አዲስ አበባ፡- ለተለያየ ጉዳይ ሀገር ውስጥ ገብተው ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ የቆዩና ባልተፈቀደላቸው ሥራ ተሰማርተው የተገኙ 765 የውጭ ሀገር ዜጎች ከሀገር እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡23 ደግሞ በህግ ተጠይቂ ሆነዋል፡፡ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዓለምብርሃን ታፈሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ በቱሪስት ቪዛ የሚገቡ አንዳንድ የውጭ ዜጎች ያለፈቃድ ሥራ በመስራት ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡
መምሪያው ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደው የውጭ ሀገር ዜጎች የምዝገባና ቁጥጥር ሥራ 788 የውጭ ዜጎች ከሀገር እንዲባረሩና በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም 705ቱ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ ቆይታ ያደረጉ ሲሆኑ የጉዞ ሰነድ ተዘጋጅቶላቸው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ 60ዎቹ ደግሞ በኃይል እንዲወጡ የተደረጉ ሲሆኑ፣ 23ቱ ደግሞ ለህግ ቀርበዋል፡፡ለህግ የቀረቡት በቱሪስት ቪዛ ገብተው በተለያየ ሥራ ላይ ተሰማርተው የተገኙ፣ ባልተሟላ የጉዞ ሰነድና በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑን አቶ ዓለምብርሃን አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ዓለምብርሃን ማብራሪያ፣ በቱሪስት ቪዛ የሚገቡ የውጭ ዜጎች ስድስት ወር መቆየት ስለሚችሉ በፋብሪካዎች የማሽን ተከላ እና በተለያየ ሥራ ላይ ይሰማራሉ፡፡ በመሆኑም በቱሪስት ቪዛ በሚገቡ የውጭ ዜጎች ላይ ችግሩ ጎልቶ ይስተዋላል:: በኢንዱስትሪ ኩባንያዎች አማካኝነት ለአጭር ጊዜ ለሥራ የሚመጡም እንዲሁ ከተፈቀደላቸው ቀናት በላይ ይቆያሉ፡፡ ከተፈቀደላቸው የሥራ ፈቃድውጪም የሚንቀሳቀሱ የውጭ ዜጎች መኖራቸውን ኤጀንሲው የደረሰባቸው ሲሆን በጥቆማና ከሀገር ሊወጡ ሲሉ የደረሰባቸውንም ለፍትህ አካል በማቅረብ እንዲቀጡ ማድረጉን አቶ ዓለምብርሃን አስታውቀዋል፡፡
የቆይታ ጊዜያቸውን ያሳለፉ በገንዘብ፣ ባልተፈቀደላቸው ሥራ ላይ የተሰማሩትን ደግሞ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ኤጀንሲው የሀገሪቷን ህግ አክብረው የማይንቀሳቀሱ የውጭ ዜጎች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ከኤምባሲዎቻቸው ጋር በመነጋገርና ምክር በመስጠት እንዲታረሙ የማድረግ ሥራን እንደሚያስቀድም የጠቆሙት አቶ ዓለምብርሃን፣ በቅርቡም በቱሪስት ቪዛ ገብተው በልመና ላይ ተሰማርተው የነበሩ 37 የሶሪያ ዜጎች በነፃ የመውጫ ቪዛ ተዘጋጅቶላቸው መስተናገዳቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በስደተኛ መመዝገብ ለሚፈልጉም ምርጫቸው እንደተጠበቀላቸውም አመልክተዋል፡፡
ሶሪያውያኑ ከሌሎች የውጭ ሀገር ዜጎች በተለየ ሁኔታ የተስተናገዱ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ለኢንቨስትመንት፣ለንግድ፣ለምርምር እና ለተለያየ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ዜጎች ከመምጣታቸው በፊት በቆንጽላ ጽህፈት ቤት አማካኝነት እና ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላም ሸክም እንዳይሆኑ የምዝገባና የቁጥጥር ሥራ ይሰራል››ያሉት አቶ ዓለምብርሃን፣ኤጀንሲው ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር እንዳይገባ ከመነሻ ጀምሮ የመከላከል፣ በህገወጥ የገባውንም መከታተል፣ ከገባ በኋላም ከተፈቀደለት ጊዜ በላይ እንዳይቆይ፣ ባልተፈቀደለት የሥራ መስክ ላይ ተሰማርቶ ከተገኘ ተከታትሎ ለሚመለከተው እንደየ ጉዳዩ እንደሚያቀርብ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ከመጣው ኢንቨስትመንትና የቱሪስት ፍሰት ጋር የሚመጥን የቁጥጥር ሥርዓት እንደሚያስፈልግ በኤጀንሲው በመታመኑ ስጋቱን በሚያስወግድ መልኩ በአየርና በየብስ ወደሀገር የሚገቡ የውጭ ዜጎች ህጋዊነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ በዘመናዊ አሰራር በመታገዝ ለማጠናከር ሥራዎች መጀመራቸውን አቶ ዓለምብርሃን አስታው ቀዋል፡፡ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰው ኃይል ጥናትና የሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ኃይሌ በበኩላቸው እንደገለፁት፣ እነማን ህጋዊ እንደሆኑ፣በተፈቀደላቸው የሥራ ፈቃድ ስለመስራታቸው እና የሥራ ፈቃዳቸውን በአግባቡ ስለማሳደሳቸው ክልሎች ተከታትሎ የማስፈጸምና የተሟላ መረጃ የማቅረብ ኃላፊነት ቢኖርባቸውም በአግባቡ እየተወጡ አይደለም፡፡
መረጃን በዘመናዊ መንገድ አደራጅቶ በወቅቱ በመለዋወጥ ላይ ክፍተት መኖሩን ያመለከቱት አቶ አበበ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሟላ መረጃ በጊዜው እንደማያገኝም አመልክተዋል፡፡ ክፍተቱን ለመሙላት እና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በ2012 ዓ.ም በተደራጀ መልኩ ለመስራት ከወዲሁ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ መንግሥታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ለሚሰሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ እንደሚሰጥ የጠቆሙት አቶ አበበ፣ 60 በመቶ የሚሆኑት ባለሙያዎች መሆናቸውንና ቀሪዎቹ በእጅ ሙያና በተለያየ ዘርፍ የሚሰማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በተያዘው በጀት አመት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለ18ሺ734 የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ የሰጠ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በለምለም መንግሥቱ