መስከረም ለእኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ፀጋና በርካታ በረከትን ይዞልን ይመጣል። ሁሌም የያዝነው ዓመት ተገባዶ አዲሱን ስንቀበል በወጋገን ፈክተን በልምላሜ ተከበን በአደይ አበባ አጊጠን ነው። እኛ የራሳች የዘመን መቁጠሪያ፣ የራሳችን ፊደልና ከተፈጥሮ ጋር የምንግባባበት ልዩ ቀመር ያለን ሀዝቦች ነን። ለዚያ ነው ጉሙና ጨለማው ሲገፍ አበቦች በፍካት ሲፈነድቁ በራችንን ከፍተን በልዩ ተስፋ ተውበን ዘመኑን የምንቀበለው።
መስከረም ሲጠባ የአሮጌው ዓመትን ሽኝት የምናደርግበት ብቻ አይደለም። ልዩ ልዩ በዓላትን የምናከብርበት ለቀጣዩ ወራት እቅድ አውጥተን የህይወት ስኬት ለማስመዝገብ የምንሰናዳበት ጭምር እንጂ።
አዲስ ዓመት ሁሌም ይናፈቃል። ሁሉም የአገሬ ሰው በዚህ ግዜ በደስታ ይቅበጠበጣል። ከላዩ ላይ እርጅና የሚለውን ስሜ ገፍፎ ደምቆና አምሮ ይታያል። በሸኘው ዓመት ያገኘውን ድል በአዲሱ ደርቦ ደራርቦ ስኬታማ ለመሆን ያቅዳል። ማንፀባረቁ የፊት ገፅታው ላይ ሲገለጥ፣ ማማሩ ደግሞ ከባህላዊ እሴቱ በተቀዳው ማራኪ አልባሳት በማጌጡ ላይ ይታያል። በአጠቃላይ አዲስ ዓመት ሁሌም አዲስ ሁሌም ፍካትን የሚሻበትና “አሃዱ” ብሎ ዳግም የሚነሳበት ወቅት ነው።
መስከረም ለእኛ ብቻ አይጠባም። ወሩን ጠብቀው ውብ ባህላችንን፣ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን እንዲሁም ልዩ ልዩ መገለጫዎቻችንን ለመጎብኘት ከተለያዩ የዓለም ክፍለ አገራት ወደ ውቢቷ አገራችን የሚጎርፉ አያሌ የውጪ ዜጎች አሉ። እኛ ልዩና ብው ባህል፣ ማንነት ያለን ህዝቦች ነን። በዚህ ምክንያት ደግሞ ብዙዎች ያሉንን እሴቶች ለማየት ይናፍቃሉ። እኛም እንግዳን ተቀብለን “እሽሞንሙነንና” ዳግም ደጃችንን እንዲናፍቅ አድርገን መሸኘት የምንችል ኢትዮጵያውያኖች ነን።
ለምሳሌ ዛሬ ደመራ ነው። መላው ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የመስቀል በዓልን ለማክበር “በመስቀል አደባባይ” ተገኝተው ደመራ ደምረው በሃይማኖታዊ ስርዓት ደምቀው የሚውሉበት እለት ነው። ይሄ ክንውን በዓመት አንዴ የሚመጣ ከመሆኑ አንፃር በመእመናኑ ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም ለሚጎርፉ ጎብኚዎች፣ የሌላ እምነት ተከታዮች በሆኑ ተባብሮና ተቻችሎ የመኖር እሴት በገባቸው ኢትዮጵያውያን ጭምር የሚናፈቅ ነው።
መስከረም አንድ ሲል “አበባ አየሽ ወይ” ብለን ቢጫውን የተስፋ ምልክት ይዘን በደስታ እንደምንቀበለው ሁሉ በመስከረም 16 እና 17 ደግሞ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች “የመስቀሉን ከጠፋበት” በንግስት እሌኒ አማካኝነት መገኘትን ምክንያት በማድረግ ሌላ ብስራት ሌላ ደማቅ በዓል ኢትዮጵያ እንድታከብር ያደርጋሉ። በዚህ በዓል ውስጥ አንድነት፣ ፍቅር፣ ባህል፣ ማንነትና ውብ ስነስርዓት በጎዳና ላይ ይታያል። ዓለም ፊቱን ወደ እኛ ያዞራል። ህፃናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንት ጎልማሶች ሴት ወንዱ ሳይቀር እምነቱ በሚፈቅደው ስርዓት አምሮና ተውቦ ከነብሱ ምግብ በተጨማሪ እግረ መንገዱን ባህሉንና ታሪኩን ያስተዋውቃል። ጎብኚዎች ካሜራዎቻቸውን ደቅነው፣ አይኖቻቸውን አጉልተውና ነብስያቸውን በሙሉ በመስቀል ዓደባባይ በሚደረገው “ሃይማኖታዊ ትርኢት” ላይ ጥለው እምነት፣ ስርዓት፣ ባህል፣ ውበት፣ ኢትዮያና ኢትዮጵያዊነትን ይደመሙበታል። ምን ይሄ ብቻ በባህላዊ ልብሶቻችን ደምቀውና አጊጠው በጎዳናዎች ላይ ሽር ብትን ይላሉ።
