አስመራ ከተማ የተወለዱት ዶክተር ፋሲል ናሆም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ በማዕረግ አግኝተዋል፡፡ አሜሪካ በሚገኘው የይል ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤትም ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ እኝህ አንጋፋ የህገ መንግስት ምሁር ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ጋርም አብረው ተምረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ10 ዓመት በላይ በመምህርነት፣ በተመራማሪነት፣ በዲንነትና በሕግ አማካሪነት አገልግለዋል፡፡ ሁለት የተለያዩ መጽሐፎችንና ሙያዊ መጣጥፎችን ጽፈዋል፡፡ ከአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ ድረስ ሶስት የተለያዩ መንግስታት የህግ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ጡረታ ከወጡ አንድ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባል ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ኑሮዬ በሙሉ ከህገ መንግስት ጋር የተያያዘ ነው ከሚሉት ዶክተር ፋሲል ጋር በህገ መንግስቱ መሻሻል አስፈላጊነት፣ በተለያዩ ወቅታዊና በማማከር ስራቸው ዙሪያ ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸዋል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ለረጅም ዓመታት ሶስት ለተለያዩ መንግስታት የህግ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ መሪዎች በኩል የታዩ ክፍተቶች ምን ምን ናቸው?
ዶክተር ፋሲል፡- አምላክ ጤንነቱን ፣ጉልበቱንና ችሎታውን ሰጥቶኝ በተቻለኝ መጠን ህዝቤን ለማገልገል ሞክሬያለሁ፡፡ መንግስታት ይፈራረቃሉ፡፡ እኔም በአጼ ሀይለስላሴ ዘመን ገና ወጣት ተመራማሪና አስተማሪ ነበርኩ፡፡ ወደ መጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው ህግ መንግስቱ መሻሻል አለበት የሚል የህዝብ ግፊት ስለነበረ ከዚህ በመነሳት ቀዳማዊ አጼ ሀይለስላሴ በህገ መንግስት ንጉሰ ነገስቱ የስርዓቱ የበላይ ታዛቢ ሆነው ነገር ግን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር በጃፓን፣ በእንግሊዝና በተለያዩ ስካንዲቪያ አገሮች የሚታየው አይነት ስርዓት ለማምጣት ጥረት የተደረገበት ዘመን ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ እኔ ወጣት አስተማሪና ተመራማሪ ነኝ፡፡ በህገ መንግስቱ ዙሪያ 30 ሰዎች በአባልነት የያዘ ኮሚሽን ተቋቁሞ ይህንን በሚሰራበት ጊዜ የማማከር፣የማርቀቅ ስራዎችን ሰርቻለሁ፡፡ ሆኖም ያ ህገ መንግስት ሳይሳካ ደርግ ስልጣኑን ያዘ፡፡
አዲስ ዘመን፡-ለምን አልተሳካም ?
ዶክተር ፋሲል፡- ወዲያው ወታደራዊ መንግስት ስልጣን በመያዙ ነው፡፡ ደርግ ደግሞ አገሪቱን ያለ ህገ መንግስት 13 ዓመታትን ገዝቷል፡፡ ሆኖም ደርግ በመጨረሻ የስልጣን ዘመኑ ህገ መንግስት ቢኖረኝ ይጠቅመኛል የሚል ሃሳብ አነሳ፡፡ እኔ በዚያ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ነበርኩ፡፡ በኋላ የደርግ ህገ መንግስት እንዲረቀቅ ብዙ ሰዎች የተሳተፉበት ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም የበኩሌን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ ሆኖም ህገ መንግስቱ ስራ ላይ ውሏል ማለት አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በምን ምክንያት?
ዶክተር ፋሲል፡- ዘመኑ የእርስ በርስ ጦርነት የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ እንዲሁም ደርግም ቢሆን ህገ መንግስቱን ስራ ላይ ለማዋል ፍላጎት አለው ተብሎ የሚታመን መንግስት አልነበረም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢህአዴግ ዘመንስ ህገ መንግስት ሲረቀቅ ተሳትፈዋል ወይ?
