አካባቢው በረሀማ ቢሆንም፤ ጠንካሮቹ ሴቶች ግን ብዙ ርቀት ተጉዘው ውሃ እየቀዱ የቤት ሥራቸውን እየሰሩና ልጆቻቸውን እያሳደጉ መኖር ለእነሱ ያን ያህል ትልቅ ተግባር አይደለም። በኦሎንጪቲ ከተማ በቦሰት ወረዳ ያገኘናቸው ሴቶች ይህ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው፡፡
ዛሬ ላይ ግን ውሃ ከመቅዳት አልፈው፤ የኢኮኖሚ አቅማቸውን አሳድገው ከባሎቻቸው ጥገኝነት ለመውጣት እን ዲሁም ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው አስፈላጊውን ሁሉ ለማሟላት በማህበር ተደራጅተው እየቆጠቡ፣ እየተበደሩ እና ባገኙት ገንዘብም የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ ራሳቸውን በመለወጥ ላይ መሆናቸውን ከአንደበታቸው ሰምተናል። በቲሪ ቤሬቴ የንጋት ኮከብ የገንዘብ ቁጠባናብድር የህብረት ሥራ ማህበር ውስጥ አባል እንዲሁም የሂሳብ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ባፈና ነዲ እንደሚሉት፤ በ1996 ዓ. ም በተቋቋመው ማህበር ተሳትፎ በማድረግ እስከ አስረኛ ክፍል የዘለቀ እውቀታቸውን በመጠቀም በሂሳብ ባለሙያነት በማገልገል ላይ ናቸው።
የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ባፈና ወደ ማህበሩ ከመቀላቀላቸው በፊት ባለቤታቸው በሚያንቀሳቅሱት የግብርና ሥራ ከመተዳደር ውጪ ተጨማሪ የገቢ ምንጭም ሆነ ቤታቸውን ሊደግፉበት የሚችሉበት ገንዘብ እንዳልነበራቸው ይናገራሉ። ወደ ማህበሩ ከመጡ በኋላ ግን ቤታቸውን እንደሚፈልጉት ማስተዳደር ከመቻላቸውም በላይ ከመሰሎቻቸው ጋር በመገናኘት የተለያዩ ሃሳቦችን በመለዋወጥና ከቤት በመውጣት ትልቅ ጥቅም ማግኘታቸውንም ያብራራሉ።
ማህበሩ ሲመሰረት በእያንዳንዱ አባል ማሳ ላይ በመሄድ እርከን በመስራት የተቦረቦሩ መሬቶችን በመሸፈን እንዲሁም የውሃ ማቆር ተግባሩን በማከናወን ነበር የሚሉት ወይዘሮ ባፈና፤ ይህ መሆኑ ደግሞ የራሳቸውን መሬት እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው በሚገባ ማወቃቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚያም በወር አምስት ብር በማዋጣት ከሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ገንዘብ መቆጠብ እንደተማሩም ነው የሚናገሩት።
«ሰዎች ለውጥ ማምጣት የሚችሉት በማህበር ተደራጅተው አንድ መሆን ሲችሉ ነው፤ ምክንያቱም ቀድሞ በአካባቢው አንዲት ሴት ገንዘብ ቢቸግራት የምታደርገው ወደ አራጣ አበዳሪ በመሄድ መበደር ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ወለዱ ብቻ ከፍተኛ ስለሆነ በችግር ላይ ችግር መጨመር ነበር፡፡ ከዚህ መጥፎ አካሄድ ለመውጣትም በማህበሩ ገንዘብ ቆጥበን መበደራችን ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶልናል» ይላሉ። እርሳቸውም በየዓመቱ ከማህበሩ ያስቀመጡትን ገንዘብ በመበደር ቤተሰባቸውን እየደገፉ እንዲሁም አንዳንዴም ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና አርም ማጥፊያን በመግዛት ምርታማነታቸውን እያሳደጉ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ዘመኑ ጥሩ ነው የሚሉት ወይዘሮ ባፈና፤ የትኛዋም ሴት ብትሆን እቤት ተቀምጣ የሰው እጅ ከምታይ ለልጆቿ መሟላት የሚገባውን ከምታጎል በማህበር ተደራጅታ ብትሰራ መልካም ነው ሲሉም ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።
