ኢትዮጵያን በቅርቡ የህዝብና የቤት ቆጠራ እንዲሁም በመጪው ዓመት አጠቃላይ ምርጫን ያሉ ትላልቅ ኢቨንቶችን ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
እነዚህን ትላልቅ ኢቨንቶች ስኬታማ ለማድረግ ሚዲያ ካውንስል ማቋቋም አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረገ ኮንፍረንስ ትላንት መጋቢት 01 ቀን 2011 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሂዷል። በኮንፍረንሱ ላይ የህዝብ ሚዲያ ሃላፊዎች፣ የግል ሚዲያ ባለቤቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተካፋይ ሆነዋል።
የኦ ኤም ኤን ባለቤት አቶ ጃዋር ሙሃመድ “ሚዲያ በሽግግር ወቅት” በሚል ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍ ላይ ሚዲያው አገራዊ ሪፎርሙ የፈጠረለት መልካም አጋጣሚዎች መኖራቸውን አንስተው ፤ ይሁንና ይህን አጋጣሚ በአግባብ እየተጠቀመበት ባለመሆኑ በአስቸኳይ የሚዲያ ካውንስል ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።ሚዲያው ውጥረት ለማርገብም ሆነ ችግር ለመፍጠር አቅም ያለው በመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በአግባብና በሃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ጃዋር ተናግረዋል።
“ሚዲያ በአገር ግንባታ” በሚል ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ባቀረበው የመነሻ ጽሁፍ ላይ አሁን ላይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሰፊው ተከፍቷል፤ ይሁንና እኛና እነርሱ የሚል አካሄድ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው ፤ እንደነዚህ ያሉ አካሄዶችን ለመቅረፍ የሚያስችለው ደግሞ የሚዲያ ካውንስል በመሆኑ በአስቸኳይ መቋቋም እንዳለበት አብራርተዋል። የሚቋቋመው የሚዲያ ካውንስልም የጋዜጠኛ ማህበራትን ጨምሮ ከሁሉም አካል የተወከለ መሆን እንዳለበት አቶ ሲሳይ ጠቅሰው የካውንስሉ መቋቋም ለሚዲያው ስራ እንደሚያቃልልና ሁኔታዎችንም እንደሚያመቻችም ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ባቀረቡት ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ ለአገር ግንባታ የሚዲያ ሚና እና ለሚዲያው እድገት የዴሞክራሲ መጠናከር ወሳኝ በመሆኑ ሚዲያው ይህን ታሳቢ አድርጎ እንዲሰራ ጠቁመው፤ አሁን ላይ የሚዲያ የካውንስል መቋቋም በመንግስት በኩል ያለውን የመረጃ አቅርቦት ችግርም እንደሚቀርፍ ጠቅሰው ሚዲያዎችም በሃላፊነት ስሜት መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም ህብረተሰቡ መደበኛ ሚዲያንና ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለይተው ማየት እንዳለባቸው ተናግረዋል።