ጅግጅጋ፡- በሶማሌ ክልል በከተማም ሆነ በገጠር ያለውን ትልቅ የኢንቨስትመንት አቅም ለመጠቀም የውጭ ባለሃብቱ እንዲሳተፍ ከማድረግ አኳያ ክልሉ ከሚያከናውነው ተግባር በተጓዳኝ የፌዴራል መንግስት በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ኤምባሲዎች ሊያግዙ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ ክልሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊያገኝ የሚችልበት ሂደትም ሊታሰብበት ይገባል ተብሏል፡፡
የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዱልፈታህ ሼክ ቢሂ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በከተማም ሆነ በገጠር ሰፊ የኢንቨስትመንት አቅም አለ፡፡ ይሁን እንጂ በሚፈለገው ልክ በተለይም የውጭ ባለሃብቶች እየገቡ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በውጭ አገራት ኤንባሲዎች ያለ ብዥታና ስጋት ውጤት ሲሆን፤ ይሄን ችግር ከማቃለልና የውጭ ባለሃብቶች ወደክልሉ እንዲገቡ ከማድረግ አኳያ የፌዴራል መንግስት ሊያግዛቸው ይገባል፡፡
ኢንቨስትሮችን ተሳትፎ ከአገር ውስጥና ከውጭ አንጻር የሚገልጹት ዶክተር አብዱልፈታህ፤ ቀድሞ ኢንቨስተሮች ሲመጡ አካባቢው የደህንነት ችግር አለ የሚል ስጋት እንደነበራቸው በመጠቆም፤ አሁን ላይ ክልሉ የትኛውም ብሔር ብሔረሰብ በሰላም የሚኖርበት ሆኖ ሳለ የአገር ውስጥ ባለሃብቱ በክልሉ ኢንቨስት ላለማድረግ የያዘው ምክንያት ግልጽ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
የውጪ ባለሃብቶች ወደክልሉ የማይገቡት ግጭት ስላለ መሆኑን ግልጽ አድርገው እንደሚናገሩ በማውሳት፤ እነርሱም ቢሆኑ አንዳንድ ጊዜ ተገኝተው ጭምር ያለውን ሁኔታ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ የእነርሱን ኤንባሲ ድረ ገጽ ሲያነቡ አንዳንድ ጊዜ ሶማሌ ክልልን “ኖ ጎ ኤሪያ” ወይም “የማይኬድበት አካባቢ” በሚል መገለጹ በክልሉ ኢንቨስትመንት ላለመሰማራታቸው እንደ አንድ ምክንያት ያነሳሉ፡፡
እንደ ዶክተር አብዱልፈታህ ገለጻ፤ እስካሁን ባለው የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ነገር ግን የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለሃብቶች ወደክልሉ እየገቡና መሬት እየሰጠናቸው በኢንቨስትመንት እየተሰማሩ ነው:፡ ሆኖም በሌሎች ክልል ከተሞች እንደሚገቡት አይነት ዓለማቀፍ ትልልቅ ኩባንያዎች ወደክልሉ እንዲገቡ ክልሉ የኢንቨስትመንት ሀብቱንና የድጋፍ ማዕቀፎችን ለይቶ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ሆኖም ኢንቨስትመንቱ በሚፈለገው ልክ እየመጣ ስላልሆነ የፌዴራል መንግስት ይሄን አስረድቶ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲመጣልን ከማድረግ አኳያ ኤምባሲዎችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሊያግዙ ይገባል፡፡
እንደ ዶክተር አብዲልፈታህ ገለጻ፤ የአንድን አከባቢ ኢንቨስትመንት ምቹ የሚያደርገው መሬቱና ያለው ሀብት ወይም ህዝቡና ቆዳ ስፋቱ ብቻ እንዳይደለመሆኑም፤ ክልሉም ወጪን በመቀነስ ለኢንቨስተሮች ትርፍ የሚያስገኙ የመሰረተ ልመት አማራጮች አሉት፡፡ በዚህ ረገድ ክልሉ እንደ በርበራና ቦሳሶ ላሉ ወደቦች ቅርበት ያለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከውጫሌ- በርበራ፤ እና ከዋርዴር- ቦሳሶ ወደቦች ያለውን ርቀት መመልከት በቂ ነው፡፡ ወደ ወደቦቹ ያለውን ጉዞ የሚያቃኑ ምቹ መንገዶችም አሉት፡፡
እንደ አገር በመጣው ለውጥም የኦብነግ ወደሰላም መመለስ፤ ክልሉ ጠረፍ ቢሆንም ለሽብር ተጋላጭ አለመሆኑም ለሰላሙ አጋዥ ነው፡፡ እናም በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚሰጉ የውጭ አካላት ተጨባጩን ሁኔታ በማስረዳት፤ ክልሉ ያሉትን አማራጮች ወደልማት ለመቀየር የክልሉን ህዝብና አመራር ለሰላምና ልማት ያለውን ቁርጠኝነት ተመልክቶ የፌዴራሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ከዚህ ባለፈ ምንም እንኳና መንግስት በዘርፉ ጉልህ ተግባር እያከናወነ ቢሆንም፤ የሶማሌ በቆዳ ስፋትም ሆነ በህዝብ ብዛት ከአራቱ ዋና ዋና ክልል ከሚባሉት ጎራ የሚያስመድበው አቅም ያለው ክልል ሆኖ እያለ አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንኳን የታሰበለት ባለመሆኑ የፌዴራል መንግስት ይሄን ሊመልስ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
ወንድወሰን ሽመልስ