ባለፈው እሁድ፣ ጥር አንድ ቀን 2014 ዓ.ም፣ ኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆቿን ሸልማለች፤ እውቅና ሰጥታለች። ለክብሯና ለነፃነቷ ሲፋለሙ በክብር የተሰውትን ልጆቿን ጭምር ስማቸው በስራቸው ከመቃብራቸው በላይ ከፍ ብሎ እንዲታወስ በክብር ጠርታቸዋለች።
የአገር ዘብ የሆነው ጀግናው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት አባላቱ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት እና በ ‹‹ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት›› ላሳዩት ጀግንነት ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ሽልማቱ በመከላከያ ደረጃ በአዋጅ የተፈቀዱትን ሽልማቶችን ያካተተ ሲሆን በሦስት ደረጃዎች ተለይተው የቀረቡ የሜዳሊያ (የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ አንደኛ ደረጃ፣ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ሁለተኛ ደረጃ እና የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ) ሽልማቶችን፣ ለላቀ የሥራ ውጤት የሚሰጠውን ሽልማትን፣ የዓድዋ ድል ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ ሽልማትን እንዲሁም ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ሽልማት ለጀግኖቹ ተሰጥቷል።
በርካታ ጀግኖች እንደየስራ አፈፃፀማቸው ከላይ የተጠቀሱትን ሽልማቶች ያገኙ ሲሆን ለአብነት ያህል ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና፣ ሌተናል ጀኔራል በላይ ስዩም፣ ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ፣ ሌተናል ጀኔራል መሰለ መሠረት፣ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ፣ ሌተናል ጀኔራል አብዱራህማን እስማኤል፣ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ እና ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን ኢተፋ የዓድዋ ድል ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚዎች ሆነዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ፣ ጀኔራል ባጫ ደበሌ እና ሌተናል ጀኔራል አለምእሸት ደግፌ ደግሞ ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚዎች ሆነዋል።
ለዛሬ ከእነዚህ በርካታ ጀግኖች መካከል የጥቂቶቹን ባለውለታዎቻችንን የጀግንነት ጀብዱ በጥቂቱ እንዳስሳለን። ሌተናል ጀኔራል ዓለምእሸት ደግፌ በሐረር እና በገነት ጦር አካዳሚዎች ወታራዊ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። ለከፍተኛ ወታደራዊ ትምህርት ወደ ሶቭየት ኅብረት ሄደው በሌኒንግራንድ መድፈኛ አካዳሚ ትምህርታቸውን ተከታትለው የአካዳሚው ወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑ ጀግና ናቸው።
የሶማሊያን ወረራ በመመከት ታላቅ ገድል ፈፅመዋል። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም የአገራቸውን ጥሪ ተቀብለው በጀግንነታቸው አገራቸውን አስከብረዋል። የጥምር ጦር ውጊያ መሃንዲሱ ሌተናል ጀኔራል ዓለምእሸት፤ የአየር ወለድ ውጊያን ከአየር ኃይል ጥቃት ጋር አቀናጅተው በፈፀሟቸው ጀብዶች ይታወቃሉ። የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ከሃዲው ሕ.ወ.ሓ.ት የአገሪቱ አድራጊ ፈጣሪ ኃይል በነበረበት ወቅት ይህን ታላቅ የጦር ጠቢብ አስሮ አንገላቷቸዋል፤ ማዕረጋቸው ተገፍፎ ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱም አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የጀግናው ማዕረጋቸው እንደመለስላቸውና ጡረታቸውም እንዲከበርላቸው አድርገዋል። ጀግና ወታደር ምንጊዜም ቢሆን አገሩን ያስቀድማልና በተፈፀመባቸው በደል ቂም ያልያዙት ጀግናው ሌተናል ጀኔራል ዓለምእሸት፤ የተደረገላቸውን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው ከሃዲው ቡድን አከርካሪው እንዲሰበር አድርገዋል።