ዶክተር ፋሲል፡- ኢህአዴግ አገሪቱን እንደተቆጣጠረ ሁለት ኃላፊነቶች ከፊቱ እንደነበሩበት ማየት ይቻላል፡፡ አንዱ ወቅታዊ የሆነው አገሪቱን ሰላም የማረጋጋት ሲሆን ሁለተኛው በጊዜያዊው የሽግግር መንግስት ለረጅም ጊዜ ምን አይነት አስተዳደራዊ ስርዓት ነው የሚያስፈልጋት የሚለው መመለስ ነው፡፡ በመጨረሻም የህገ መንግስት ረቂቅ ተዘጋጅቶ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት በጸደቀው ህግ መንግስት ተካፍያለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን የነገሩኝ በህገ መንግስቶች ማርቀቅ መሳተፍዎን ነው መንግስታቶቹን በቀጥታ አማክረዋል?
ዶክተር ፋሲል፡- አዎ አማክሬያለሁ፡፡ ማማከር ማለት የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል ነው፡፡ እኔ በመሰረቱ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፡፡ እኔ የሙያ ሰው ነኝ፡፡ እና ሙያዊ የሆነ ምክር በተለይ ህገ መንግስትን በተመለከተ ህገ መንግስታዊ ስርዓትን ከማስፈን አንጻር አዎ ሶስቱንም የአፄ ኃይለስላሴ፣ የደርግንና የኢህአዴግን መንግስታት ሳማክር ቆይቻለሁ፡፡ የማማክረው ግን ከህገ መንግስት አንጻር ነው፡፡ ህገ መንግስት በምልበት ጊዜ በእኔ እምነት መንግስት የህዝብን መብት ከመጠበቅ እና ከማስጠበቅ ሌላ ኃላፊነት የለበትም፡፡
የማንኛውም መንግስት ትልቁ ዋናው መሰረታዊው ኃላፊነት ሰብዓዊ መብትን ማክበርና ማስከበር ነው፡፡ የህዝቡን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ደህንነቱንና መብቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት እና ከዚህ አንጻር ምንድን ነው መሰራት ያለበት የሚለውን ለማማከር ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ በኢህአዴግ ዘመንም እንዲሁ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ሚኒስትር ሆኜ ለ27 ዓመታት ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከአማከሯቸው መንግስታት መካከል ምክርዎትን ተጠቅመው ውጤታማ ስራ ሰርተዋል ማለት ይቻላል?
ዶክተር ፋሲል፡- የመንግስት ስራ በጣም ሰፊና ውስብስብ ነው፡፡ የእኔን ምክር መንግስት እየተቀበለ ስራ ላይ ሲያውል ቆይቷል ለሚለው ጥያቄ በብዙ መልኩ አዎ፡፡ በተሟላ መልኩ ግን ላይሆን ይችላል፡፡ ግን የምሰጠው ምክር እንደዚሁ ወደ ጎን ተጥሎ የሚገኘ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ሆኖም ከጊዜ አንጻር በተሟላና በተፈለገው መልኩ ወዲያውኑ ተግባራዊ አድርገዋል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፖለቲካው አንዱ ነገር ነው፡፡ ክህሎት፣ አፈጻጸም፣ ገንዘብና የመሳሳሉ ነገሮች የመንግስት መሰረታዊ ችግሮች ሆነው የሚታዩት ግን ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሶስት መንግስታት የህግ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ምክርዎትን አልቀበል የሚል መሪ አጋጥመዎት ይሆን?
