አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትናንት በስቲያ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቤተሰቦች ስለአደጋው ለማወቅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በሚያደርጉት ቆይታ ሙሉ ወጪያቸውን እንደሚሸፍንና አስፈላጊውንም ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የአየር መንገዱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ወልደማርያም ትናንት በደረሰው አደጋ ዙሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች ማብራሪያ ከሰጡ በሁዋላ ለጋዘጠኞች እንደተናገሩት ፤ አየር መንገዱ እስከአሁን የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም በ35ቱም ሀገራት ለሚገኙ የሟች ቤተሰቦች ስለአደጋው መረጃዎችን ሲያደርስ ቆይቷ።
በቀጣይም ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የሟች ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፤ ወጪንም ይሸፍናል። የትራንስፖርት ሚኒስቴር ፤ ሲቪል አቪይሽንና የአየር አደጋ ሲከሰት ለምርመራ ከሚቋቋም ቦርድ ጋር በመሆን የአደጋውን መንስኤ ለማወቅም ዓለም አቀፍ ህግጋትንና መመሪያዎችን በተከተለ አካሄድ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ የማጣራቱ ሥራ ከተጠናቀቀም በኋላ አየር መንገዱ አስክሬኖችን ወደ ቤተሰባቸው ያደርሳል:፡ ምርመራው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅም አደጋው የደረሰበት ቦታ አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል።
ለጊዜው የተለየ ችግር ባይኖረም ቀሪዎቹ ስድስቱ ቦይንግ 737 – 800 ማክስ አውሮፕላኖች ከአገልግሎት ታግደዋል፡፡ ‹‹ቦታውን እኛም የተጎጂ ቤተሰቦችም ማየት እንፈልጋልን›› የሚል ጥያቄ ከዲፕሎማቶቹ ቀርቦ እንደነበር አቶ ኢሳያስ ጠቅሰው፣ ጥያቄውን ውሳኔ ለሚሰጠው አጣሪ ቦርድ እንደሚያቀርቡም ተናግረዋል። በተመሳሳይ የሟቾች ሙሉ መረጃ ይሰጠን የሚል ጥያቄ እንደተነሳና ለጊዜው ለሟቾች ሀገራት በቻ እንደሚነገር አስታውቀዋል።
የካሳ ጉዳይም ዓለም አቀፍ መመሪያዎችን በተከተለ ሁኔታ እንደሚፈጸም ተናግረው፣ ዲፕሎማቶቹ የአደጋውን መነሻ ለማጣራት ለሚደረገው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡ አየር መንገዱ በ73 ዓመታት ታሪኩ በቴክኒክና በባለሙያ ስህተት ምንም ዓይነት አደጋ ደርሶበት አያውቅም ያሉት አቶ ኢሳያስ ፣ ዛሬም ደረስ በቀን 300 በረራዎች በማድረግ ሃያ ሺ የሚደርሱ መንገደኞችን እያጓጓዘ እንደሆነም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በየራስወርቅ ሙሉጌታ