በከሃዲው የሕ.ወ.ሓ.ት ቡድን ላይ እርምጃ መውሰድ ሲጀመር ጠላትን ድባቅ ለመምታት በዘመናዊ ወታደራዊ ትምህርትና በልምድ የታገዘ የጦር አመራርና ውጊያ ያስፈልግ ነበር። ይህ ዓይነቱ የውጊያ ሥልጠናና ልምድ ካላቸው ወታደራዊ አዛዦች መካከል አንዱ ሌተናል ጀኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ነበሩና ጀኔራሉ የአገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ብርቱና ቆራጥ የሆነ ተጋድሎ ፈፅመው አንጸባራቂ ድል አስመዝግበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ‹‹በምስራቅ በኩል በተለይ ከባድ መሳሪያን በማስተባበር ስራ የጀመረው ወታደራዊ ሊቁ ጀኔራል ዓለምእሸት ነበር›› ብለው የመሰከሩላቸው ሌተናል ጀኔራል ዓለምእሸት፤ በራያ ግንባር የከባድ መሳሪያዎች አስተባባሪ ሆነው የተካኑበትን የውጊያ ስልት በመተግበር ጠላትን ዶግ አመድ አድርገውታል።
በመድፍና በሜካናይዝድ ኃይል የተቀናጀ እቅድ በመንደፍ በአፋር በኩል አድርጎ ወደ ትግራይ ዘልቆ የገባውን የመከላከያ ሠራዊት ኃይል መርተዋል። በዚህ የላቀ ችሎታ ጠላትን እየደመሰሱ ገስግሰው ከጀኔራል ባጫ ደበሌ ጦር ጋር ማይጨው ላይ ተገናኝተዋል።
ተራሮችን እየሰነጠቀ፣ አለቱን እየሰባበረና ገደሉንም እየዘለለ ከምዕራብና ከሰሜን አቅጣጫ ከመጣው የጀኔራል አበባው ታደሰ ጦር ጋር መቀሌ ገብተዋል። የጦር ሊቁ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ሄዋነ ላይ በሰጡት መግለጫ፡- ‹‹… ወጣ ገባ የሆነው መሬት ጠላት እመክትበታለሁ፤ አቆምበታለሁ ብሎ ያሰበበት ቦታ ነበር። ያሉንን መሳሪያዎች በማስተባበር በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በአካባቢው መሽጎ የነበረው ኃይል ለሦስት ቀናት ያህል መራራ ውጊያ ካደረገ በኋላ ተፍረክርኮ እንዲበተን ማድረግ ተችሏል። … ውጊያ ማለት ተኩስና ንቅናቄ ነው። ንቅናቄውን የሚሰራው እግረኛው ነው፤ በእርግጥ ሜካናይዝዱም ይነቃነቃል።
ግን ዋናው ስራ ተኩስ ነው። ተኩስ በጥሩ ሁኔታ ከተሰራ ጠላት በሙትም በቁስለኛም ጉዳት ይደርስበታል። ለእግረኛው ምቹ ሁኔታ ይጠርግለታል። ይህ ሥራ በሚገባ በመሰራቱና ጠላት በሚገባ በመመታቱ ሸሽቶ ሄዷል … በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕዝባችን የድል ብስራት እናሰማለን ›› ብለው ነበር። በተናገሩት የጀግና ቃላቸው መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የድል ብስራት አሰምተዋል።
ሌተናል ጀኔራል ዓለምእሸት በትግራይ የተቋቋመው የመከላከያ ቀዳሚ መምሪያ አባል በመሆንም የሕወሓት አመራሮችን ለማደንና የተበታተነውን ኃይሉን ለመደምሰስ ለተካሄዱ የዘመቻ እቅዶች እንዲሁም ለመከላከልና ለፀረማጥቃት የውጊያ ስልቶች ሲነደፉ የዳበረ ልምዳቸውን አካፍለዋል። ሌተናል ጀኔራል ዓለምእሸት በካበተ ልምዳቸውና በውጊያ ችሎታቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦ ወደር የሌለው የጥቁር አንበሳ ጀግና ሜዳይ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ የአየር ኃይሉ ጀግንነት እንኳንስ ወገን፣ ጠላትም ጭምር የመሰከረለት ነው። የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ደግሞ ራሳቸውም የተዋጣላቸው ጀግና አብራሪ ናቸው። እርሳቸው በተደጋጋሚ እንደተናገሩት ያልተፈቀደለት በራሪ ኃይል በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እንዳይንቀሳቀስ በዘመኑ ቴክኖሎጂ እየታገዘ ቀን ከሌሊት አስተማማኝ ጥበቃ ያደርጋል።
እንደታላቁ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በንቃት ይጠብቃል። በዚህ አኩሪ ኃይል እየተጠበቀ ግንባታው የተፋጠነው ታላቁ የህዳሴ ግድብም ኃይል ከሚያመነጭበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
በአሸባሪው ሕወሓት ላይ የተወሰደው እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን አየር ኃይሉ የጎላ ሚና ነበረው። የሕግ ማስከበር ዘመቻው በተጀመረ በሁለተኛው ቀን፣ ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም፣ ውጊያውን የተቀላቀሉት ንስሮቹ የጠላትን መሳሪያና የነዳጅ ማከማቻዎች ነጥለው በማጋየት ለእግረኛው ሠራዊት ግስጋሴና ድል አድራጊነት ታላቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። በጦርነቱ ቀጣና ውስጥ በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገዋል።
