ሐዋሳ፡- በብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እና ኤልሻዳይ በተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ጥምረት ከጎዳና ተነስተን በተለያዩ ሙያዎች ብንሰለጥንም ተመልሰን ወደ ጎዳና ሕይወት እንድንገባ እየተገደድን ነው ሲሉ በሃዋሳ በአንድ መጋዘን ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ተናገሩ።
ቅሬታቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የገለጹት ወጣቶቹ፤ በአፋር ክልል ሰርዶ የተቀናጀ የግብርና ልማት ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠና ተሰጥቷቸው በሃዋሳ የተሰባሰቡ ናቸው። ላለፉት አራት ዓመታት ቤትና ንብረት አፍርተንና ሕይወት ከጀመርንበት ቦታ መፈናቀላችን ተገቢ አይደለም ብለዋል። እንደ አገር ሜቴክ በፈጠረው ቀውስ እኛም ሰላባ ሆነናል ያሉት ሰልጣኞቹ፤ በተወለዳችሁበት አካባቢ ተደራጅታችሁ ትሠራላችሁ በሚል ሰበብ ከነበርንበት ቦታ የገነባነውን ቤት ካሳ ሳንወስድና የልፋታችን ዋጋ በአግባቡ ሳይከፈለን ተበትነናል፡ ፡
በተለይም 4 ሺ 400 ሄክታር መሬት መንጥረን ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ ሽንኩርትና ቲማቲም እያለማንና ከብት እያደለብን ነበር ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በስልጠናው የከባድ መኪኖች አሽከርካሪነት፣ የብየዳ፣ የኤሌክትሪክ ሥራ እና በሌሎች ሙያዎች ሰልጥነው መመረቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የወጣቶቹ ተወካዮች፤ በአንድ መጋዘን ውስጥ 180 ሆነው በመታጎራቸውን በመተፋፈግ ለከፋ በሽታ እንዳይጋለጡ ስጋታቸውን ጠቁመዋል፡ ፡ ከዚህም ባሻገር ከተማ አስተዳደሩ ከሚያደርጋቸው 15 ኪሎ ስንዴ ድጋፍና የዘይት ዕርዳታ ውጪ ቃል የተገባላቸው 60ሺ ብር እንዳልተሰጣቸውና ተደራጅተው ሥራ እንዳልጀመሩ አስገንዝበዋል፡፡
የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የርዕሰ መስተዳድር ፅህፈት ቤት፤ ከግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር በቁጥር 13/17/06/02/11 ጥቅምት 23 ቀን 2011 ዓ.ም የተፃፈን ደብዳቤ ዋቢ በማድረግ ለሲዳማ ዞን እና ለሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ፅህፈት ቤት በፃፈው ደብዳቤ፤ «በአፋር ክልል ሰርዶ የተቀናጀ የግብርና ልማት ማሰልጠኛ ስር የነበሩ ወጣቶች ወደ ክልላችን ተመልሰው በሥራ ዕድል ፈጠራ ሥርዓት በመታቀፍ የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሰልጣኞችን ዝርዝርና የሰለጠኑበት ሙያ መስክ ጨምሮ የላከ ሲሆን፤ ወጣቶቹ ወደ የአካባቢያቸው ተመልሰው በመደራጀትና የቢዝነስ ፕላን በማዘጋጀት ቋሚ የሥራ ሥምሪት እስኪያገኙ፤ ወደተፈለገው መስክ ገብተው እራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ አምስት ወር ሊጠይቅ እንደሚችል ታሳቢ ተደርጎ የመቋቋሚያ ገንዘብ ከመስከረም እስከ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ተሰልቶ በጀቱ በብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር በኩል ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን ገልፆልናል፡፡
«በመሆኑም ቀደም ሲል ከዞናችሁ የወጡና ወደዚያው ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑ በድምሩ 125 ወጣቶች ዝርዝር ከዚህ ደብዳቤ ጋር አባሪ ተደርጎ መላኩን እየገለፅን ሚኒስቴሩ በሥራ ዕድል ፈጠራው መርሐ ግብር እንዲውል በፌዴራል ደረጃ ከተያዘው ተዘዋዋሪ ፈንድ የብድሩን ገንዘብ ለእያንዳንዱ ሰልጣኝ 60ሺ ብር ሂሳብ እንዲያወራርድላቸውና በክልሎች የብድር አሰጣጥ ህግና አሠራር መሠረት እንዲጠቀሙ ይደረግ ሲል በገንዘብ ሚኒስቴር በቁጥር 13/36/08/98 ህዳር 04 ቀን 2011 ዓ.ም በአድራሻ ፅፎ በግልባጩ የደረሰን ሲሆን፤ ይህም የመንግሥትን አሠራር ጠብቆ በቀጣይ ፋ/ኢ/ል ቢሮ በኩል ወደ ዞናችሁ ለተላኩ ወጣቶች የሥራ ስምሪትና የመጠለያ ድጋፍ እንዲውል የሚደረግ ይሆናል፡፡
የክልላችን ፋ/ኢ/ል ቢሮም በ598 ሰልጣኞች ብዛት ተሰልቶ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሚወርደውን ተዘዋዋሪ ፈንድ ተከታትሎ ወጣቶቹ ወደተላኩባቸው ዞኖች፣ ሐዋሳ ከተማና ልዩ ወረዳዎች እንዲያስተላልፍ የዚህ ደብዳቤ ግልባጭ ተመዝግቦለታል›› ሲል ህዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ደብዳቤ ጽፏል፡፡ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ሹካሬ ሹዳ በበኩላቸው፤ ወጣቶቹ በከተማ ውስጥ መኖራቸውን ጠቁመው ሠብዓዊ ፍጡር በመሆናቸው ላለፉት ጥቂት ወራት 250 ሺ ብር ለቀለብ ተበጅቶላቸው በአንድ ሥፍራ እንዲቆዩ መደረጉን አስታውቀዋል፡ ፡
ችግሩ የተፈጠረው ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ያሉና የሚመለከታቸው አካላት የቤት ሥራቸውን ባለመወጣታቸው የተነሳ እንጂ ከተማ አስተዳደሩ ችግር እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም ወጣቶቹ ህጋዊ መስፈርቶቹን አሟልተውና ተደራጅተው ከመጡ አስፈላጊ ትብብር እንደሚደረግ ገልጸው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመሥራት ከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የክልሉን ሠራተኛ ማህበራዊ ቢሮ በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ሜቴክ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ማጓተት እና የጥራት መጓደል ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ በሀገር ላይ ያስከተለ እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት አዲስ ዘመን ጋዜጣ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር