አዲስ አበባ፦ የሰው ልጅ ለአካላዊ ዕድገቱ ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ መጻሕፍት ደግሞ የአዕምሮ ምግብ ናቸው። እነዚህን የአዕምሮ ምግቦች ለአንባቢዎቻቸው ለማድረስ በራቸውን ከፍተው ከሚጠባበቁት መጻሕፍት መደብሮች አንዱ በሆነው በጃፋር ቅርንጫፍ ኢማድ የመጽሀፍ መደብር ተገኝቻለሁ። አምስት በአራት በሆነች አነስተኛ መደብር ውስጥም በርካቶች ለመግዛት፣ ጠይቆ ለመሄድ፣ ጓደኛውንና/ዋን ለማጀብ ገባ ወጣ የሚሉ ይስተዋላሉ።
እኔም በመደብሩ ገባ ወጣ የሚሉትን ደንበኞችእያስተዋልኩ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ። አይኖቻቸውን ከመጻሕፍት መደርደሪያ ግራና ቀኝ በሚያማትሩ ደንበኞች መካከል ደንበኞቿን እንደየፍላጎታቸው ከምታስተናግደዋ ወጣት ጋር ለደቂቃዎች ተያየን። ወደ እርሷም ጠጋ በማለት ራሴን አስተዋውቄ የመጣውበትን ዓላማ አስረዳኋት። እርሷም ያለማንገራገር ልታስተናግደኝ ፈቃደኝነቷን በመግለፅ ደንበኞቿን አስተናግዳ እስክትጨርስ እንድታገስ ጠይቃኝ ወደ ስራዋ ተመለሰች።
እኔም በመደብሩ ውስጥ ከነበሩት ገዥዎች አንዱ ከሆነው ወጣት ጋር «ግብይት እንዴት ይሆን?» ስል ጥያቄ በማንሳት ጥበቃዬን በስራ አጅቤ ቀጠልኩ። በእጆቹ የያዘውን የልጆች አጋዥ መጻሕፍትን እያገላበጠ ከተመለከተ በኋላ፤ ጥሩ መሆኑንና የአራተኛና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ለሆኑት ልጆቹ አጋዥ መጻሕፍትን ለመግዛት ወደ መደብሩ ጎራ ማለቱን አወጋኝ።
በግል ስራ የሚተዳደረው አቶ ፍቅሩ ዓሊ፤ የመጻሕፍት ዋጋ በመወደዱ መግዛት ያሰበውን በሙሉ መግዛት እንዳልቻለና ዋጋውም ከጠበቀው በላይ መጨመሩን ገለፀልኝ። ከዋጋው ጋር ተያይዞ ከዓመት ዓመት የመጨመሩ ሁኔታ በመጻሕፍት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የደብተር ዋጋም ቢሆን ከዕለት ዕለት ውድነቱ እየጨመረ እንደመጣ በማንሳት መላ ሊፈለግለት ይገባል፤ ይህ ካልሆነ ግን እየሞተ ያለውን የንባብ ባህል ይበልጥ ይገድለዋል ሲል ሃሳቡን ገልጿል።
ከአቶ ፍቅሩ ጋር የነበረኝን ቆይታ በዚሁ አብቅቼ በመደብሩ የሽያጭ ባለሙያ ከሆነችው ሂንዲያ ሺፋ ጋር ለመወያየት ጊዜው ሆነና ቀጠልኩ። ሂንዲያ፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ የወረቀት ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ የመጻሕፍት ዋጋም አብሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የንባብ ባህሉን እየጎዳው ነው ስትል ሃሳቧን ትናገራለች።
በመሆኑም ትላለች፤ ደንበኞች በከፍተኛ ሁኔታ ያማርራሉ። ለዚህ ደግሞ ከወረቀት ጋር ተያይዞ የሚፈጠር እንደሆነ ምክንያት ታስቀምጣለች። በርካታ ደንበኞች ነበሩኝ። በአሁኑ ወቅት እነኚህ ደንበኞቼ ቁጥራቸው ተመናምኗል። ምናልባት የቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የህብረተሰቡ የንባብ ባህል መቀነስ፣ የመጽሐፍ ዋጋ እየናረ መምጣቱ እንደ ምክንያትነት ሊጠቀሱ እንደሚችሉም የግል ሃሳቧን ሰንዝራለች።
ሌላው በመጽሐፍት መደብሩ ያገኘሁት ደንበኛ በኔትዎርክ ማርኬቲንግ ሙያ ውስጥ የተሰማራ መሆኑን የገለጸልኝ ኤፍሬም በላይ ነው። ኤፍሬም፤ የወረቀት ምርት ዋጋ መጨመር የፈጠረውን ችግር መንግስት ለመፍታት አቅሙ እንዳለው ያለውን እምነት ይገልፃል። መንግስት ትልቅ አቅም አለው ብዬ አምናለሁ። መንግስት በምግብ ዘይቶችና በነዳጅ ላይ ድጎማ ሲያደርግና የዋጋቸውንም ሁኔታ በትኩረት ለመቆጣጠር ሲሞክር አስተውለናል።
መንግስት ለነዚህና መሰል መሰረታዊ ፍጆታዎች ብቻ ድጎማ ማድረጉ በቂ አይሆንም። ምክንያቱም ትውልድ የሚቀረጸው በመማርና በማንበብ ጭምር ስለሆነ፤ እውቀትን ለማሸጋገርም መጻሕፍት ያስፈልጉናል። የመማር ማስተማሩንም ሁኔታ ለመከወን ደብተር እና መጽሀፍ መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። ይህ ደግሞ የሚያመላክተው በወረቀት ላይ የሚደረገው ድጎማ እጅጉን አስፈላጊ ነው በማለት አስተያየቱን ሰንዝሯል።
