አምቦ፡-አፋን ኦሮሞ ካለው የተናጋሪ ህዝብ ብዛት፣ የአገሪቱን ህዝቦች እርስ በርስ ለማስተሳሰር ካለው አቅምና የአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚታይበት ከመሆኑ አንጻር ታይቶ ተጨ ማሪ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ተጠየቀ።
«አፋን ኦሮሞ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ቢሆን ያለው ጠቀሜታ/ዕድሎች» በሚል ርዕስ የአምቦ ዩኒቨርሲቲና የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ ባዘጋጁትና በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ ከተለያዩ ክልሎችና ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በጥናታዊ ጽሁፎቹ እና በተሳታፊዎቹ የተለያዩ ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን ቋንቋ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችንና የዜጎችን ዝውውር በማሳለጥ የህዝቦች አንድነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የማሳግ ከፍተኛ ሚና አለው።
አፋን ኦሮሞ በሀገሪቱ ከፍተኛ ተናጋሪ ያለው በመሆኑ፤ በክልሉ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና የዜጎች ዝውውር ከመካሄዱ አንጻር እንዲሁም እያደገ ከመጣው የምርምርና የጥናት፤ የትምህርት እና የስነጽሁፍ ቋንቋነቱ አኳያ ሲታይ ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ቢሆን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑም ተመላ ክቷል፡፡
በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት የሀገራችንን ቋንቋዎች በተገቢው መንገድ መጠቀም ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገትና ለህዝቦች ትስስር ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ያስችላል ብለዋል፡፡ እንዲህ አይነት ሀገራዊ እይታ እና ጠቀሜታ ያላቸው ውይይቶች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚያበረታታ ገልጸው፣ ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአምቦ ዩኒቨርሲቲን ፈለግ በመከተል ተመሳሳይ መድረኮችን ማዘጋጀት ይገባቸዋል ሲሉም አክለዋል፡፡
በሲምፖዚየሙ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩና በተለያየ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ሳይንሳዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ መጻሕፍት በተለይ በኢትዮጵያ ጋዜጦች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የአፋን ኦሮሞ ጋዜጣ የሆነው በሪሳ ለእይታ ቀርበው በተሳታፊዎች ተጎብኝተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
ቸርነት ሁንዴሳ