ይህ ጥንቃቄያቸውም በጦር ጥበብ ሰልጥነዋል የሚባሉት አገራት ጭምር ማሳካት ያልቻሉትን ጥንቃቄ እንዲያሳኩ አድርጓቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም አየር ኃይሉ ሠራዊትን በማጓጓዝ፣ ቁስለኛን ፈጥኖ ወደ ሕክምና በማድረስ እንዲሁም በአስቸጋሪ ስፍራዎች ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ ለምድር ኃይሉ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል። የጠላት ኃይል የአማራንና የአፋር ክልሎችን ከወረረ በኋላም እንደፈለገ እንዳይንቀሳቀስ የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል።
የጠላት ኃይል አመራሮችን ደምስሶ ፉከራቸውን መና አስቀርቷል። የጠላት ተሽከርካሪዎችን ከነጫኗቸው ተዋጊዎች ጋር ረምርሟቸዋል። አሸባሪው ቡድን ተዋጊዎቹን እንዳያስተጋባ፣ እርስ በእርስ እንዳይደጋገፍና የዘረፈውን ንብረትና የሚሸሸውን ሰራዊቱን ይዞ እንዳይወጣ ከጀርባ እያሳደዱ በመምታት የሽብር ቡድኑ መልሶ እንዳይደራጅ የውጊያ አቅሙን በመሰባበር የላቀ የግዳጅ አፈፃፀም አሳይቷል። ከእኒህና ካልተጠቀሱ ሌሎች ድሎች ጀርባ የዚህ አኩሪ ኃይል ዋና አዛዥ የሆኑት የሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ጠንካራ የአመራር ጥበብ አለ።
በመሆኑም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት የአገሪቱ ሰማይ እንዳይደፈር ላደረጉት ለጀግናው ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ የዓድዋ ድል ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ እንዲሰጣቸው ወስኖ ሽልማቱን ተቀብለዋል።
ሌተናል ጀኔራል መሰለ መሰረት ሌተናል ጀኔራል መሰለ መሰረት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በመከላከያ ሰራዊት ልዩ ልዩ ክፍሎች ግዳጃቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በፈፀመበት ወቅት ሌተናል ጀኔራል መሰለ በምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል ለተመደበው ጦር አመራር በመስጠት ላይ ነበሩ።
የሕግ ማስከበር ዘመቻው ሲጀመር የሚመሩትን ሰራዊት ይዘው ምዕራብ ትግራይ ደርሰው ጠላት ‹‹ውጊያውን ከትግራይ ውጭ አደርገዋለሁ›› ያለውን እቅዱን እንዲመክን አድርገዋል። በጠላት ከበባ ስር የነበሩ የወገን ጦር አባላትን በማስለቀቅ፣ ጠላት የወገንን የጦር መሳሪያ እንዳይጠቀምባቸው በማድረግና ሕወሓት በሱዳን ድንበር በኩል ከውጭ አጋሮቹ ጋር እንዳይገናኝ በመዝጋት የላቀ አስተዋፅዖ አበርከተዋል።
ከዚያም የመልሶ ማጥቃት ውጊያ በመምራት እስከጠላት የሥበት ማዕከል ድረስ መዝለቅ ችለዋል። ሌተናል ጀኔራል መሰለ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ግዳጆችን የመምራት ብቃት አላቸው። የጠላት ከበባና ደፈጣ ሲጋያጥማቸው ሠራዊታቸው ከበባውን ጥሶ እንዲወጣ በማድረግም ይታወቃሉ። ሌላው መገለጫቸው ደግሞ ችግሮችንና ድክመቶችን በግልጽ መናገራቸው ነው።
በ‹‹ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት›› በበርካታ ስፍራዎች ተገኝተው ጦራቸውን እየመሩ ጠላትን ደምስሰዋል። እነዚህ አበርክቶዎቻቸውና ሌሎች ገድሎቻቸው ለዓድዋ ድል ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚነት አብቅተዋቸዋል።
ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ የሚመሩት የኮማንዶና የልዩ ኃይል ሠራዊት ‹‹ውጊያ ቀያሪ›› በመባል ይታወቃል። ፈታኝና አስጨናቂ ውጊያዎች ባሉበት ቦታ ሁሉ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታና ኮማንዶዎቻቸው ተወርውረው ይደርሳሉ። በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት በጠላት ከበባ ውስጥ የነበሩ የወገን ጦር ክፍሎችን ከከበባ አስወጥተዋል።
በወቅቱ በተደረጉት የምዕራብ፣ የምስራቅና የደቡብ ግንባር ውጊያዎች ላይ ኮማንዶዎች ግዳጆቻቸውን በብቃት ተወጥተዋል። የሌተናል ጀኔራል ሹማ ኃይሎች የአየር ፀባዩና የመሬት አቀማመጡ እጅግ አስቸጋሪ በሆነባቸው አካባቢዎች ጭምር በመገኘት የጠላትን ኃይል ደምስሰዋል።
ተወርዋሪዎቹ ኮማንዶዎች የፈፀሙት ገድል በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። በተሰለፉበት ግንባር ሁሉ ድል አብሳሪ የሆኑት ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ፤ ለተወርዋሪ ኃይላቸው የሚሰጡት በሳል አመራራቸው ያስገኘው ድል የዓድዋ ድል ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥር 4/2014