ኤፍሬም ቀጠል አድርጎ፤ በዚህ ረገድ ሌሎች አገራት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ዜጎቻቸውን እንደሚያበረታቱ ጎረቤት አገር ኬኒያን ምሳሌ በመጥቀስ በወረቀት ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቅናሽ እንደምታደርግ ይናገራል። ከዚህ በተጨማሪም፤ ታክስ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የህትመት ውጤቶች የህብረተሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ ገበያ ላይ እንዲውሉ ማስቻላቸውን በስራ አጋጣሚ በሄደበት ወቅት መታዘቡን በመግለጽ በሀገራችንም መንግስት ለህትመት ሚዲያው የታክስ እፎይታ ፈጥሮ፤ ቅናሽ እንዲሁም ድጎማ ቢያደርግ የንባብ ባህሉንም ማበረታታት ነው በማለት ሃሳቡን ይቋጫል።
የህትመት ዘርፍ ሰፊ ቢሆንም እየተሰራበት አይደለም የሚሉት የዋንኮ ማተሚያ ቤት ኃላፊ ናቸው። ኃላፊዋ፤ የወረቀት ችግር ትልቅ ማነቆ እንደሆነ በመግለጽ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ ዋንኮ ማተሚያ ቤት መጻሕፍት፣ መጽሄት፣ ብሮሸርና ሌሎች የህትመት ስራዎችን እንደሚያከናውን በመጠቆም፤ የወረቀት ዋጋ መናር በህትመት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ይናገራሉ። በሀገራችን የወረቀት አምራች ድርጅቶች በሚፈለገው መጠን ያለመኖራቸው ብቻ ሳይሆን ጭራሹኑ የሉም ማለት በሚያስችል ደረጃ ላይ መሆናቸውንና ያሉት የወረቀት አምራች ድርጅቶችም ከሁለት እንደማይበልጡ ገልፀዋል።
የድርጅቶቹ በበቂ ሁኔታ አለመኖር ደግሞ የህትመት ደርጅቶችንም ሆነ የህትመት ውጤቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ይገኛል። የህትመት/ማተሚያ ቤቶቹ የሚፈልጉትን አይነት ወረቀት በሚፈለገው ጊዜና መጠን ለማግኘት ይቸገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የሚገነቡት በከፍተኛ ወጪ በመሆኑ ተጽዕኖው የጎላ ነው። የዋጋ መጨመር ደግሞ ተወደደም ተጠላ በተጠቃሚው ጫንቃ ላይ ማረፉ የግድ መሆኑን አብራርተዋል።
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የወረቀት የፓኬጂንግና ፕሪንቲንግ ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ለገሰ፤ የወረቀት ምርት ዋጋ ከጊዜ ወደጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን ይስማማሉ።
በሀገራችን ፍላጎትን ከአቅርቦት ያጣጣሙ በቂ አምራች ፋብሪካዎች አለመኖራቸውንም በምክንያትነት ያነሳሉ። የወረቀት ምርት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡ በህትመት ውጤቶች የሕብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም በማለት የችግሩ ስፋት ከዋጋ በላይ መሆኑን ይናገራሉ።
በአገር ውስጥ ያሉት የወረቀት አምራቾች በዓመት እስከ 90 ሺህ ቶን የማምረት አቅም ቢኖራቸውም፤ የሚገኘው የምርት መጠን ግን ከ60 ሺ ቶን የሚበልጥ አይደለም። አምራች ኢንዱስትሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለውን የወረቀት ፓኬጂንግ ፍላጎት ለማሟላት ያልቻሉበት ምክንያት መኖሩን በመግለፅ ችግሩን ለመቅረፍ ተቋሙ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራና መፍትሄ ለመስጠትም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢንዱስትሪዎች በኢንዱስትሪ ዞን ወይም ፓርክ እንዲጠለሉና የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዳያጋጥሟቸው በማድረግ፣ ተመጋጋቢ ስርዓት ለመፍጠር አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን በማስተዋወቅ፤ በአገር ውስጥ የሚገኙ ባለሀብቶችን በዘርፉ እንዲሰማሩ በማበረታት፤ ብሎም አገር ውስጥ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዲሰሩ ትኩረት ቢደረግ ችግሮቹ ሊቀረፉ ይችላሉ በማለት ሃሳባቸውን አብራርተዋል።
በመጨረሻም በአገሪቱ የወረቀት ምርት በሰባት ኢንዱስትሪዎችና በ60 ሺ ቶን መገደቡንና ፍላጎትን ለማሟላት ከውጪ በዓመት እስከ 150 ሺ ቶን የወረቀት ምርት እንደሚገባ በመግለጽ ለዚህም ሀገሪቷ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደምታደርግ ገልጸዋል። የሀገሪቱ የወረቀት ፍላጎት በዓመት ከ200 ሺ ቶን በላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በ2030 ዓ.ም የፍላጎቱ ደረጃ አድጎ ከሁለት እጥፍ በላይ የወረቀት ፓኬጂንግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በዳንኤል ዘነበ