ዶክተር ፋሲል፡- እኔ ሙያዊ ምክር ነው ስሰጥ የቆየሁት፡፡ ሙያዊ ምክሩ ተቀባይነት አገኘ ወይም አላገኝም ወይ የሚለው በመሪዎቹ የሚወሰን ነው፡፡ ምክንያቱም ምክር ከሰጠህ በኋላ በግድ መፈጸም አለበት ብዬ የማስገድድበት ሁኔታ የለም፡፡ ምክር አሰጣጡ ደግሞ ከሚመጡ ፋይሎች አንጻር ነው፡፡ በእነዚህ ፋይሎች ህገ መንግስታዊ ዕይታዬን ነው የማሰፍርበት፡፡ በአጭር ጊዜ ጥቅም እንዲገኝባቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለረጅም ጊዜ የሚበጀው ምንድን ነው ከሚል ነው ሰፋ ባለ መንገድ ሳማክር የቆየሁት፡፡
የአጼ ኃይለስላሴ መንግስትን የመጨረሻ ዘመን አካባቢ ነው ያማከርኩት፡፡ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሁኜ ሳማክር የነበርኩት የምክር አሰጣጡም ውስን ነው፡፡ ለምሳሌ በመጨረሻ ዓመታት አካባቢ ለአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ማንኛውንም ሰው ምክንያት ሳይሰጥ ለሶስት ወር ሊያስር ይችላል የሚል ስልጣን የሚሰጥ አዋጅ ወጥቶ ነበር ፡፡ ይህ አዋጅ ሶስት ወሩ ካለቃ በኋላ ደግሞ ለሚቀጥሉት አራት ወራት እንደገና ምክንያት ሳይሰጥ ሊያስር ይችላል ይላል ፡፡
ይህ አዋጅ ህገ መንግስታዊ አይደለም፡፡ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በምክንያት አንድን ሰው በቁጥጥር ስር ሊያውል ይችላል፡፡ በ48 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ፍርድ ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ ይህ መሰረታዊ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ምክንያት ግን ለሶስት ወር ሲቀጥል ለአራት ወራት ማሰር ህገ መንግስታዊ አይደለም በሚል ሃሳብ አቅርቤ ውይይት ተካሂዶበት ተገቢ አለመሆኑ ታምኖበታል፡፡
የደርግ ጊዜ አስተማሪ ነበርኩ፡፡ አራትና አምስት ዓመት ሲቀረው ነው ህገ መንግስት ቀረጻ ለመግባት የተገደደው፡፡ በዚህ ጊዜ ህገ መንግስት አስፈላጊነት ዙሪያ ውይይት የተደረገበት ዘመን ነው፡፡ ከቀይ ሽብር በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ለእኔ በዛ ዘመን ህገ መንግስት ጥያቄዎች መነሳታቸው እሰየው ነው፡፡ ምክንያቱም ከዛ በፊት ብዙ የሰብዓዊ መብት ረገጣና ጭፍጨፋ የተካሄደበት ነው፡፡ የደርግ ህገ መንግስት ስራ ላይ ውሏል ማለት አልችልም፡፡
በኢህአዴግ ዘመን ነው ከአፈጻጸም አንጻር ብዙ ነገር መስራት ተችሏል የምለው፡፡ ማንኛውም መንግስት ወደ ኋላ ተሄዶ ሲታይ ጥንካሬውና ድክመቱን ዘርዝሮ ማየት ይቻላል፡፡ እናም የኢህአዴግ ጥንካሬ ከደርግ ውድቀት በኋላ ህገ መንግስት ያስፈልጋል ብሎ መነሳቱና ይህን ህገ መንግስት በተቻለ መጠን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከሩ ነው፡፡ ኢህአዴግ በራሱ አመለካከት ነው ሲሄድበት የነበረው የሚለው ትክክል ነው፡፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር የጀመረው የአብዛኛውን ገጠር ህዝብ አመለካከት ይዞ ነው፡፡ ኢህአዴግ ዲሞክራቲክ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ግን ዴሞክራሲ ስራ ላይ መዋል አለበት ብሎ የሚያምን አካል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በደርግም ጊዜ ይሁን በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ታይቷል፡፡ በህገ መንግስቱ የሰብዓዊ መብት ማክበርና ማስከበር መሰረታዊ መርሆዎች ሆነው ሳለ ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸሙ ምን ይሰማዎታል?
