አዲስ
አበባ፡- ለ2011/2012 ምርት ዘመን ለበልግና ለመኸር ወቅት የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ በማሰራጨት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና
ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ። የተለያዩ የግብርና ግብአቶችንም በማቅረብ ላይ ነው። የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ማህበራዊ
ጉዳዮች አገልግሎት ኃላፊ ወ/ሮ አማረች በቀለ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ለአርሶ አደሩ በወቅቱና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ
የሚያስችል የግዢ ሂደት ተከናውኖ በአሁን ሰዓት ማዳበሪያው ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዘና እየተሰራጨ ነው።
ሀገር አቀፍ የማዳበሪያ አቅርቦት አንድ ሚሊዮን 125 ሺ ሜትሪክ ቶን መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ ይህም ግብርና ሚኒስቴር በሚያደርገው ድልድል መሰረት ለህብረት ሥራ ዩኒየኖች የሚከፋፈል መሆኑን አስታውቀዋል። ኮርፖሬሽኑም የራሱን ድርሻ ባሉት የሽያጭ አውታሮቹ መሰረት ሽያጭ እንደሚያከናውን ጠቅሰው በዚሁ መሰረት በአሁን ሰዓት 542 ሺ 166 ኩንታል ማዳበሪያ በብር 702 ሚሊዮን 402 ሺ12 ሽያጭ ማከናወኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽ በገበያ ላይ ባደረገው የዋጋ ድርድር በዩሪያ ማዳበሪያ በአማካይ በአንድ ቶን የአርባ ሁለት ነጥብ ሃምሳ
አራት ዶላር የዋጋ ቅናሽ ማግኘቱን አስታውቀው ባለፈው ዓመትም የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያ በማድረግና የግዥ ሂደቱን በማስተካከል ወደ ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ቅናሽ በመገኘቱ አርሶ አደሩ በኩንታል ከሁለት እስከ ሦስት መቶ ብር ቅናሽ እንደተደረገለት አስታውሰዋል፡፡ ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ለምርት ዘመኑ በእቅድ ከተያዘው 150 ሺ 870 ኩንታል ውስጥ 115 ሺ 155 ኩንታል ለማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ይሄም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተለያዩ ተጠቃሚዎች የተሰራጨ ሲሆን በኮርፖሬሽኑ በኩል በአሁን ወቅት 30 ሺ 967 ኩንታል
ተሸጧል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የጸረ- አረም መድሃኒት፤ የተለያዩ የጓሮ አትክልት ዘሮች፤ የመርጫ መሣሪያዎች፤ የተለያዩ የእንስሳት መድሃ ኒቶች፤ የተለያዩ ጸረተባይ መድሃ ኒቶች፤ ፈሳሽና የአበባ ማዳበሪያዎች፤ ትራክተርና የተለያዩ የተሽከርካሪ መለዋወጫና ጎማዎች፤ የመሬት ልማት አገልግሎት፤ የደረቅ ጭነትና የጥገና አገልግሎት በማቅረብ ላይ የሚገኝ ሲሆን የኮንስትራክሽንና የእርሻ መሣሪያዎች ጥገና የቴክኒክ ሙያ ማስልጠኛ ማዕከል በማደራጀትና የዕውቅና ፈቃድ በማግኘት በርካታ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ላይ መሆኑን ኃላፊዋ አስታውቀዋል
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
ሞገስ ፀጋዬ