የሃያ ሰባት ዓመቱ የሕወሓት የበላይነት በወጣቶችና በለውጥ አመራሩ ብርቱ ትግል አክትሞ ኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ በጀመረች ማግስት የፈነጠቀውን ብርሃን አጥፍተው ወደ ነበረችበት ዳፈና ለመመለስ የተመኙ የውጭና የውስጥ ጠላቶቿ ለቁጥር የሚታክቱ ደባዎችን ሲፈጽሙ ከርመዋል። አሸባሪው የሕወሓት ቡድንና ሸኔ በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና አኮኖሚያዊ ቀውሶችን በመፍጠር አገር የማፈራረስ ዓላማቸውን ከወሬ በዘለለ በተግባር አሳይተውናል።
ጋላቢዎቻቸው የውጭ ሃይሎችም በንጹኀን ላይ የሚፈጽመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አይተው እንዳላዩ በመሆን፤ እልፍ ሲልም ያላቸውን ዓለማቀፍ ተሰሚነት ተጠቅመው በመንግሥት ላይ ጫና በመፍጠርና የአሸባሪ ቡድኖቹን እኩይ ድርጊቶች ከማውገዝ ይልቅ በማወደስ ምሽግ ሆነዋቸዋል።
ለውጡ ጥቅማቸውን የነካባቸው የውጭና የውስጥ ጠላቶች ጥምረት ፈጥረው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቢረባረቡም በውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን በማጠናከር ሴራቸውን እየመከቱ ይገኛሉ።
በሀገር ውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ከደጀን እስከ ግንባር ባሉ አደረጃጀቶች ተሰልፎ አገሩ በእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝና በባንዳዎች እጅ እንዳትወድቅ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሲከፍል በውጭ ሀገር የሚኖረው ወገኑም በ/#NO MORE/ ንቅናቄ የምዕራባውያኑን ጫና የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎችን በማድረግ ዓለም እውነታውን እንዲገነዘብ አድርጓል፤ በዚህም ተጽዕኖ መፍጠር ችሏል።
የውጭ ሚዲያዎች አዲስ አበባ ላይ በማነጣጠር የዲፕሎማቶች መናኽሪያ በሆነችው ከተማ የሚኖሩ የውጭ ዜጎችን ለማስበርገግና ኢትዮጵያን ከዓለምአቀፍ ግንኙነቶች ውጭ ለማድረግ ሴራ መሸረብ ከጀመሩ አንስቶ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች የከተማቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል። አሁንም ኢትዮጵያን ለማፍረስ በውጭ ሃይሎችና በውስጥ ባንዳዎች የተሸረበው ሴራ አዲስ አበባን ሰለባ እንዳያደርጋት ወጣቶቿ ነቅተው ሰላሟን እያስጠበቁ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገሩ እየገባ ያለው ዳያስፖራ በቆይታው ምንም አይነት ችግር እንዳይገጥመው ወጣቶች በበጎ አድራጎት ሥራ ታቅፈው ሊያስተናግዱት ተዘጋጅተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር መስተንግዶውንና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ ያግዛሉ ያላቸውን ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች አሰልጥኖ የሥራ መመሪያ ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የኀብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አስፋው ተክሌ በስልጠና መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያና መልዕክት አስተላልፈዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የኢትዮጵያ ነባር እሴት መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ይህንን እሴት ማጠናከር አገራዊ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያውያን መተጋገዝ፣ መተባበርና በአንድነት መቆምን ባህላቸው አድርገው በርካታ ድሎችን ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት የበጎ አድራጎት ሥራ በተቋም እንዲመራ መደረጉን ተከትሎ የአዲስ አበባ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ከባለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደጀመረ አስታውሰዋል። ወጣቶቹ ወሰን አይገድበንም በማለት በአገራችን ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉ እየሄዱ ሚናቸውን በከፍተኛ ደረጃ ሲወጡ እንደነበር አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ መሆኗንና በአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን የተረዱ የውጭ ሃይሎች ወደኋላ ሊመልሷት በማሰብ ከውስጥ ሃይሎች ጋር የሚያደርጉትን ሴራ በመቀልበሱ ሂደት የአዲስ አበባ ወጣቶች ያንዣበበውን አደጋ ቀልብሰዋል ብለዋል።
