አዲስ አበባ፦ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የፖሊስ አባላት ሲጋራ እና የተለያዩ ሱስ አስያዥ ነገሮችን እያስገቡ ይሸጣሉ የሚል ቅሬታ ቀረበባቸው።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና የፌዴራል ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በዚህ ህገወጥ ተግባር የተያዙ አባላት መኖራቸውን ገልጸዋል። በጎንደር ማረሚያ ቤት ለሦስት ወራት ታስሮ እንደነበር የሚናገረው ወጣት ዮሐንስ ጌታነህ፤ በእስር ቤቶች ውስጥ ሲጋራ እና የተለያዩ ሱስ አስያዥ ዕጾችን የሚያስገቡት የፖሊስ አባላት ናቸው። በተለይ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሠሩ እና መውጪያ መግቢያውን የሚያውቁ የፖሊስ አባላት እና አመራሮች ሲጋራ እያስገቡ ለታራሚው በድብቅ ይሸጣሉ።
እንደ ወጣት ዮሐንስ ገለጻ፤ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ሲጋራ፣ጫት እና የተለያዩ ሱስ አስያዥ ነገሮች የማይፈቀዱ በመሆኑ አቅራቢዎቹ በውድ ዋጋ ነው የሚሸጡት።ታራሚውን ላልተፈለገ ወጪ እና ለባሰ ሱስ እየዳረጉት በመሆኑ መንግስት ችግሩን መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ብሏል። ለስምንት ወራት ታራሚ ልጃቸውን ጥየቃ ወደ አዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መመላለሳቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አዳነች መላኩ በበኩላቸው፤በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገቡ ወጣቶች ሲጋራ እና ጫት በድብቅ የሚሸጡ የፖሊስ አባላት መኖራቸውን ከልጃቸው መረዳታቸውን ተናግረዋል።
በተለይ ከሱስ እንዲላቀቁ ተብለው ወደ ማገገሚያ ማዕከላት ጭምር የሚገቡ ታራሚዎች የባሰ ሱስ ውስጥ እንዲዘፈቁ የሚያደርግ ተግባር መኖሩ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል። እንደ ወይዘሮ አዳነች ገለጻ፣ ማንኛ ውም የታራሚ ቤተሰብ ወይም ጠያቂ ወደ ማረሚያ ቤቶች ሲገባ በአግባቡ ተፈትሾና ምግብ ተቀምሶ ነው የሚያልፈው። በመሆኑም ከጠያቂዎች ነው ሲጋራ እና ጫት የሚያገኙት ብሎ መገመት አይቻልምና አስፈላጊውን ቁጥጥርና የእርምት ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል። የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የስነምግባር መከታተያ ጽህፈት ቤት ሐላፊ አቶ የሺበላይ ኃይለመስቀል እንደገለጹት፤ ወደማረሚያ ቤት እንዳይገቡ የተከለከሉ ሲጋራና የተለያዩ ዕጾችን ፖሊሶች ይዘው ስለመግባታቸው የሚያሳይ ጥናት የለም።
ይሁንና ሲጋራ እና የማይፈቀዱ ነገሮችን ይዘው ከሚገቡት መካከል ፖሊሶች ተጠርጣሪ መሆናቸው አይቀርም። ከሁለት ዓመት በፊት በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት በሸሚዝ ኮሌታው ስር ሲጋራ ይዞ ሊገባ ሲል ተደርሶበት አስፈላጊው የዲሲፕሊን ዕርምጃ የተወሰደበት አንድ የፖሊስ አባል እንደነበር አስታውሰዋል። እንደ አቶ የሺበላይ ገለጻ፣ በድሬዳዋ ማረሚያ ቤት «ቡሪ» የሚባል ትንባሆ የመሰለ ተክል ከዚህ ቀደም ይገባ ነበር። አሁን ግን ቡሪም ይሁን ጫት እንዳይገባ ተከልክሏል።
በተመሳሳይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያልተፈቀዱ ነገሮች እንዳይገቡ በፖሊስ አባላትም ሆነ ጠያቂዎች ከፍተኛ ፍተሻ ይደረጋል። በሌላ በኩል በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ለእርሻ ልማት ሥራ የሚሰማሩ ታራሚዎች በእርሻ ላይ የሚያገኙትን የትንባሆ ቅጠል እንደሚይዙ ይታመናል። ከእርሻ ሥራ መልስ የሚደረግ ፍተሻ ቢኖርም አያልፍም ብሎ መደምደም እንደሚያስቸግር ተናግረዋል።
የፌዴራል ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት አስተዳዳሪ ኮማንደር ተክሉ ለታ በበኩላቸው፤ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በዘንድሮው ዓመት ሁለት የማረሚያ ቤት ፖሊስ አካላት ሲጋራ ሲያስተላልፉ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው አስፈላጊው የህግ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሦስት የህግ አካላት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ጥርጣሬ በመፈጠሩ ከቦታው እንዲነሱ ተደርጓል። እንደ ኮማንደር ተክሉ፤ ስነምግባር የጎደላቸው የማረሚያ ቤት አባላት ለታራሚ የማይፈቀዱ ነገሮችን በጥቅም በመደለል ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ይታመናል። በመሆኑም ሲጋራም ሆነ ማንኛውም የማይፈቀድ ነገር ወደ ታራሚዎች እንዳይደርስ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011
በጌትነት ተስፋማርያም