ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ‹‹ስሙኒ›› (ሃያ አምስት ሳንቲም) ለችግራቸው መፍትሄ እንደሚሆን በማመን ነበር በየሳምንቱ ሐሙስ እለት ማጠራቀም የጀመሩት። አንዳንዶች ጀምረው ትተውታል፤ ‹‹ተስማምቶናል›› ያሉት ደግሞ ዘልቀውበታል። ከስሙኒ ወደ ሁለት ብር፣ ከዚያም ወደ ሦስትና አምስት ብር በማሳደግ ዛሬ ላይ 50ብር መድረስ የቻሉት የተስማምቶናል የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር አባላት መቆጠባቸው አኗኗራቸው እንዲሻሻል ሚናው የጎላ እ ንደሆነይናገራሉ።
በደቡብ ክልል፣ ጉራጌ ዞን፣ ቸሃ ወረዳ፣ እነአቴ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት 70 ሴቶች በ2002 ዓ.ም ማህበሩን ሲመሰርቱ ለችግራቸው ምርኩዝ እንደሚሆንላቸው በማመን እንደሆነ ይገልጻሉ። ከማህበሩ አባላት አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ላቀች ደንድር እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ ከቁጠባም ባለፈ የብድር አገልግሎት ያገኛሉ። በቆጠቡት ገንዘብ የጓሮ አትክልታቸውን ያለሙበታል። ኑሯቸውንም አሻሽለውበታል። ብድር ወስደው ትርፋማ ከሆኑ በኋላ ይመልሳሉ።
በቅርቡም ስደስት ሺህ ተበድረው ለአራት ልጆቻቸው ማስተማሪያ እንዳዋሉትም ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ ሁለቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመሆናቸው ድጋፍ ለማድረግና ያለምንም መሳቀቅ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን እንዳሟሉላቸው ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉት፤ ወደፊት የፍራፍሬ መደብር እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ከእለት ጉርስ አልፎ ለገበያ ፍጆታ እንዲውልም መስራት ይሻሉ።
አትክልትን ወደሌላው አካባቢ ማስጫን ድረስ ህልም አላቸው። ለዚህ ደግሞ ብዙዎቻቸው የተማሩ ባለመሆናቸው ተገቢ የሆነ ስልጠና ቢሰጣቸው ይፈልጋሉ። የማህበሩ ጸሐፊ ወይዘሮ አበራሽ ዘርጋ በበኩላቸው እንደሚሉት በመቆጠባቸው ከመጠቀማቸው በተጨማሪ እርስ በርስ በሚያደርጉት ውይይትም ደስተኛ ናቸው። ‹‹ድንችና ጎመን አመርታለሁ፤ ስንዴም እዘራለሁ። ልጆቼን አስተምራለሁ›› ይላሉ።
ወይዘሮ አበራሽ የሸክላ ንግድም ያከናውናሉ። እምድብር ገበያ በመሄድ ጀበናና ድስት ገዝተው ባሉበት ቀበሌ ይሸጣሉ። ‹‹ወደፊት ቁጠባዬ ከፍ ቢል ሱቅ የመክፈት ዓላማ አለኝ፤ ከማህበሩ አባላት ጋር በመሆንም ወፍጮ ቤት መክፈት እፈልጋለሁ›› በማለት ተናግረዋል። ባለቤታቸው በሽመና ሥራ የሚተዳደሩ ሲሆኑ፣ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ እንደሚመካሩና እንደሚደጋገፉ ገልፀውልናል። ‹‹ለወጣት ሴቶች የምመክረው ቆጥቡ፤ የቆጠበ ለነገ ኑሮው ስኬት መንገድ ነው።›› ብለዋል።
‹‹እኔ እስካሁን አንድ ሺ ብር ቆጥቤያለሁ። የተበደርኩት ደግሞ ስድስት ሺ ብር ነው፤ እሱንም ለንግዴና ለአትክልት ማልሚያ አውዬ ተጠቃሚ ሆኛለሁ›› ብለዋል። ወይዘሮ ብዙነሽ ግርማ ልክ እንደ ሌሎቹ ሁሉ መስራች አባል ናቸው። ድንች፣ ቀይስር፣ ካሮት፣ ሽንኩርትና ቲማቲም በጓሯቸው የሚያለሙ ሲሆን፣ በማሳቸው ደግሞ ገብስ ያመርታሉ። እስካሁን ስድስት ሺህ ብር ያህል ቆጥበዋል።