ደመራ ሲሆን“ መስቀል ከጎለጎታ እስከ ግሸን ደብረ ከርቤ” በሚለው መፅሃፍ ላይ ደመራ ሲሆን በመስቀል በዓል እረኞችና ወጣቶች የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ይጫወታሉ፤ እናቶችና አባቶችም በተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ተሳታፊ ይሆናሉ። በቆየው የኢትዮጵያውያን ሥርዐተ ባህል መሠረት ተራው ሕዝብ ብቻ ሳይኾን፣ ነገሥታት አዲስ አዋጆችን የሚያውጁ በየቤቱና በየአካባቢው ተበታትኖ የከረመውን ሠራዊታቸውን ክተት ብለው የአደባባይ ላይ ትርኢት የሚያሳዩበት በዓል ጭምር መሆኑን ይገልፃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለመኳንቶቻቸው፣ ለካህናትና ለታላላቅ እንግዶች ግብር የሚያበሉበት፣ ከእኒህ አካላት ጋራ በሀገርና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚወያዩበት ዕለትም ነበር ።ሕዝቡም በየጎጡና በየሰፈሩ በነቂስ በመውጣት የደመራ በዓሉን በድምቀት ካከበረ በኋላ በኅብረት እየተመገበና እየጠጣ ስላለፈው ክረምትና ስለመጪው መኸር የሚጨዋወትበት ልዩ አጋጣሚ ነው ።በተለይ የሀገር ሽማግሌዎች ሰብሰብ ብለው የሚወያዩበት ዕለት እንደኾነ ይታወቃል ፡፡
የመስቀል በዓል ልዩ የሚያደርገው ሌላው ገጽታው ሰዎች በክረምት ምክንያት እርስ በእርስ ተለያይተው ከከረሙ በኋላ የሚገናኙበት ፣ እሸት የሚደርስበትና የሚቀመስበት ወቅት በመኾኑ ጭምር ነው ።ጊዜው የዘርና የአረም ሥራ የሚያበቃበት ፣ በአንጻሩ እህሉ ገና ለእሸትና ለአጨዳ የማንደረደርበት ፣ ገበሬው ከአድካሚው የክረምት ሥራ ተላቆ አንጻራዊ ዕረፍት የሚያገኝበት በመኾኑ ተለያይቶ የከረመው ወዳጅ ዘመድ ለመጨዋወትና ለመገናኘት ያመቸዋል።ኢትዮጵያውያን የመስቀልን በዓል የሚያከብሩት ብቻቸውን አይደለም፤ ዕፀዋቱም፣ እንስሳቱም ምድሪቱም ሰማዩም ከሰው ጋራ ተስማምተው ተዋሕደው ነው የሚያከብሩት ማለት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ መስቀል የጠለቀ ዕውቀት እንደነበረው የሚያሳዩ የተለያዩ ኹኔታዎች አሉ።ለምሳሌ ገበሬው ሌላው አካሉ ጥቁር /ዳልቻ/ ኾኖ ግንባሩ ነጭ ያለበት በሬውን መስቀል፣ በተመሳሳይ ላሙን መስቀሌ እያለ ነው የሚጠራቸው።ይህም ምሳሌያዊ ነው።ይኸውም አንደኛው ምክንያት የሰው ልጅ ለ5500 ዓመታት በጨለማ ከቆየ በኋላ እውነተኛ ብርሃን ያገኘው ከመስቀል በኋላ መኾኑን ለማሳየት ሲኾን በሌላ አባባል መስቀል የብርሃን ተምሳሌት መኾኑን ለማመልከት ነው። በትግራይ ሰዎች አደይ አበባን ገልገለ መስቀል /የመስቀል አጃቢ/ ብለው የሚጠሩትም ለዚሁ ይመስላል።የመስቀል ወፍን ጉዳይ ሳንረሳ ማለት ነው፡፡
ሃይማኖታዊ ስርዓት
