አዲስ አበባ፡- ከሞቱ ሰዎች ኩላሊት በመውሰድ ንቅለ ተከላ ለማካሄድ የሚያስችለው የህግ ማዕቀፍ ፀድቆ ስራ ላይ አለመዋሉ የኩላሊት ታማሚዎችን ለከፋ ችግር እየዳረገ መሆኑን የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ከሞቱ ሰዎች ኩላሊት በመውሰድ ንቅለ ተከላ ለማካሄድ የሚያስችለው የህግ ማዕቀፍ ከዓመት በፊት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢቀርብም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታን አግኝቶ እስካሁን ስራ ላይ አልዋለም፡፡
ይህም ቤተሰብ የሌላቸውና ቢኖራቸውም ከኩላሊት ለጋሽ በኩል በሚኖሩ ያልተስተካከሉ የጤና ችግሮችና ልዩ ልዩ ምክንያቶቸ ኩላሊት ማግኘት የማይችሉ ታማሚ ዎችን ለከፋ ችግር ዳርጓል፡፡ እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ፤ በሃገሪቱ በተከታታይ የኩላሊት እጥበት የሚያደርጉ በርካታ ሰዎች ቢኖሩም የህግ ማዕቀፉ በቶሎ ፀድቆ ስራ ላይ ባለመዋሉ ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገዋል፡፡ የኩላሊት እጥበት ለማ ድረግ የሚያስችል አቅም የሌላቸው ታማሚዎችም ልመና ውስጥ ገብተ ዋል፡፡ በዋናነትም በሃገሪቱ ህግ መሰረት ኩላሊት መለገስ የሚቻለው በቤተሰብ ብቻ በመሆኑ ከሌሎች ሰዎች ኩላሊት የማግኘት እድላቸው ጠቧል፡፡
አሁን ባለው መረጃ ከ676 ኩላሊት ህመምተች ውስጥ አብዛኞቹ ዕድሚያቸው ከ50 ዓመት በታች በመሆናቸው ሁሉም የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡ የህግ ማዕቀፉ ፀድቆ በቶሎ ስራ ላይ እንዲውል በድርጅቱና በጤና ሚኒስቴር በኩል ግፊት እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፤ ከአምስት ወራት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ እንዲሁም ለፕሬዚዳንቷ በድጋሚ ደብዳቤ መፃ ፉንም አስታውሰዋል፡፡
የህግ ማዕቀፉ ለኩላሊት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሊቀየሩ የሚችሉ የሰውነት አካላትንም በማካተት ወጥ በሆነ መልኩ እንዲዘጋጅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ስራ አስኪያጁ አያይዘው ጠቁመዋል። ከሞቱ ሰዎች ኩላሊት በመውሰድ ንቅለ ተከላ ለማካሄድ የሚያስችለው የህግ ማዕቀፍ ፀድቆ ስራ ላይ መዋል የሚችል ከሆነ በኩላሊት እጦት ሲሰቃዩ የነበሩ ታማሚዎችን ችግር እንደሚቀርፍና የሰዎች ኩላሊትን የማግኘት እድል በእጅጉ እንደሚያሰፋው ገልፀዋል፡፡ የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ከሰባት ዓመት በፊት ከተቋቋመ ወዲህ ለ676 ህሙማን የኩላሊት እጥበት ወጫቸውን ሙሉ በሙሉ በመሸፈን ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011
አስናቀ ፀጋዬ