ሌላዋ የማህበሩ አባል ደግሞ ወይዘሮ ደብሪቱ በሻህ ናቸው። እርሳቸውም እንደሚሉት፤ በቲሪ ቤሬቴ የንጋት ኮከብ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ማህበር አባል ሆነው በመቀላቀላቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት ትልቅ ለውጥ ማምጣታቸውንና ለዚህ ለውጥ መምጣት ዋናው ምክንያት ከሚያገኟት ገንዘብ ጥቂቷን ወደ ማህበሩ አምጥተው መቆጠባቸው መሆኑን ይናገራሉ። «ሴቶች በቤትም በውጪም በርካታ ጫና አለብን» የሚሉት ወይዘሮ ደብሪቱ፣ በዚህ ማህበር አማካይነት ግን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ከማሟላት አልፈው አባወራቸውን በመደገፍ ላይ ስለመሆናቸውና እርሳቸውም ሁሌም በየዓመቱ ሰኔ ወር ላይ የቆጠቡትን በመበደር ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እየገዙ ማገዝ መቻላቸውን ነው የሚያስረዱት።
የሰባት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ደብሪቱ እራሳቸውን በማነቃቃት ገንዘብ ቆጥበው የኔ የሚሉት ነገር በማስቀመጣቸው፤ አራት ልጆችን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ማስመረቅ መቻላቸውን እንዲሁም ሌሎቹ በጥሩ ሁኔታ ምንም ሳይጎልባቸው እየተማሩ አልፈው ተርፈው የልጅ ልጅ እያሳደጉ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ሴቶች ገንዘብ መቆጠባቸው ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረጉም በላይ ልጆቻቸው የእነሱን ፈለግ ተከትለው ቁጠባን እንዲማሩ ያደርጋቸዋል፤ ይህ ደግሞ እንደ አገርም እድገትን የሚያመጣ ነው ካሉ በኋላ በማህበር የተደራጁም ሆነ ያልተደራጁ ሴቶች እራሳቸውን ከጥገኝነት ለማላቀቅ ትልቁ መፍትሔ ከሚያገኙት ገንዘብ ትንሽም ቢሆን ማስቀመጥ መቻላቸው መሆኑን አብራርተዋል።
ዘንድሮ ሴቶች በመንግሥት በኩል እያገኙ ያሉት ትኩረት ጥሩ ቢሆንም፤ በቁጠባ በኩል ስልጠና ቢሰጥ እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ቢሟሉ መልካማ መሆኑንም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። ወይዘሮ ዛሊካ አደም በቦሰት ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ፤ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በቲሪ ቤሬቴ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ያለው የንጋት ኮከብ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ማህበር ከሌሎች በተሻለ እንቅስቃሴን እያደረገ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ባልና ሚስት ተሳስበው በመበደር የጋራ ቤታቸውን እየገነቡ ልጆቻቸውን እያስተማሩ በመሆኑ ነው ይላሉ። በወረዳ ደረጃ ሴቶች ከቤት ወጥተው አደባባይ እንዲውሉ እንዲሁም የእኔ ብለው የሚያዙበት ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ በቁጠባና ብድር ማህበራት አማካይነት ትልቅ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ወይዘሮ ዛሊካ፤ ይህ ጅምር ደግሞ ተጠናክሮ ዩኒየን ደረጃ እንዲደርሱ፤ በሴቶች ላይ ከሚሰሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ላይ የሚታይ ሥራ ተሰርቷል ባይባልም እንደ ጅምር ግን ከወርልድ ቪዥን ጋር በመተባበር በማህበር ያልተደራጁ ሴቶች በመንደር ቁጠባ ራሳቸውን እንዲችሉ ሳጥኖች እየታደሉ ይገኛሉ፤ ካሉ በኋላ እነዚህን ሴቶች ደግሞ በሂደት ወደ ማህበር በመቀላቀል ተጠቃሚነታቸውን የማስፋት ሥራ ለመስራት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት። እንደ ወረዳ ሴቶቹ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ሆነዋል ማለት ባይቻልም ዛሬ ላይ እናት ከራሷ መቀነት ፈትታ የምትፈልገው ነገር ለራሷና ለቤተሰቧ ማድረግ ችላለች፡፡ ከዚያም ባለፉ ደግሞ መብትና ግዴታዋን በሚገባ ማወቅ ችላለች ይህ ደግሞ ትልቅ ግብ ነው ማለት ይቻላል ይላሉ ወይዘሮ ዛሊካ።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በእፀገነት አክሊሉ