አዲስ አበባ ላይ ተጀምሮ አዲስ አበባ ላይ ይጠናቀቃል በሚል ተላላኪዎቹና ጋላቢዎቻቸው የወጠኑትን ደባ የአዲስ አበባ ወጣቶች ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመናበብና አካባቢያቸውን በንቃት በመከታተል በከተማዋ ኮሽታ እንዳይኖር አድርገዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ለመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደረግ የበጎ ፈቃደኞች ሚና ከፍተኛ ነበር። በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ በጎ ፈቃደኞች ከሚያደርጉት አካባቢን የመጠበቅ ተሳትፎ በተጨማሪ ከአርባ ሺህ ዩኒት በላይ ደም ለግሰዋል። በባንክ በማጋራት ከአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገዋል። ከሁለት ሺህ አራት መቶ ሀምሳ ዘጠኝ በላይ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች መሥራት ችለዋል። በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብ የቁስና የእውቀት ድጋፍ በበጎ ፈቃደኞች ተደርጓል ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህሕመድን ጥሪ ተከትሎ በውጭ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች አንደ አገር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ የውጭ ሃይሎች በውስጥ ተላላኪዎቻቸው አማካኝነት በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ዘርፈ ብዙ ጦርነት ለመቀልበስ በውጭም በውስጥም የሚኖሩ ኢትዮጵያውን አንድ በመሆን እየመከቱ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ዳያስፖራው ሐሰተኛ ዜናዎችን የሚዘግቡ ሚዲያዎችንና እጅ ጠምዛዦችን አደባባይ ወጥቶ በማውገዝ ለእናት አገሩ፣ ታሪክ የማይረሳው ውለታ እየከፈለ ነው። ዳያስፖራው በገንዘብ፣ በሞራል በዲፕሎማሲው መስክ ጠንካራ ድጋፍ አድርጓል። አሁንም የተደረገላቸውን ጥሪ ተከትሎ በአገራቸው ጉዳይ ለመምከርና አዲስ አበባ በአስተማማኝ ሰላም ውስጥ እንደምትገኝ፤ ለዓለም ህዝብ መልዕክት ለማስተላለፍ፤ የውጭ ሚዲያዎችን ሐሰተኛ ዘገባ ለማጋለጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው እየገቡ መሆናቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ዳያስፖራው ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ባደረገው ትግል ምስጋና እንደሚገባው የተናገሩት ኮሚሽነሩ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ለመሳተፍም ሌላ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
የቻይና እና የህንድ ዳያስፖራዎች ለአገራቸው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳበረከቱ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችም በተለያዩ የልማት ሥራዎች በመሳተፍ በአገራቸው የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ እንዲያስቀምጡ የሚጋብዝ ጥሩ አጋጣሚ መፈጠሩን ገልጸዋል። ዳያስፖራው ኢትዮጵያን ለማሳደግ በሚያደረገው ርብርብ የቀሰመውን እውቀትና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ያፈራውን ሀብት ሥራ ላይ አውሎ አገሩን እንዲያበለጽግ መድረክ ተከፍቶለታል ብለዋል።
ዳያስፖራው በማረፊያ ቦታዎች፣ በባዛር፣ በኤግዚብሽን፣ በውይይት ቦታዎችም ሆነ ለጉብኝት በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች ሁሉ ተገቢውን መስተንግዶ እንዲያገኙ የአዲስ አበባ በጎ አድራጊ ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስልጠናውን ከሚያስተባብሩና በስልጠናው ላይ ከተሳተፉ ወጣቶች ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል።
ወጣት ዳዊት ሙሉጌታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የኀብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ነው። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያ ካሏት ባህላዊ እሴቶች አንዱና ጥንታዊ ነው ያለው ዳይሬክተሩ እንደ ጅጊ፣ ወንፈል የመሳሰሉ የማኅበራዊ ትብብሮች ማሳያ እንደሆኑ ጠቅሷል። የኢትዮጵያ ህዝቦች በኢጣሊያ ወረራ ጊዜ አንድነታቸውን አጠናክረው ጠላትን ለመመከት የቻሉት ጠንካራ ማኅበራዊ አንድነት ስላላቸው ነው።
መተጋጋዝና መረዳዳቱ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለና ኢትዮጵያ የተገነባችበት እሴት መሆኑን ተናግሯል። በደርግ ዘመነ መንግሥት የነበሩት የእድገት በኅብረትና የመሰረተ ትምህርት ዘመቻዎች፤ እንዲሁም በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ጎጆ ቀልሶ ሌላ ቦታ የማስፈሩ ጉዳይ ከባህላዊ እሴቶቻችን የተቀዱ የትብብርና የመተጋጋዝ መንፈስ ማሳያዎች ናቸው ብሏል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ተቋማዊ ማድረግ ኢትዮጵያን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው በመታመኑ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሦስት ዓመት በፊት በሰጡት አቅጣጫ መነሻነት በተቋም ደረጃ እየተመራ መሆኑን ተናግሯል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሁን ባለው ወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ የአካባቢን ሰላም በመጠበቅ፣ የዘማች ቤተሰቦችን በመደገፍ፣ ደም በመለገስ ወዘተ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጿል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን አስመልክቶ ሐሰተኛ ዜናዎችን የሚያስተላልፉ ሚዲዎችን እንዲሁም አሸባሪውን ቡድን ደግፈው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና የሚያሳድሩ ዓለምአቀፍ ተቋማትና መንግሥታትን በመቃወም ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግሯል።