ዛሬ የመስቀል በዓል (ደመራ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበርበት ቀን ነው። ሁሉም በየመንደሩ ባለ ክፍት ቦታ ላይ በዓደይ አበባ ያጌጠ በችቦና በደረቅ እንጨት፣ በሳርና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተዋበ አናቱ ላይ የመስቀል ምልክት ያለው “ደመራ” በጠዋት ተነስቶ የሚሰራበት ቀን ነው። ምን ይሄ ብቻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ምእመናኑ “በመስቀል አደባባይ” ተገኝተው ደመራውን አዘጋጅተው እነሱም በአንድነት ተደምረው አምላካቸውን “ለኢትዮጵያ ሰላሙን” እንዲያመጣላት አንድነቷን እንዲመልስላት የሚለማመኑበትና ፀሎት የሚያደርጉበት ቀን ነው።
ከሁሉም ደብር የሚመጡ ዘማሪያን፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ምእመናን በመስቀል አደባባይ ይገኛሉ። እጅግ ግዙፍ የሆነ ደመራ ይዘጋጃል። በሃይማኖት መሪዎች ተባርኮ፣ ዝማሬ ተደርጎ፣ ቀልብን የሚስብ እንደ ያሬዳዊ ዜማና ወረብ በመሳሰሉ ስነስርዓቶች ደምቆ ደመራውን በእሳት የማያያዝ ስነስርዓት ይካሄዳል። ሁሉም ጧፉን እያበራ እልልታው እየተሰማ አስደማሚ ትእይንት ይካሄዳል። ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በደንብ የማያውቁት ቱሪስቶች በመደነቅ እጃቸውን አፋቸው ላይ ጭነው ትእይንቱን ይታደማሉ። በአይናቸው ያዩትና በልባቸው ያስቀሩት ትውስታ ብቻ ሆኖ እንዳይቀርም ስነስርዓቱን በካሜራቸው ለማስቀረት ፎቶ ያነሳሉ፤ ቪዲዮ ይቀርፃሉ።
የዛሬው “የደመራ” ስነ ስርዓት ደግሞ ልዩ የሚያደርገው ደመራው በሚደመረበት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪው ቱሪስት በብዛት በሚታደምበት የመስቀል አደባባይ በመንግስት ከፍተኛ ወጪ ሰፊ ፕሮጀክት ተይዞ በልዩ ሁኔታ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑ ነው። የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ሲከናወን አስቀድሞ የከተማ አስተዳደሩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር ተመካክሮ ፕሮጀክቱን መጀመሩንና የአደባባዩን ይዞታና የመስቀል ደመራ አከባበርን በማያውክ ደረጃ እየተከናወነ እንደነበር የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውን ከዚህ ቀደም ሰምተን ነበር። በዚህ ዓመት ደግሞ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ አልቆና ተመርቆ ለትራፊክ ክፍት ከመሆኑም ባሻገር “ለመስቀል ደመራ በዓል” ስነ ስርዓት ዝግጁ ተደርጓል ። በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት ጃንሜዳን በተመለከተም በጊዜያዊነት ለአትክልት ተራነት እንዲውል ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ጉዳይ እንዲያበቃና ለብሄራዊ በበዓል አከባበር ዝግጁ እንዲሆን አፋጣኝ ስራዎች ተሰርተው ነበር። የመስቀል አደባባይም በተመሳሳይ እጅግ ውብና ዘመናዊ ሆኖ ተሰርቶ እና ተጠናቆ ለክብረ በዓሉ ዝግጁ ተደርጓል።
በመስቀል አደባባይ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በአልም ሆነ በጃንሜዳ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና የባህል ድርጅት ( ዩኒስኮ )የተመዘገቡ ዓለምአቀፍ ቅርሶች ናቸው። በዚህ ምክንያት የሃይማኖቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ መላው ኢትዮጰያውያን በየዓመቱ የሚከበሩት እነዚህ ስነ ስርዓቶች እንቅፋት እንዳይገጥማቸው ጋሻ መሆን ይጠበቅበታል።