ዶክተር ፋሲል፡- በጣም ያሳዝነኛል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኢ ህገ መንግስታዊና ኢ ሰብዓዊ ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ባህልና አስተሳሰብ ያፈነገጠም ጭምር ነው፡፡ ይህ ድርጊት ወንጀል ብቻ ሳይሆን እንስሳነትም ነው፡፡ ሰብዓዊነት በጎደለው ተግባር በማንኛውም መንግስት ሲፈጸም ፈጽሞ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም፡፡
የህገ መንግስቱ መሰረታዊ ትምህርት ሰብአዊ መብት ማክበር ነው፡፡ እናም በአገራችን ሲፈጸም የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሃይማኖት፣ከህገ መንግስትም አንጻር መወገዝ ያለበት ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ ይህ አይነቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም የሚያስፈልገውን ሁሉ ስራ መሰራት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የህግ የበላይነት የለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ዶክተር ፋሲል፡- የህግ የበላይነት በምንልበት ጊዜ ሂደት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዘመን የተሻለ የህግ የበላይነት አሰራር አለ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ግን የህግ የበላይነት ፈጽሞ የለም የሚባልበት ሁኔታ የለም፡፡ የህግ የበላይነት አለ በምንልበት ጊዜ ጥሰቶች ካለ መንግስት መጀመሪያ እንዳይፈጸሙ ከተፈጸሙ ደግሞ በአስቸኳይ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ መንግስት ፖሊሲ፣ፍርድ ቤት፣አቃቤ ህግና ማረሚያ ቤቶች ተቋማትን ያዋቀረው የህግ ልዕልናን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሁልጊዜ በየትም አካባቢ የህግ ልዕልና በተሟላ መልኩ አለ የሚባልበት ሁኔታ የለም፡፡
እንግዲህ በህብረተሰቡ ውስጥ የተለያዩ ቡድኖች የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እነዚህ ቡድኖች በሌሎች ላይ ፍላጎታቸውን ለመጫን ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህ ሳይሳካ ሲቀር ኃይል የመጠቀም ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ነው የህግ ልዕልና መኖር ያለበት፡፡ ሁላችንም ሃሳባችንን በሰላም ገልጸን በዴሞክራሲዊ መንገድ ብዙኃኑ የሚለውን ሃሳብ በስራ እየተረጎምን የመሄድ ጉዳይ ሊኖር ይገባል፡፡ በዚህ መልክ ነው የህግ ልዕልና ሊከበር የሚገባው፡፡
የህግ ልዕልና ሲባል ህገ መንግስቱ መከበር ይኖርበታል፡፡ ህገ መንግስቱን የሚያከብረው ደግሞ ህዝብም መንግስትም ነው፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር፡፡ ከዚህ በመነሳት ህገ መንግስቱን ተከትለው የሚወጡ የተለያዩ ህጎች፣ደንቦችና መመሪያዎች ስራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው የግለሰብና የህዝብ ነጻነት ለማክበር፣ለማስከበር ጭምር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ እርስዎ ይህን ሃሳብ ይጋሩት ይሆን?
ዶክተር ፋሲል፡- ህገ መንግስት የእግዜአብሄር ቃል አይደለም፡፡ ህዝብ ይህ ይሻለናል የሚላቸው ሃሳቦች ያሉበት ሰነድና እናት ህግ ነው፡፡ እናም በየዘመኑ አሰራሩን አይቶ ዛሬ በደረስንበት ደረጃ በዚህ መልክ ከምንሰራ በዚህኛው መልክ ይሻላል ብሎ ማሰቡ ጠቀሜታ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስታችን መሰረታዊ ግቦችን የያዘ ነው፡፡ አንደኛ ሰላም ፣ሁለተኛ ዴሞክራሲና ሶስተኛ ደግሞ ልማት ናቸው፡፡
እኔ እነዚህ ግቦች የሉም የሚል ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ በታቻለ መጠን ዴሞክራሲን እያሰፋንና እያስፋፋን በሌላ በኩል ደግሞ ከድህነት መውጣት ብቻ ሳይሆን ፈጣን ልማታችንን በማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተደላደለ ኑሮ መኖር የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚል ነው፡፡ እናም እነዚህ ግቦች መለወጥ አለባቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡
ህገ መንግስቱ ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላ እንደገና ውስጡን መፈተሽና እኛ ዛሬ ከደረስንበት ሁኔታ ምን ማሻሻል እንችላለን ብሎ መነሳቱ ጠቀሜታ ያለው ይመስለኛል፡፡ እናም ህገ መንግስታት በየጊዜው ይሻሻላሉ፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ ፈጽሞ ባይለወጥም ማሻሻል ግን ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ለምሳሌ ህገ መንግስቱ ፌዴራላዊ ስርዓት የሚያቋቁምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስራ ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው፡፡ ከቅርጽ አንጻር ፌዴራላዊ ሆኖ መቀጠሉ፣መሰረታዊ አሰራሮችን ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ማድረጉ መለወጥ አለበት አልልም፡፡
አዲስ ዘመን፡-መሻሻል አለባቸው የሚሏቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው ?