እስከ 4 ሺ ብር በመበደርም ከአትክልቱ ጎን ለጎን ሻይ ቤት በመክፈት ብስኩቱንም ሻዩንም በመሸጥ ላይ ይገኛሉ። ‹‹ስድስት ልጆች አሉኝ። ድሬያለሁ፣ ኩያለሁ። የልጅ ልጅም አይቻለሁ። እህት፣ ወንድም፣ እናትና አባት የለኝም፤ ከባለቤቴ ጋር እና ከልጆቼ ጋር በመተሳሰብ እንኖራለን። በመቆጠቤም ደስተኛ ህይወት በመምራት ላይ እገኛለሁ›› ሲሉም ተናግ ረዋል። ‹‹እኔ ከዚህ ቀደም ልብስ እንኳን ይቸግረኝ ነበር። በማህበሩ ውስጥ አባል ከሆነች ጓደኛዬ ነበር ለምኜ የምለብሰው።
አሁን ግን ለውጥ አግኝቻለሁ። ሌሎችም እንደ እኔ ተጠቃሚ ለመሆን ቆጥቡ ነው የምለው›› በማለትም ስለ ቁጠባ ጥቅም ይናገራሉ። የማህበሩ ሰብሳቢ ወይዘሮ ምስጋነች ፈረጃ እንደሚሉት፤በወቅቱ ሰው እንዳቅሙ ስለሆነ ነው በስሙኒ የተጀመረው። አሁን ግን አቅማቸው ዳብሯል፤ በመሆኑም ጽህፈት ቤት በመስራት ላይ ናቸው።በወር አንዴ በመሰብሰብ በጉዳዮቻቸው ላይ ይወያያሉ። ‹‹አብዛኛዎቻችን በሸክላ ንግድ ነው የምንተዳደረው። እኔም በዚህ ዓመት አቆምኩ እንጂ በዚሁ በሸክላ ሥራ ላይ ነበር ለብዙ ጊዜ የሰራሁት።
የማመጣው ከእምድብር ነው፤ከዛ ወደ ጉመር ወረዳበመውሰድ እሸጣለሁ።››ይላሉ። የቸሃ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ወርቅታዊ ገብሬ እንዳሉት፤ በቸሃ ወረዳ በሚገኙ 38 ቀበሌዎች ውስጥ ሴቶች በግብርናውም ሆነ በሌሎች ንግዶች ላይ በመሰማራት የገቢ ማስገኛቸውን ያጠናክራሉ። በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ እናቶች አሉ።
በዶሮ እና በእንስሳት እርባታ፣እንዲሁም እህል በማምረትና የጓሮ አትክልት በማልማት፣ በጥቃቅን ንግድ በመሰማራት እየተንቀሳቀሱ ነው። አብዛኞቹም ሴቶች በህብረት ሥራ የታቀፉ ናቸው። በወረዳዋ ከሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራት መካከል ተጠናክረው በመጓዛቸው መውቂያ ማሽን፣ ወፍጮ ቤት፣ሰፋፊ መሬትን በመውሰድ እህል የሚያመርቱም አሉ። በህብረት ሥራ ማህበር እስከ 250 ሺ ብር ካፒታል ያለው ማህበር ትልቅ የሚባል ነው።ይህ እነአቴ ቀበሌ በካፒታሉ በወረዳ ደረጃ ፊተኛ ነው ተብሎ የሚታሰብ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል። እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፤በወረዳ ደረጃ የሚሰጠው ስልጠና ለሁሉም ተደራሽ አይደለም።
በአብዛኛው ስልጠና የሚሰጠው ለመሪዎቹ ነው። እነሱ ደግሞ ለአባላቱ ግንዛቤ እንዲሰጧቸው ያደርጋሉ።የሴቶች ጉዳይ መዋቅር በቀበሌ ደረጃ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት ትልቅ ሚና ያለው ነውና።ሁሉንም ተደረሽ ለማድረግም ወሳኝ ነው። ድጋፍም ለማድረግ ያስፈልጋል። ኃላፊዎ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት የማህበሩ ጠቅላላ ካፒታል ከሦስት መቶ 50 ሺ በላይ ሆኗል። አባላቱም 150 ደርሰዋል።የተቆጠበው ብርም በአግንዩት የህብረት ሥራ ማህበር ነው የሚቀ መጠው።የማህበሩ አባላትም ወደፊት በአካባቢያቸው ያሉ ሴቶች እንደ ወፍጮ ቤት፣ዳቦ ቤትና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በአስቴር ኤልያስ