መስቀል (ደመራ) የዓለም ቅርስ
ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያው “የመስቀል ክብረ በዓል” በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ዩኔስኮ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።ዩኔስኮ የመስቀል ክብረ በዓልን (Commemoration feast of the finding of the True Holy Cross of Christ) በዓለም ቅርስነት መመዝገቡንይፋ ያደረገው ፣ በማይዳሰሱ (መንፈሳዊ) ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃና ክብካቤ ላይ የሚሠራው ኮሚቴው ስምንተኛውን ጉባኤ እያካሄደባት በነበረበት የአዘርባጃኗ ባኩ ከተማ ነበር፡፡
የመስቀል ክብረ በዓል የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን የያዘ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ መምጣቱና በአገሪቱ ማኅበራዊ አንድነትንና የእርስ በእርስ ትስስርን ፣ ብዝኃነትን የሚያንጸባርቅ ፣ በበርካታ ብሔረሰቦች ባህሎች መካከል ትስስርን የፈጠረ በመኾኑ ዓለም አቀፍ መስፈርቱን እንዲያሟላ አድርጎታል።በዚህ መነሻ ቱሪስቶች ከየአቅጣጫው ወደ ኢትዮጵያ በዚህ ወር ለመግባትና ስነስርዓቱን በቀጥታ ለመታደም ይፈልጋሉ። ቀጠሮ ቀጥረውም በበዓሉ አከባበር ስፍራ ይገኛሉ።
ባሳለፍነው ዓመት የመስቀል በዓል እንደ ሁልጊዜው በደማቅ ስነ ስርዓት እንዳይከበር “የኮሮና ወረርሽኝ” እንዲሁም በአገሪቱ የተስተዋለው የፀጥታ ችግር እክል ፈጥሮ ነበር ። ዘንድሮም ቫይረሱ መዛመቱን ያላቆመ ቢሆንም በከፍተኛ ጥንቃቄ ግን ይህ ክብረ በዓል እንደሚካሄድ ይታወቃል። ካሳለፍነው ዓመት የተሻለ ስርዓትና ድምቀት እንደሚኖረውም ይጠበቃል።
ዛሬ “መስቀል ደመራ ነው” ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ የበዓሉ ታዳሚያን የሆኑት ምእመናን ፣ ስነስርዓቱን ለመመልከት ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው የመጡ ጎብኚዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስትና የግል ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ሁሉ መስቀሉ በሚከበርበት “መስቀል አደባባይ” ይተማሉ። ደመራውም የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ተስፋ የበለጠ ሊያደምቅ ይለኮሳል። መጪው ዘመን በሀገራችን ብርሀን የምናይበት ፣ ተስፋችን የሚለመልምበት፣ ሰላማችን የሚረጋገጥበት የብልጽግና ዘመን እንደሚሆን የመስቀሉ ብርሀን አመላካች ነው። እኛም መልካም የመስቀል በዓል ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች እና ታዳሚዎች እንዲሆን ተመኘን። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2014