አዲስ አበባ፡- በ2009 ዓ.ም እና በ2010 ዓ.ም 18ሺ ፍቺ እና 208ሺ በላይ ጋብቻ መፈፀሙን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
178ሺ የሞትና 965ሺ457 የልደት ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ግንበቶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ኤጀንሲው ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት የልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ፣ ፍቺና ጉዲፈቻ ምዝገባና ምስክር ወረቀት መስጠት መጀመሩን አስታውሰው፤ በ2009 ዓ.ም እና 2010 ዓ.ም ለ76ሺ 385 የፍቺ እና 229ሺ93 የሞት የምስክር ወረቀት ለመስጠት አቅዶ፤ 18ሺ89 የፍቺ እና 178ሺ579 የሞት ምስክር ወረቀት መስጠቱን ገልፀዋል፡፡ በተመሳሳይ ዓመታት 178ሺ የሞት፣ 965ሺ457 የልደትና 565 የጉዲፈቻ ምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡
እንደ አቶ ታምሩ ገለፃ፤ የመሰል ክስተቶች ምዝገባ ያልተለመደ መሆኑ፣ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችና ተቋሙ በማህበረሰቡ ዘንድ የፈጠሩት ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ ባህላዊ እሳቤዎችና በሌሎች ምክንያቶች የወሳኝ ኩነትምዝገባው በስፋት አልተሠራም፡፡ በተለይም ሞት እና ፍቺን በማሳወቅ ረገድ ቁጥሩ ብዙም ያልተጠበቀ ቢሆንም ተገልጋዮች በፍጥነት እያስመዘገቡና ምስክር ወረቀት እየወሰዱ መሆኑን አብራተዋል፡፡
መረጃዎቹ ለአገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አንድምታቸው የገዘፈ በመሆኑ፤ በቀጣይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በመላ አገሪቱ 19ሺ32 ቀበሌዎች ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እየተከናወነ ነው፡፡ ይሁንና በገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ምዝገባዎቹ የሚከናወኑት በቀበሌ ሊቃነመናብርት በመሆኑና እንደ አገር ደግሞ መረጃዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ ባለመሆናቸው በተፈለገው ደረጃ ውጤታማ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከ2008 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም በሚዘልቀው የስትራቴጂክ እቅድ፤ ፍቺ ለሚፈፅሙ ለ183 ሺ 229 ዜጎች፣ 3ሚሊዮን 482 ሺ 734 የልደት፤ አንድ ሚሊዮን 170ሺ የጋብቻ እና አንድ ሚሊዮን 142 ሺ 578 የሞት የምስክር ወረቀት ለመስጠት አቅዷል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 30/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር