አዲስ አበባ፡- የህግ የበላይነት የምትደራደርበትና የምትሸማገልበት ጉዳይ አይደለም ሲሉ የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ተመስገን ዘውዴ አመለከቱ፡፡ አቶ ተመስገን በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት፤ መንግሥት የህግ የበላይነትን ማስከበር ቀዳሚ ተግባሩ ሊያደርግ እንዲሁም በህግና በስርዓት ዜጎች ተንቀሳቅሰው የመሥራት ህገ መንግሥታዊ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፡፡
‹‹የህግ የበላይነት የምትደራደርበትና የምትሸማገልበት ጉዳይ አይደለም›› ያሉት አቶ ተመስገን፣ በህግና በስርዓት ማንም ዜጋ የትም ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ህገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ ይህንን እውነታ ህዝቡ መረዳት እንደሚገባውና ክልሎችም ይህንኑ ማስረዳትና የህዝቡንም መብት ማስከበር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ክልል ማለት አጥር ነው፡፡
ከሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሰዎች ሌላው ክልል ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩና እንዳያለሙ የተደረገበት ሁኔታ አለ። ይህ መቀየር አለበት›› ያሉት አቶ ተመስገን፤ ዜጎች ህጋዊ በሆነ መንገድ ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ እውን መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ የህግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡
እርቀ ሰላም ቢደረግም የአገሪቱን ህግ ባከበረ መልኩ መፈጸም አለበት፡፡ ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳና ረብሻ እንዲፈጠር ያደረጉ ሰዎች ወይም ቡድኖች በህግ ፊት መቅረብ አለባቸው፡፡ መንግሥት የህግ የበላይነትን ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት መንፈስ በፍቅር የኖረ ህዝብ መሆኑን በመጠቆምም፤ አልፎ አልፎ የሚታየው አለመረጋጋት ታፍኖ የቆየው ህዝብ መብትና ስልጣን ሲያገኝ ራሱን ለመግለጽ ያደረገው እንቅስቃሴ ነው›› ብለዋል፡፡
ህዝቡ ራሱን የሚገልጽበት መንገድ ሰላማዊ እንዲሆንም መክረዋል፡፡ ‹‹በብሄር እየተደራጀን የምንታገልበት ጊዜ አልፏል፡፡ ለአገርም ጥቅም የለውም›› ያሉት አቶ ተመስገን፤ ‹‹ከክልላዊ አመለካከት መውጣት ይገባል›› ብለዋል፡፡ የሚያዋጣው ህብረ ብሄራዊነት ነው፡፡ ሰዎች በቋንቋና በባህል የሚከፋፈሉበት ዘመን እያበቃ አንድ የሚሆኑበትና ወደ ሰልጣኔ እየሄዱ ባለበት ጊዜ ወደ ትንሿ ጉድጓድ መመለስ አያዋጣምና ፓርቲዎች መጣመርና ህብረ ብሄራዊ መሆን እንደመኖርባቸው አስረድተዋል፡፡
‹‹ወደፊት አዲስ አስተሳሰብ ሊመጣ ይገባል›› ያሉት አቶ ተመስገን፤ ‹‹ዕድገት እንዲመጣ ከተፈለገ ስለአደረጃጀት፣ ስለኑሮ፣ ስለኢኮኖሚና ስለማህበራዊ ግንኙነት ወጣ ያለ ሃሳብ የሚያስቡ ፖለቲካውን ሊቀላቀሉ ይገባል፣ ለወጥ ያለ አደረጃጀትና ፍልስፍና የሚከተሉ ወጣቶች መምጣት አለባቸው፡፡›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በዘላለም ግዛው