፊዋ፤ የኋላ ፍጆታና የቅጣት ክፍያ ከማስከፈል በተጨማሪም ድርጊቱ ወንጀል ስለሆነ ህግ ክፍልም ይዞት በወንጀል እንዲጠየቁ የማድረግ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የቅጣትና የኋላ ፍጆታ ተመን ስለሚተመንበት መንገድ ሲያብራሩም፤ ደንበኛው ውል ሲዋዋል የውልና የአይዲ ቁጥር ስላለው በዚያ መሰረት የአሞላል ታሪካቸውን በማየት ከሲስተም ጋር የተዋወቀበትን ጊዜ በማየት፤ ቤት ውስጥ እየተኖረ ስለመሆኑም በማጣራትና ቤት ውስጥ ያሉ የኤልክትሪክ ቁሳቁሶችን በማየት ለእያንዳንዱ የተቀመጠ መስፈረትን መሰረት በማድረግ ዋጋ ይተመናል ብለዋል።
ደንበኛው ከሲስተሙ ጋር ተዋወቀ የሚባለው ካርዱን ለመጀመሪያ ጊዜ ቆጣሪውን ሲያስነብብ ነው የሚሉት ኃላፊዋ፤ ካርዱን ሳያስነብብ በቀጥታ መጠቀም የጀመረ ደንበኛ ቅጣቱ እንዴት ነው የሚሰላው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አልቻሉም።
በምዕራብ አዲስ አበባ የደንበኞች አገልግሎትና ሽያጭ ኃላፊ ወይዘሮ ምናቤ ገብረስላሴ መብራት የቋረጠባቸው ደንበኞች እያቀረቡ ላሉት ቅሬታ የመስሪያ ቤታቸው ምላሽ ምን እንደሆነ ሲገልጹ” እርምጃ ወደመውሰዱ ብንገባም ሆነ ተብሎ ነው የተፈጸመው ወይስ ቴክኒካል እውቀቱ ስለሌለው ነው የሚለውን ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁመን እየመረመርን ነው ። መቋጫው ላይ አልደረስንም ግን ጀምረናል” ብለዋል።
የምርመራ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘውዱ ኃይለሚካኤል ደግሞ የቆጣሪው አገጣጠም ትክክል ይሁን አይሁን ወደፊት በኮሚቴው እንደሚረጋገጥ ገልጸው፤ ደንበኞች ስለተጠየቁት የተጋነነ ክፍያ ሲያብራሩ ደንበኛው ቆጣሪውን በመንካቱ የሚቀጣው መኖሪያ ቤት ከሆነ ብር 500፤ ንግድ ቤት ከሆነ ደግሞ ብር 1000 ነው ፤ የተቀረው ሂሳብ ፍጆታው ነው ብለዋል።
ስለቅጣት ክፍያው ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ወይዘሮ ጽርጌሬዳ ገበየሁ የፍጆታ ሒሳቡ የስርቆት ሲሆን ቅጣት ስላለው አንድ ደንበኛ በትክክለኛው መንገድ ቢጠቀም ከሚከፍለው ይልቃል ብለዋል። እስከ 1500 ብር ድረስ ካርድ ሞልተው 44 ሺ ብር እንዲከፍሉ ስለተጠየቁ ደንበኛ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የሞሉትን ካርድ ሒሳብ ከ44 ሺ ብሩ ላይ ተቀናሽ እናደርጋለን ብለዋል። በየቤቱ በመሄድ ዋጋ የሚገምቱት ሶስት የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ከደንበኞች ጋር በመመሳጠር ደንበኛው የሚገለገልባቸውን የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች ቀንሶ በማስመዝገብ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ጥረት እንዳያደርጉ በምን መልኩ እንደሚከላከሉ ሲጠየቁም ግምቶቹ የተጋነኑ ወይም ከምንገምተው ውጭ ከሆኑ የማጣራት ስራ እንሰራለን ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
የትናየት ፈሩ