የኢትዮጵያን ክብር ላለማስደፈር በተለያዩ የዓለም ከተሞች ተጽዕኖ ሲፈጥሩ የነበሩ ዳያስፖራዎች ወደ እናት አገራቸው ሲመጡ የበጎ አድራጎት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችም በክብር ተቀብለው የማስተናገድ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል ብሏል።
ዳያስፖራዎች ላደረጉት ተጋድሎ እውቅናና ምስጋና እንደሚገባቸው የተናገረው ዳይሬክተሩ ይህ አጋጣሚ ያካበቱትን እውቀትና ሙያ ተጠቅመው አገራቸውን በበጎ አድራጎት ሥራ እንዲያገለግሉ የሚያስችል ጥምረት ለመፍጠር የሚያግዝ ነው። በ ‹‹#NO MORE›› ንቅናቄ ያበረከቱትን አስተዋጽዖ በመልሶ ግንባታና በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን በቋሚነት በመርዳት የበጎ አድራጎት ሥራውን እንዲያጠናክሩ የሚረዳ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግሯል።
ሌላኛዋ አስተያቷን ያካፈለችን የበጎ ፈቃድ አግልግሎት ሰጪ ወጣት ሰናይት አስረስ ትባላለች። ዳያስፖራዎች እውነታውን ለዓለም ህዝብ በማሳየትና የህዝብ ድምጽ በመሆን ላሳደሩት ተፅዕኖ ምስጋና ይገባቸዋል ትላለች። የበጎ አድርጎት አገልግሎት ሰጪ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደ ባህሉ እንግዶቹን በጨዋነት ማስተናገድ እንደሚገባው ትገልጻለች።
የዳያስፖራው በሰላም ተስተናግዶ መመለስ ትልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም እንዳለው፤ በተለይም በውጭ ሚዲያዎች ስለ ኢትዮጵያ የሚነገረው ነገር ፍጹም ሐሰት መሆኑን ተረድተው የሚያስረዱበት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑንና የኢትዮጵያውያንን ጠንካራ ህብረትና አንድነት የሚያሳይ ነው። የዲያስፖራው መምጣት የውጭ ሚዲያዎች ስለአዲስ አበባ ከተማ ያሰራጩትን ዜና ውሸትነት የሚያረጋግጥ፤ የተዳከመውን የቱሪስት እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ እንደሚሆን ጠቅሳለች። እርሷም በተሰጣት የሥራ መመሪያና የአገልግሎት አሰጣጥ መሰረት እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀቷን ገልጻለች።
ወጣት ነብዩ ሙሰማ በበጎ አድራጎቱ ሥራ ለመሳተፍ ስልጠና ሲወስድ ያገኘነው ሌላው ወጣት ነው። የሚሠራው በኢትዮጵያ ደም ለጋሾች ማህበር ውስጥ በመሆኑ ወትሮም ለበጎ አድራጎት ሥራ ቅርብ መሆኑን ይናገራል። በበጎ አድራጎት ሥራ መሳተፍ ከጀመረ ወዲህ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎችን እንደሠራም ገልጿል። ዳያስፖራውን ለመቀበል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የአዲስ አበባ ከተማን ንጽህና፤ ሰላምና ጸጥታ ከማስጠበቅ የሚጀምር መሆኑን ይገልጻል። በእለቱ የተሠጠው ስልጠናም እንግዶችን በአግባቡ ለማስተናገድ ያለመ በመሆኑ ከበጎ አድራጎት አገልግሎት ሰጪው ባለፈ ማንኛውም ዜጋ የኢትዮጵያን ሰላም፣ የህዝቦቿን ቅንነት የሚገልጹ ሥራዎችን መሥራት አለበት ይላል።
የውጭ ሚዲያዎች የአዲስ አበባ ከተማ የጸጥታ ችግር እንዳለባት ሲያሰራጩ የነበረው ወሬ የፈጠራ ድርሰት መሆኑን ዓለም የሚረዳበት መልካም አጋጣሚ ነው ብሏል። ከውጭ የመጡ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ሌሎች ዜጎች በቆይታ ጊዜያቸው ምንም አይነት ችግር እንዳያጋጥማቸው ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከጸጥታው ባሻገር ዳያስፖራዎች ተገቢውን ማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ወጣቱ እግዛ ማድረግ ይኖርበታል። በትራንስፖርት፣ በማረፊያ ቦታ፣ በመዝናኛና በተለያዩ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ህገ-ወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ለሚመለከተው ክፍል መጠቆም እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። የተሰጠው ስልጠናም ወጣቱን ለማንቃት ከፍተኛ ጥቅም አለው ብሏል። ወጣቱ ዳያስፖራውን ተቀላቅለው የሚገቡ የጸረ ሰላም ሃይሉ ደጋፊዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተረድቶ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ መከታታል ይኖርበታል ብሏል።
እኛም ድምጻችንን ለዓለም ህዝብ ያሰሙልንን የኢትዮጵያ ኩራቶች በሚገባ ተቀብለን በማስተናገድ ፍቅራችንን ልንገልጽላቸው ይገባል እንላለን። ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 22/2014