አዲስ አበባ፡- ከአማራ ክልልና አጎራባች አካባቢዎች በግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ከክልሉ ውጪ በአዲስ አበባ የተቋቋመው የገቢ ማሰባሰቢያ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ።
የኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ ትናንት በሸራተን አዲስ ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤በክልሉና ከክልሉ ውጪ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከ90 ሺ በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። እነዘህን ተፈናቃዮች በዘለቄታው ለማቋቋም በክልሉና ከክልሉ ውጪ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል።
በአዲስ አበባ የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴም ለመልሶ ማቋቋሙ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ገንዘቡን ለማሰባሰብ ኮሚቴው በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች የሚገኙ የክልሉ ተወላጆችን፣ ባለሀብቶችን፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዳያስፖራዎችንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር በገንዘብና በቁሳቁስ ሀብት የማሰባሰብ ተልእኮውን እየፈፀመ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለዚህም የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ መላኩ፣የንዑሳን ኮሚቴዎቹ የስራ ማጠናቀቂያና የምስጋና ፕሮግራም በመጪው መጋቢት 7 በሸራተን አዲስ እንደሚዘጋጅ አመልክተዋል። እንደ ዋና ሰብሳቢው ገለጻ፤ በሸራተኑ መርሀግብር የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ይዘጋጃል። በስነ ስርአቱ ላይም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች ይገኛሉ። ተፈናቃዮችን በግላቸው መርዳት ለሚፈልጉ ዜጎች በአማራ ክልል መንግስት አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ፈንድ በተዘጋጁ የባንክ አካውንት ቁጥሮች ገቢ ማድረግ እንደሚችሉም ዋና ሰብሳቢው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በአስናቀ ፀጋዬ