አዲስ አበባ፡- ብዙ ሴቶችን የሚያጠቃው የጡት ካንሰርንና የማህፀን ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል መርሐግብር ቀርፆ እየሰራ እንደሚገኝ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ገለፀ። በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ሐኪሙ ዶክተር ሙሉጌታ ካሳሁን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ሰባት ወራትን ያስቆጠረው መርሐ ግብር በቅድሚያ በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 9 ጊዜያዊ ካምፕ በመስራት የተጀመረ ሲሆን፤ በአካባቢው ላሉ 110 እናቶች ምርመራ ተካሂዶ በአምስት ሴቶች ላይ የማህፀን ጫፍ ካንሰር ተገኝቷል፤ ህክምናም ተደርጎላቸው መዳን ችለዋል።
በመድኃኒዓለም ሁለተኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ከጤና ጥበቃ ጋር በመተባበር በተካሄደው ዘመቻ ለ800 ሴቶች የጡትእና የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ የተካሄደ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ በቅድም ምርመራ ላይ ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ ትምህርት ተሰጥቷል። መርሐ ግብሩ በአዲስ አበባ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል፣ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ለሚሰሩ በአማካኝ በእያንዳንዱ ተቋም ለመቶ ሴቶች ምርመራ ተካሂዷል። በተደረገውም ምርመራ ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸውን በመለየት ጉዳያቸውን እንዲከታተሉና መታከም ያለባቸውም እንዲታከሙ ተደርጓል። በዚህም ቀዶ ጥገና የሚያስፈልጋቸው እና የባሰባቸውም እንዲታከሙ ተደርጓል።
በክልል ደረጃም በጉራጌ ዞን ወራቤ ላይ መርሐግብሩ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፤ በአካባቢው ምንም እንኳ የጡት ካንሰር ያለባቸውን ማግኘት ባይቻልም፤ የማህፀን ጫፍ ካንሰር የታየባቸው ሴቶች እንደነበሩ ተናግረዋል። በተለይ አንደኛዋ ሴት፣ ካንሰሩ ባይሰራጭባትም ምልክቱ በደንብ ስለታየባት በቀዶ ጥገና ከበሽታው እንድትድን ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል። እንደ ዶክተር ሙሉጌታ ገለፃ፤ ‹‹ካንሰር ኬር›› የተሰኘውን ይህን መርሐግብር ተግባራዊ ለማድረግ የታቀደው በዚህ በሽታ የሚጠቁ አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ሐኪም ቤት የሚመጡት መዳን በማይችሉበት ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ ነው።
በተጨማሪ በሽታው በስፋት እየታየ ሲሆን፤ ቀድሞ በመመርመር ከበሽታው ለመዳን ያለው ዝግጁነት አነስተኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው። ‹‹ካንሰር ህክምና የሌለው በሽታ አይደለም። ቀድሞ ከተደረሰበት መታከምና መዳን ይቻላል›› ያሉት ዶክተሩ፤ ሆኖም ‹‹በካንሰር መያዜን ባውቅ ባላውቅ መዳን ስለማይቻል ምንም ዋጋ የለውም›› ከሚለው አስተሳሰብ መውጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በምህረት ሞገስ