ዶክተር ፋሲል፡- ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የምርጫ ስርዓቱ አሁን ከአለው አብላጫ አሰራር ወደ ተመጣጠነ( ፕሮፖርሽናል) ውክልና ቢሄድ ይሻላል የሚለው እኔ የምቀበለው ነው፡፡ እንዲሁም በክልልና በማዕከላዊ መንግስት መካከል ያለው የስልጣን ክፍፍሉ ምን ይምሰል የሚለው እንደገና አይቶ በዚህ መልክ ቢሻሻል ቢባል ችግር የለውም፡፡ እናም አንዳንድ የሚሻሻሉ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ እኔም ይታየኛል፡፡ ሆኖም መሰረታዊ የሚባሉት ነገሮቹ ግን መለወጥ አለባቸው የሚል እምነት የለኝም ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የክልል አከላለል ቋንቋና ባህል ላይ ብቻ ማተኮሩ አገሪቱ ላይ ብሄር ተኮር ግጭት እንዲበራከት አድርጓል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ፋሲል፡- መንግስትን በምን መልክ እናዋቅረው የሚል ጥያቄ ሲነሳ አሃዳዊ መንግስት ወይንስ ፌዴራላዊ መንግስት እናድርገው የሚሏቸው ምርጫዎች አሉ፡፡ እንዲሁም አጼያዊ መንግስት ወይስ ሪፐብሊካዊ መንግስት እናድርገው የሚሉት በተለያየ ደረጃ ውይይት ሊካሄድባቸው የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሆኖም የአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታውስ ምን ይመስላል የሚለው መገንዘብ ያሻል፡፡
እኛ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ነው የምንፈልገው፡፡ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል በምን መልኩ ነው አስተዳደሩን ማዋቀር ያለብን? እኔ ዛሬ ባለንበት ሁኔታ ከፌዴራል ስርዓት መውጣት የምንችል አይመስለኝም፡፡ ከአሃዳዊ መንግስት ይልቅ ፌዴራላዊ ስርዓት ይሻላል፡፡ ፌዴራላዊ ስርዓት ስንል በመሰረቱ ያልተማከለ አሰራር ስራ ላይ ማዋል ነው፡፡ ክልሎቹም በህገ መንግስቱ እውቅና የሚያገኙ የተወሰነ ስልጣን በህገ መንግስት ደረጃ የሚሰጣቸው ወይም ያላቸው ክልሎች ስንት ይሁኑ? እነማን ይሁኑ? በምን መስፈርት ይከለሉ? የሚሏቸው ሌላ ጥያቄ ይነሳል፡፡
ስለዚህ የተወሰኑ ሰዎች የሆነ ነገር ሊሉ ይችላሉ፤ሌሎቹ ደግሞ ሌላ ነገር ሊሉ ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ የህዝቡ አብላጫ አስተሳሰብ ምንድን ነው የሚለው ነገር ወደ ውሳኔ ህዝብ የመሄዱ ጉዳይ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ሃይማኖቶች ያሏት አገር ነች፡፡100 ሚሊዮን ህዝብ አለን፡፡
ይህን ህዝብ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ፈጣን ልማት እየተረጋገጠ በሄደበት ሁኔታና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የተደላደለ ኑሮ እንዲኖር የሚችልበት ስርዓት እንዴት ነው የምንፈጥረው በምንልበት ጊዜ ቋንቋዎቹን፣ ባህሎቹን፣ ሃይማኖቶቹን ምን እናድርጋቸው፡፡ የመልካም ስነ ምህዳር አቀማመጡና ከተሞቹንም በታሳቢነት ይዞ የማየቱ ጉዳይ ይሆናል፡፡ በተለያየ ዘመን ኢትዮጵያ በተለያየ መልክ ነው ስትተዳደር የቆየችው፡፡
ለምሳሌ ያህል በአጼ ምኒልክ ዘመን የኢትዮጵያ አስተዳደር አሃዳዊ ሆኖ አከፋፋሉ ምን ይመስል ነበር፡፡ ጣሊያንስ ኢትዮጵያን 5 ዓመት ለአስተዳደር እንዲመቸው እንዴት ከፍሏት ነበር፣ የደርግ አከፋፈል? እነዚህን ሁሉ በታሳቢነት ይዞ የሚበጀን ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡
ፌዴራሊዝም የራሱ የሆነ ለችግር ሊያጋልጥ የሚችል ስርዓት አድርገው የሚያዩ ሰዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መፍትሄው ፌዴራሊዝም ነው ሌላ አማራጭ የለም ብለው ደግሞ በጽኑ የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ቁጭ ብለው ተወያይተው አንድ ሊያሰራ የሚችል ሃሳብ ላይ መድረሱ በግድ አስፈላጊ ነው የሚሆነው፡፡ እና በቀላሉ የሚታይና ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረገን ፌዴራሊዝም ነው ብሎ መነሳቱ እኔ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ፌዴራሊዝም መፍትሄዎችን ነው ይዞ የሚመጣው፡፡
ሌላው ነገር መታየት ያለበት መሰረተ ሃሳቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አፈጻጸሙን ነው፡፡ እናም ጥሩ መሰረተ ሃሳብ ይዞ ብልሹ የሆነ አፈጻጸም ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ችግራችን አፈጻጸም ወይስ አመለካከት የሚለው ግንዛቤ ተይዞበት ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት የጸረ ሽብር፣ የበጎ አድራጎትና ማህበራትን ማደራጃ ፣ የመረጃ ነጻነትና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅና ሌሎች ህጎችን ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል፡፡በእነዚህ ህጎች መሻሻል ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር ፋሲል፡- ማንኛውም ህግ በደረቁ አይደለም ስራ ላይ መዋል ያለበት፡፡ ህጉ መጀመሪያ ሲወጣ ለምን አስፈለገ? ከህጉ በስተጀርባ ምን ችግሮች ታይተው ነው ህጉ እንዲወጣ የተደረገው? የሚለው አንዱ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የጸረ ሽብር አዋጅን ብንወስድ ህጉ ለምን ወጣ? ምን ችግሮች አጋጥመውና ስጋት ተፈጥሮ ነው ይህ ህግ ሊወጣ የቻለው? የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ህግ ከወጣ በኋላ አፈጻጸሙን ማየት ይገባል፡፡ ምክንያቱም በጠባቡ ወይም ሰፋ ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ እና አንዳንድ ጊዜ በጠባቡ መተርጎም ያለበት ሰፋ ተደርጎ ከተተረጎመ ችግሮች ይፈጥራሉ ወይም ሰፋ ተደርጎ መተርጎም ያለበት ጠበብ ተደርጉ የሚተረጎም ከሆነ ሌሎች ችግሮች መፍጠራቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ህጎች መጀመሪያውኑ ለምንድነው ያስፈለጉት? ሁለተኛ ደግሞ አፈጻጸማቸው ምን ይመስላል? የሚለው መታየት አለበት፡፡
እነዚህ ህጎች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሌሎች ህጎቻችን እንደገና ቢፈተሹ ነው አስፈላጊ የሚሆነው፡፡ሁልጊዜ ህጎች በአጠቃላይ መፈተሽ አለባቸው፡፡ከህጉ በስጀርባ ምን አስተሳሰብ አለ የሚለው ጭምር ማየቱ ተገቢ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ተመዝብሮ ወደ ውጭ የሄደውን ገንዘብ መንግስት ለማስመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር የማስመለስ ሙከራው ይሳካ ይሆን?
ዶክተር ፋሲል፡- ይሳካል አይሳካም የሚለውን ወደፊት የምናየው ነገር ነው፡፡ የመንግስትና የህዝብ ንብረት መዝረፍ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ አሰራር አንጻር በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ መንግስታት የተመዘበረና ተዘረፈ የሚሉትን ገንዘብ ለማስመለስ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ የአንዳንዶቹ ሲሳካም አይተናል፡፡
ለምሳሌ ናይጄሪያ በጀነራል ሳኒ አባቻ ዘመን ከአገሪቱ የወጣ ገንዘብ ሲውዘርላንድ ባንክ ተቀምጦ የተወሰነ ገንዘብ ወደ ናይጀሪያ መንግስት መመለሱ ይታወቃል፡፡ ግን ውጣ ውረዱ ከፍተኛ ነው፡፡ አንዳንድ መንግስታት በዚሁ ነው የሚተዳደሩት ማለት ይቻላል፡፡ የስዊዝ ባንኮች እኛ የዓለም ባንኮች ነን የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ እና እዚያ ውስጥ ገብቶ ተከራክሮ አሸንፎ ገንዘብ ማስመለስ ቀላል ስራ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአገራዊ ለውጡ ዙሪያ ምን ዕይታ አልዎት?
