በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው የሚነሱት ፖለቲካዊ ትኩሳቶች የሚያርፉት በህዝብ ላይ ነውና ሰበብ አስባብ እየተፈለገ ከየቀዬው የሚፈናቀለው ዜጋ ቁጥር ጨምሯል። ጊዜያዊና ነቢባዊ ፍላጎት የነገሰባቸው ወገኖች በሚነዙት አፍራሽ ትርክት የዜጎች ማህበራዊ ህይወት እየተበጠበጠ ነው። በዚህም የተነሳ የጌዲኦ ዞንና የምዕራብና መካከለኛው ጎንደርን ጨምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቁጥሩ ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የበለጠ ህዝብ ተፈናቅሏል።
እንደዚህ ዓይነቱ በጊዜያዊ፤ ያውም ሰው ሰራሽ በሆነ ችግር ዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁና የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን በምንም መመዘኛ አግባብ አይደለም። ከኖሩበት፤ ሀብት ንብረት ካፈሩበት፤ ለዘመናት በትውልድ ቅብብሎሽ ከተጋመዱበት አካባቢ ሰበብ እየፈለጉ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ህዝቦችን ማፈናቀል በምድራዊ ህግም ይሁን በመንፈሳዊ መንገድ የሞራል ተጠያቂነት ያስከትላል።
ዜጎች በሚፈናቀሉበት ወቅት የሚከሰተው ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ በጋራም ይሁን በተናጠል ከሚያጋጥማቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ይልቃል። ቀውሱ በሚታከምበትም ወቅት ረጅሙን ጉዞና አሻጋሪውን ምዕራፍ የሚይዘው ይኸው ጉዳት ነው።
ዜጎች ባላሰቡት ጊዜ፤ በተለይም ተገድደውና ተገፍተው ሲፈናቀሉ ይበልጡኑ የሚጎዱት ሕፃናት፤ ሴቶች፤ አካል ጉዳተኞችና አዛውንቶች ናቸው። እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ ይኖሩበት ከነበረው ቤተሰባዊ ህይወት ወጥተው ቤትና ንብረታቸውን ጥለው ወደ አልኖሩበት አካባቢ ሲሰደዱ የሚሰማቸው የመጀመሪያው ስሜት ባይተዋርነት ነው። ሰው በሀገሩ ውስጥ ሆኖ ባይተዋርነት ሲሆን ደግሞ ትልቁ ሰብዓዊ ቀውስ ነው። ነገር ግን ይህ ቀውስ ሊቆም ዜጎችም ወደ ቀያቸው ሊመለሱና ሊቋቋሙ ይገባል።
በዚህ በያዝነው ሰሞን እነዚህን የተፈናቀሉ ወገኖች ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም ጥረቶች ሲደረጉ እያየን ነው። የሚሰጠው ድጋፍ ግን ዜጎችን መልሶ ወደነበሩበት ቦታና ሁኔታ በሚመልስ መልኩ መሆን አለበት። ታዳጊዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመፈናቀላቸው ከትምህርት ገበታቸው ተነጥለዋል። እንስሳትም ተንከባካቢ አጥተው ተበትነዋል። መጪው ጊዜ ደግሞ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የክረምት ወቅት ነውና አስፈላጊውን ሁሉ አድርገን በጊዜ ካልተሰበሰቡ ችግሩ ከዚህ የበለጠ ይከፋል። እናም የዕገዛውን መጠንና ስፋትም እንዲሁ ከልክ ያሳልፈዋልና መረባረብ ይገባል።
እስካሁን በፌዴራል መንግስትም ሆነ በረጂ ድርጅቶች የሚደረገው ጥረት የሚመሰገን ነው፡፡ ሆኖም ግን ተጎጂዎች ተረጂ ሆነው መቀጠል የለባቸውም፡፡ ያለፍቃዳቸው ቤትና ቀያቸውን አስጥሎ ያሰደዳቸው ሰው ሰራሽ ችግር እንጂ ተፈጥሯዊ አደጋ ባለመሆኑ መፍትሄውም የሚገኘው በሰው እጅ ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም መረባረብ አለብን፡፡
በዚህ ረገድ የፖለቲካ ሃይሎች ብዙሃኑን በማያማክል ስሌትና ለጊዜያዊ ጥቅም እና ትርፍ ሲሉ አብሮ የኖረውን እና ወደፊት እስከ ፍጻሜ የሚዘልቀውን ህዝብ ቁርሾ ባያሲዙት መልካም ነው፡፡ እናም ከህዝብ የሚበልጥ ምንም ነገር የለምና ህዝቡን ባጠቃላይ፤ በተለይ ደግሞ ከየአካባቢያቸው ተፈናቅለው በየጥጉ የተጠለሉትን ማህበረሰቦች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ የሚያደርግ አጀንዳ ይዘው ሊሰሩ ይገባል፡፡
በየትኛውም ወገን የሚሰሩ አክቲቪስቶችም ቢሆኑ ከዚህ ጊዜ በላይ ለህዝብ ሊቆሙ የሚገባቸው ጊዜ የለም። በተለመደ የማግባባትና ወደ ተግባር የመቀየር ብልሃታቸው የአገር ውስጡም ይሁን የውጭው ማህበረሰብ ለእነዚህ ተፈናቃዮች የዘለቄታ ህይወት መለወጥ እንዲቆም ሊሰሩ ይገባል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አገር በቀልና የውጭ የእርዳታ ድርጅቶችም ተጎጂዎቹ አሁን ባሉበት ሁኔታና ደረጃ እርዳታና እገዛ የማድረጉ ነገር እንዳለ ሆኖ፤ ለዘለቄታው ወደ ነበሩበት የሚመለሱበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባቸዋል፡፡
እኒህ ለጊዜው በመጠለያ ተኮልኩለው የሰው እጅ የሚጠብቁ ዜጎች ሁኔታዎች ቢለወጡላቸው እና አካባቢያቸው ቢረጋጋላቸው ሰርተው የሚያድሩ፤ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሚተርፉ ናቸው፡፡ እናም ከእለት እርዳታ በዘለለ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መስራት ተገቢ ነው፡፡
የፌዴራልና የክልል መንግስታትም ቢሆኑ ህልውናቸው ከህዝብ ውጭ ሊሆን አይችልምና ከዚህ በላይ ለህዝብ መቆምን ማሳየት የሚችሉበት ጉዳይም ጊዜም የለምና አቅማቸውን አሟጥጠው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ የመጀመሪያውና ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሲሆን፤ በቀጣይ ማንም ዜጋ በተለይ በአካባቢው በሚነሳ ጉልበተኛና ለህግ አልገዛም ባይ እንዲህ አይነት ችግር እንዳይከሰት መስራት አለባቸው፡፡ ከምንም በላይ የህግ የበላይነት መከበር አለበትና ሁሉም ወገን ለዚህ ተግባራዊነት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ሁላችንም ዜጎችን ለዘለቄታው በማቋቋም ዋስትና ያለው ህይወት እንዲመሩ የየድርሻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2011