አዲስ አበባ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች አሰራርን ለማሻሻል የፈረሙትን የቃል ኪዳን ሰነድ ተግባራዊነት ቃላቸውን ጠብቀው እንደሚሰሩ አስታወቁ፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያነጋገራቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳስታወቁት፤ የቃል ኪዳን ሰነዱ መፈረም በፓርቲዎች መካከል የነበረውን ግንኙነት ከማሻሻል ባሻገር በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ተግተው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ «ሰነዱ ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች በመቀራረብ ወጥ የሆነ አሰራር ዘርግተው ሰላማዊ በሆነ መንገድ የፖለቲካ ግቦቻቸውን እንዲያሳኩ መደላደል ይፈጥራል» ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ገዢው ፓርቲ እንደ መንግስት በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ሲያደርስ የነበረው አፈና እና መፈናቀል ለማረምና ሁሉንም በእኩል ደረጃ ተሳታፊ ሊያደርግ የሚችል አሰራር ውስጥ እንዲገቡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል፡፡ «አሁን አገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የምናራምደው ፖለቲካ ህግን የተከተለ፣ ሰላምን የሚያረጋግጥ፣ በህዝቦች መካከል ወንድማማችነትን የሚያሰፍን፣ ለአገር አንድነት እንቅፋት በማይሆን መልኩ በሰለጠነ መንገድ ፖለቲካችንን እንድናራምድ ያግዛል» ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ ፓርቲያቸው የቃል ኪዳን ሰነዱ ድምር ውጤት ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር የተዘጋጀ ማዕቀፍ አድርጎ እንደሚወስደውም ጠቁመዋል፡፡
ሰላም የሁሉም ነገር ማጠንጠኛ መሆኑን የሚገነዘብ በመሆኑም ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ «የምንታገልለት የአማራ ህዝብ ከተደቀነበት የህልውና አደጋ መውጣት የሚችለው ሰላም ሲረጋገጥ መሆኑን ስለምንረዳና ሰነዱ አገርን ከብተና የማዳን አላማ ያለው ስለሆነ፤ ቃላችንን በተግባር ለማሳየት ዝግጁ ነን» ብለዋል፡፡ ሰነዱ በተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ የመንግስትን መዋቅር ተጠቅመው መንግስታዊ ስልጣንን የያዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመንጋ ፍርድ የሚያሰጡ አካላት አላስፈላጊ ተፅእኖ ከመፍጠር እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡
መንግስትም በተለየ መልኩ ህግን የማስከበር ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢህአን) ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤ ከትናንት በስቲያ በፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈረመው ሰነድ በሁሉም አካላት ሙሉ ፈቃደኝነት እንጂ እንደከዚህ ቀደሙ በመንግስት ተፅእኖ አይደለም። በመሆኑም ለተፈፃሚነቱ እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ «በነፃ ፍላጎታችን ላይ የተመሰረተና ሁላችንም በእኩል ደረጃ ተሳትፈንበት የዳበረ በመሆኑ የራሳችን ሰነድ እንደሆነ ነው የምንቆጥረው፡፡
ስለዚህም ያለማንም ጎትጓችነት ስራ ላይ እንዲውል እንተጋለን» ብለዋል፡፡ በሰነዱ ላይ በውጭ የነበሩና በትጥቅ ትግል የሚያምኑ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ተቀራርበው ለመነጋገር እድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም የአንዳንድ ፓርቲዎች አባላት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተለያየ አካባቢዎች የሚያደርጉትን ትንኮሳና የሰላም ማደፍረስ እንቅስቃሴ ለመግታት እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡ «በዚህች አገር ስምምነት መፈፀም ሳይሆን ትልቁ ችግር ሆኖ የቆየው ስምምነቱን በተግባር መተርጎሙ ነው» በማለት ስጋታቸውን የገለፁት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ናቸው፡፡
እንደእርሳቸው እምነት ስምምነቱን በተጨባጭ ስራ ላይ ማዋል ከተቻለ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ጭምር ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ዶክተር መረራ፤ ሰነዱ ፓርቲዎች ከመዘላለፍና ከመወቃቀስ ነፃ በሆነ መልኩ አደብ ገዝተው ለመንቀሳቀስ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የራሳቸውን የቤት ስራ የሚሰሩበትን ሁኔታ መሬት ላይ ያስቀመጠ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ለስምምነቱ ተግባራዊነት ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ህዝቡን ማደራጀትና መንቀሳቀስ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ በዚህ ረገድም ፓርቲያቸው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የአገሪቱን ህግና ስርዓት በማክበር ለአገር ሰላም እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011
በማህሌት አብዱል