ዶክተር ፋሲል፡- ባለፉት ስምንት ወራቶች በአገሪቱ በተለያየ መልኩ አስገራሚ የሆነ ለውጥ እየተካሄደ ነው፡፡ ከጎረቤት አገሮች በተለይ ደግሞ ከኤርትራ ጋር ሰላም መፈጠሩ እኔ ከሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተመሳሳይ አመለካከት ነው ያለኝ፡፡ በጣም ተደንቄአሁ፡፡ ደስም ብሎኛል፡፡ የብዙ ሕዝቦች ፀሎት መልስ አድርጌ አየዋለሁ። ይህ ቀጣይ እንዲሆን በጥንቃቄ ስራዎች ከሰራን ዘለቄታ ይኖረዋል፡፡ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር ዐብይ አህመድ በዚህ በኩል ትልቅ በር እንደከፈቱ አድርጌ ነው የማምነው፡፡
የሴቶች እኩልነት ጥያቄ ህገ መንግስቱ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አፈጻጸሙን በምናይበት ጊዜ አሁን ነው ብዛት ባለው መልኩ የመንግስት ከፍተኛ ስልጣን ለሴቶች የተሰጠው፡፡ ይህ በመንግስት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በህብረተሰቡ እስከ ታች መውረድ አለበት፡፡
በሌላ በኩል ይህ የሽግግር ወቅት ለውጥ እንደመሆኑ መጠን ውዥንብር ውስጥ የሚያስገቡ ነገሮችም እያየን ነው፡፡ መከሰት የሌለባቸው የህዝብን ሰብዓዊ መብት የሚነኩ መፈናቀልና ግጭቶች እያየን ነው፡፡ግን እኔ የኢትዮጵያ የወደፊቱ ጉዞ ብሩህ እንደሆነ ነው የማየው፡፡ ይህ የመንግስት ስራ ነው የሚባልበት ሳይሆን ሰላሙም፣ ዴሞክራሲውም እና ልማቱም በትክክልና በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ከእኔ ምን ይጠበቃል የሚለውን ነገር የሁላችንም የቤት ስራ መሆን ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለውጡ የህዝብን ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ለመመለስ ምን ምን ስራዎችን ቢሰራ የሚል ምክረ ሃሳብ አለዎት?
ዶክተር ፋሲል፡- ዛሬ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ወጣት ነው፡፡ በዚህ ወጣት ህዝብ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ ምን ይፈልጋልና በምን መልክ ነው መደገፍ ያለበት የሚለው መሰረታዊ የመንግስት የቤት ስራ ነው፡፡ ከትምህርት፣ ከስራና ለኑሮ መሟላት ከሚያስፈልጉት ጉዳዮች ዋና ትኩረቱ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ አልፎ አልፎ የሚሰራ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ስራ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህን ስል የሌሎቹ ግድ የለውም ማለቴ አይደለም፡፡
ሌላው የእኩልነት ጉዳይ ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰብ፣ የጾታ፣ የሃይማኖት፤ ከተሜና ገጠሬ ሁሉም በእኩልነት መስተናገድ አለበት፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ የሚታየው መንግስት በብቸኝነት አገልግሎት ሰጪ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያገኝ ፈቃጅና ተቆጣጣሪም ነው፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች ተደራሽ፣ አድሎ የሌለበትና ፍትሀዊና ፈጣን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ማገልገል የማይችሉ ሰዎችን ከአንዱ ወንበር አንስቶ ሌላ ወንበር ማስቀመጥ ሳይሆን ሊያገለግሉ በሚችሉ ብቃትና እውቀቱ ባላቸው ሰዎች ብቻ ነው መተካት ያለባቸው፡፡
ሌላው መንግስት ለግል ሴክተሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለበት፡፡ ለምሳሌ አብዛኛው የስራ ዕድል የሚፈጠረው በግሉ ሴክተር ነው፡፡ ስለዚህ ኢንቨስትመንት የመሳብና ስራ ለሚፈጥሩ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ከዓለም ወደ ኋላ እንዳንቀር ከማን እናንሳለን የሚለው መሰረታዊ አስተሳሰብ በህዝቡ ውስጥ እንዲሰርጽ በትምህርትም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን መሰራት አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ አሰራሮቻችን በሙሉ ቀልጣፋ ወቅታዊና ግልጽ መሆን አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ፋሲል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አጎናፍር ገዛኸኝ