ዕርዳታ ተቋርጦባቸዋል እየተባለ የሚዘገበው ከዕውነት የራቀ ነው
አዲስ አበባ፡- በምዕራብ፣ ምሥራቅ ጉጂና ጌዴኦ ዞኖች በተለያዩ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃች ሰብዓዊ ዕርዳታ እየተደረገ ሲሆን በተለይ ጌድኦ ላይ ሴቶችና ሕፃናት በተለየ መልኩ እየተረዱ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። ለተፈናቃሉ የጌዴኦ ማህበረሰብ ዕርዳታ ተቋርጦባቸዋል እየተባለ የሚዘገበው ዘገባ ከዕውነት የራቀ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታወቀ። ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት ጌድኦ ላይ በተለየ መልኩ ሕፃናትና ሴቶች እየተረዱ ቢሆንም በቀጣይ ዜጎቹን ወደ ቀያቸው በጊዜያዊነት ለመመለስ ከዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሠራ ይገኛል።
ለተረጂዎች የሚደርሰው የሰብዓዊ ዕርዳታ እስከአሁንም ያልተቋረጠና ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ በሰላም ግንባታም ሆነ ሰብዓዊ ዕርዳታ በማድረስ ረገድ የተቋረጠ ነገር አለመኖሩን ጠቅሰዋል። ከምሥራቅ ጉጂ ተፈናቃዮች 13 ሺ ገደማ የሚሆኑ ዜጎች ብቻ ሲቀሩ ከምዕራብ ጉጂ የተፈናቀሉት በሙሉ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ጠቅሰዋል። ሚኒስትሯ እንዳሉት ተፈናቃዮችን በቋሚነት የማቋቋም ሥራ ለመሥራት የኦሮሚያ፣ የደቡብ እና የፌዴራል መንግሥት አካላት ኃላፊነቱን ወስደዋል። ባሳለፍነው ዓርብ በነበረው ውይይት ከተፈናቃዮች ጋር ለስምንት ወራት ዕርዳታ አላገኘንም የተባለው ትክክል አለመሆኑን ተግባብተናል ብለዋል። መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ በዚህ መንገድ የዘገቡት ትክክል አለመሆኑን ጠቅሰዋል። በመሀል በአካባቢው
የፀጥታ ችግር ስላለ የተደራጁ ቡድኖች ዕርዳታውን የመቀማትና ለራስ ጥቅም የማዋል ችግሮች ነበሩ፤ በአመራር ችግር ምክንያት መድረስ ያለበት መጠን ሳይደርስ የቀረበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል። በማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተሰራጩ ያሉ ፎቶዎችን የሚያጣራ ቡድን መድበናል ያሉት ሚኒስትሯ በማህበራዊ ድረገፅ ላይ የተለቀቀው እናት ፎቶ በርሀብ ምክንያት ነው ወይንስ በሌላ የጤና ችግር የሚለውን ለማጣራት ለጤና ምርመራ ተልከዋል። ሀቁ ምንድነው የሚለው ወደፊት ይገለጸል፤ በርሀብና በችጋር ምክንያት በቀን አራት ወይም አምስት ሰው ይሞታል የሚለውም ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል። ከጤናና ከውሃ ወለድ በሽታዎች ጋር የተያያዙ ችግሮች ግን አሉ። እነሱን መቀየር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላም በኩል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ትናንት ባሰራጨው መግለጫው እንዳስታወቀው የፌዴራል መንግሥት በሰላም ሚኒስቴር በኩል ባደረገው ጉብኝት ከዕርዳታ ፈላጊዎቹ ጋር ተወያይቷል። በዚህ ወቅትም ያረጋገጠው ዕርዳታው ተቋርጧል በሚል የሚዘገበው ዘገባ ከዕውነት የራቀ መሆኑን ነው። የፌዴራል መንግሥት ቀደም ሲል የጀመረውን ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቋል። መንግሥት በእነዚህ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን ጠቅሶ በአሁኑ ወቅትም በእነዚሁ አካባቢዎች ምንም አዲስ የተከሰተ የጸጥታ ችግር እንዲሁም የተፈናቀለ ሰው አለመኖሩን አመልክቷል። ወደቀድሞ መንደሮቻቸው ተመልሰው ከነበሩ የጌዴኦ ማህበረሰቦች ውስጥ የተወሰኑት ምናልባት ጥቃት ሊፈጸምብን ይችላል በሚል ስጋት ወደ ካምፖቹ መመለሳቸውን አስታውሶ ሆኖም ግን ካምፖቹ አቅራቢያ የሚኖሩ ሌሎች የጌዴኦ የማህበረሰብ አባላት ዕርዳታ ለመካፈል በሚል ተመላሾቹን መቀላቀላቸው ተረጋግጧል። በዚህ ምክንያት በካምፖቹ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን መግለጫው አመልክቷል።
የፌዴራል መንግሥት የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከሁለቱ ክልሎች ጋር ከሚሠራቸው ሥራዎች ጎን ለጎን ለተመላሾች፣ መመለስ ላልፈለጉትም ሆነ ሌሎችም የዕለት የምግብ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በጊዜያዊነት ምግብና አስፈላጊውን አቅርቦት ሲያደርግላቸው መቆየቱን መግለጫው ጠቅሶ ይሄ ሥራ በቀጣይነትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
አብርሃም ተወልደ