
የ‹‹ጠቦ›› ወንዝ በክረምት ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለውን ያህል በበጋ መኖሩም አይታወቅም፤እንጥፍጣፊ ውሃ የለበትም። የቀበሌዋ ነዋሪዎች ውሃ ማቆር ላይ በትኩረት እንዲሠሩ ቢሞከርም በዚያ የመጠቀም ክህሎቱ እምብዛም አላደገም። አካባቢውም ዝናብ አጠር በመሆኑ የቀበሌዋን የውሃ ችግር አግዝፎታል። የቦሰት ወረዳዋ የበቀቱ ሎሜ ቀበሌን። ቀበሌዋን የሚፈታተናት የውሃ ችግር ብቻ አይደለም።
የወፍጮም አለመኖር ሌላው ፈተናዋ ነው፤ በዚህ የተነሳም ደካሞች የላመ እንዳይበሉ ደንቃራ ሆኖባቸዋል። የቀበሌዋ ነዋሪ ወይዘሮ አሰለፈች መሸሻ ወፍጮ በአካባቢያቸው ባለመኖሩ ምክንያት እህል ከቤታቸው ሳይጠፋ ጥሬ ለመቆርጠም መገደዳቸውን ይናገራሉ። ‹‹እኔ ለምሳሌ አቅመ ደካማ ነኝ። በአካባቢው ወፍጮ ቢኖር ጥሬ ከመቆርጠምና ከንፍሮ እድን ነበር።
በቀበሌያችን ውሃና ወፍጮ የለም። የሚችል ከተማ ድረስ በጋሪ እህሉን አስጭኖ ሄዶ ያስፈጫል፤ የማይችል ደግሞ ቆሎ ይቆረጥማል።›› ይላሉ። እንደ ድሮ ሴቶች ቤት ውስጥ መፍጨት ከቀረ ዘመናት ተቆጠረዋል፤ እንኳን ጥሬ ለመፍጨትና ቅንጬ ለመከካት መንበርከክ ቀርቶ የተፈጨውን ለማቡካትም ድካም አለ። የቤት ውስጥ ወፍጮ ከነመጁ ያላቸው ቢኖሩም እንደ ድሮ ዘመን ፈጭቶ ቤተሰቡን የሚመግብ የድሮ ጉልበት የለም ሲሉ ያብራራሉ።
የቀበሌዋ ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይ ኃይሉም መንግሥት ወፍጮ እንዲተክልላቸው ይጠይቃሉ። ‹‹አቅማችንን አሰባስበን ከተማ ድረስ ከሄድን በኋላ መብራት ጠፍቶ የምንመለስበትና ትርፉ ድካም የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው።›› የሚሉት ወይዘሮ ፀሐይ፣ ‹‹ይህንንም የሚያደርገው አቅም ያለው ነው እንጂ አቅመ ደካማው ደግሞ ጭርሱኑ መንቀሳቀስ አይችልም።›› ይላሉ።
ወፍጮ ቤት ለመሄድ የሚወስደው ጊዜ ሌላ ተጨማሪ ሥራ በመሥራት ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ነበር የሚሉት ሌላዋ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ብዙነሽ ጀማነህ ፣ የወፍጮ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ያለአንዳች አማራጭ እና ያለተተኪ ሊቀርብ የሚችለው ውሃም በቀበሌያቸው እንደ ልብ ባለመገኘቱ ኑሯቸውን እንደተፈታተነው ነው ያመለከቱት።
ነዋሪዎቹ ለኑሯቸው ወሳኝ የሆነውን ጉዳይ ማጣታቸው ብዙ ነገር እንዳመሰቃቀለባቸው ተናግረዋል። ይህ ችግርም ከመንግሥት አቅም በላይ እንዳይደለም በመጥቀስ መንግሥት የተጠማ ጎሮሮ በውሃ ሊያረሰርስላቸው እንደሚገባ ይገልጻሉ። በምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ የሴቶችና ሕፃናት ጽሕፈት ቤት የሴቶች አደረጃጀት ወይዘሮ ዛሊካ አደም እንደተናገሩት፤ ቦሰት ወረዳ የውሃ ችግር አለበት። በወረዳው አዋሽ አምስት ቀበሌዎችን ሰንጥቆ የሚያልፍ ቢሆንም፤ በቀቱ ሎሜን ግን አይጎበኛትምና የውሃ ችግር በስፋት እንዲፈታተናት አድርጓታል።
በእርግጥ አምስቱም ቀበሌዎች የአዋሽ ወንዝ ተጠቃሚ ናቸው ማለት አያስደፍርም። በበቀቱ ሎሜ ቀበሌ ውሃ ጎሮሮን የሚያረጥብ ውሃ የሚገኘው በስቃይ ነው። በቀበሌዋ የሚገኘው ‹‹ጠቦ›› በመባል የሚታወቀው ወንዝም ቢሆን ለዓይን የሚታየው በክረምት ብቻ ነው። በጋ ላይ እንዳየሽው ደርቋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ጎሮሯቸውን ማራሺያ ውሃ ሲያጡ ወደ ጠቦ ወንዝ ሄዶ አሸዋውን ዛቅ ዛቅ አድርገው ውሃ ለማውጣት ይገደዳሉ በማለት ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ዛሊካ በእርግጥ አዋሽ የቱንም ያህል ከቀበሌዋ ራቅ ቢልም ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለነዋሪው ለማድረስ ከተፈለገ ህዝቡን ከሚያስተዳድረው መንግሥት አቅም በላይ ነው የሚል እምነት የላቸውም። በመሆኑም መሰረታዊ የሆነውን ጉዳይ በማቅረብ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ህዝቡን እንዲታደጉም ይጠይቃሉ። ‹‹ውሃ ቢኖር ማምረትም ሆነ ማርባት ይቻል ነበር። ውሃ እንዲያቁሩም ግንዛቤ በማስጨበጥ ላይ ነን። በዚህም ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች አሉ፤ችግኝ ለማፍላት ፍላጎት ያላቸው ሴቶች ከተደራጁ በኋላ ውሃ ባለመኖሩ ሃሳባቸው ከንቱ ቀርቷል።›› ብለዋል።
የወፍጮ ችግር አለ የተባለውንም እሳቸውም ይጋሩታል። በግብረ ሰናይ ድርጅት በ1998 አካባቢ በነዳጅ የሚሠራ ወፍጮ እንደነበር አስታውሰው፣ በመለዋወጫ አለመኖር ሳቢያ ሥራ ማቆሙን ያስታውሳሉ። ሞተሩን በመሸጥ ተጨማሪ ገንዘብ በመመደብ እና የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችምን ድጋፍ በመጠየቅ ዘመናዊ ወፍጮ ለማቋቋም ታስቧል ይላሉ። መሄድ እስከሚቻለው ርቀት መሄድ ግድ እንደሚል ጠቅሰው፣የማህበረሰቡም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በአስቴር ኤልያስ