የዛሬዋ ነሐሴ 16 ልጃገረዶች በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አምረውና ደምቀው በየዓመቱ አደባባይ ላይ የሚታዩበት ለእነርሱ ብቻ የተሰጠች ቀን ስለመሆኗ ይታወቃል:: በተለይ በአማራና በትግራይ ክልሎች የሚገኙ ልጃገረዶች ይህችን ቀን የሚጠብቋት በጉጉት ነው:: በዕለቱ የክት የሚሏቸውን ሁሉ ያሸበርቁበታል::
የፀጉር ሥራው፣ የባህል ልብሱ፣ የአንገት ሀብሉና አሸንክታቡ፣ የእጅ አምባሩ፣ የእግር አልቦው፣ ኩሉና የመዋቢያ አይነት ሁሉ ከቀናት በፊት ይዘጋጃል:: በዕለቱ ዘፈን የምታወጣውና አጃቢዎችም በአካባቢያቸው ይመራረጣሉ:: የባህል አልባሱ ከአካባቢ አካባቢ ቢለያይም ሁሉም የአካባቢውን መገለጫ ነው የሚለብሰው:: በባህል አልባሳቸው ላይ ከወገባቸው በታች በወንዝ ዳር የሚበቅለው ቄጤማም የሚያደርጉ አሉ:: ዘፈኑንና ጭፈራውን ማድመቂያም ከበሮ አይቀርም::
ከዚህ ሁሉ ዝግጅት በኋላ አምረውና ደምቀው አደባባይ የሚወጡት ልጃገረዶች በህብረት ሆነው በዘፈን በታጀበው ጨዋታቸው በአካባቢያቸው በየቤቱ በመዞር እንኳን አደረሳችሁ በሚለው የቅድሚያ መልእክታቸው በእያንዳንዱ ቤት በመግባት ይዘፍናሉ፤ ይጨፍራሉ፤ ተደስተው ያስደስታሉ:: ነዋሪውም ልጃገረዶቹን ተዘጋጅቶ ስለሚጠብቅ በዓሉን የጋራ ያደርጉታል:: የሚሸኟቸውም አብልተውና አጠጥተው ነው::
ጊዜው እየዘመነ በመምጣቱ ባህሉ የከተማ ይዘትም ይዟል:: በመሆኑም ልጆቹም ገንዘብ በመልመዳቸው ሰጭውም ወደዚሁ አድልቷል:: ታዲያ ሁሉም በአቅሙ ስጦታውን ሰጥቶ፣ ለአመት እንዲያደርሳቸውም ተመራርቀው ይሸኛኛሉ:: አንዳንዶች ጨዋታውን ከዋዜማው ቢጀምሩም በዓሉ ግን ከዛሬዋ ነሐሴ 16 ቀን እንደሚጀምርና እስከ አዲስ አመት ዘመን መለወጫ ድረስ እንደሚዘልቅም ነው የሚነገረው::
ትዝታዋን በአይነህሊናዋ እያስታወሰችና በዓሉ በደረሰ ቁጥር እምባዋ እንደሚመጣ ልጅነቷንና በዓሉን ወደኋላ መለስ ብላ በማስታወስ ያጫወተችኝ በሥራ ምክንያት ኑሮዋን አዲስ አበባ ከተማ ያደረገችው ወይዘሮ ትርሃስ ፍቃዱ ስለአሸንዳ በዓል በሁለት ስሜት ውስጥ ሆና ነው ያወጋችኝ:: በአንድ በኩል የልጅነት ትዝታ፣ተወልዳ ባደገችበት በመቀሌ ኩሓ አካባቢ ያሳለፈችው ከአይነህሊናዋ አይጠፋም:: በተለይም የነሐሴ ወር ለእርሷ ትልቅ ትርጉም አለው:: ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ነው የአካባቢው ልጆች የሚሰባሰቡት::
በኦርቶዶክስ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 15 ቀን ያለው ጊዜ የጾም ወቅት በመሆኑና ጾሙም የልጆች ነው ስለሚባል የአንድ አካባቢ ታዳጊዎች 16ቱን የጾም ወቅት አቅራቢያቸው በሚገኝ ቤተክርስቲያን በመሄድ የፆም ፀሎት ሥርአቱን ይካፈላሉ::የአሸንዳ በዓል የጾም ፍችውን ተከትሎ በመሆኑ ከነሐሴ 14 ቀን ጀምሮ ለዚያች ለሚናፍቋት የአሸንዳ ጨዋታ ዝግጅት ያደርጋሉ:: ከእነርሱ የሚጠበቀው እርስበእርስ ሹሩባ መሰራራትና ሥር ኩል የሚባለውን ከባህላዊ ግብአት ኩል ፈጭቶ ማዘጋጀት ነው:: ወላጅ ደግሞ አዲስ ልብስ ማሰፋት ይጠበቅበታል:: በአካባቢው ህብረተሰብ አጠራር ሽፎን በመባል የሚታወቀውን ልብስ ያሰፉላቸዋል::
የፀጉር ሥራውም ተመሳሳይ ነው:: አልባሶ የሚባለው የፀጉር አሰራር ቢኖርም የተለመደውና ልጃገረዶቹ የሚሰሩት ግን በግራና ቀኝ የጆሮ ግንዳቸው እኩል አራት ወደታች፣ የተቀረው ደግሞ ሙሉውን ወደታች ወርዶ የሚሰራውን የሹሩባ አይነት ነው:: ፀጉር ሥራው ጋመ ይባላል::ፀጉራቸውንም ቅቤ ይቀባሉ:: አንዷ ሌላዋን በመኳልና በማሳመር እርስበእርሳቸው ነው የሚዋቡት:: ውበታቸውን የሚጠብቁት በተፈጥሮ ነው:: ዘመን የፈጠረውን ተጨማሪ ፀጉር(ዊግ)፣የከንፈር ቀለም፣ፊት ለማሳመር የሚቀባባውን ነገር አይጠቀሙም:: መዋቢያ ቤት(ፀጉርቤት)አይሄዱም:: ተፈጥሮ በለገሰቻቸውና ልጅነታቸውም ውበት በመሆኑ የማንንም ቀልብ ይስባሉ:: እነርሱን ለማየትና በአጋጣሚውም እጮኛ ለመፈለግ የሚከተላቸው ጎረምሳ ይበዛል::ልጃገረዶቹ ውብ ከመሆናቸው የተነሳም ለአሸንዳ ጊዜ ያየሀትን ልጃገረድ ለእጮኝነት አትምረጥ ይባላል:: ያኔ ውብ ሆና የታየችው ልጃገረድ ከበዓሉ በኋላ ያ ውበት ላይታይ ይችላል ከሚል ጥርጣሬ የመነጨ ነው ሥጋቱ::
ወይዘሮ ትርሐስ እንዳለችው ሁሉም ለጨዋታው የሚገናኝባት ነሐሴ 16 ቀን ሌቱ ይረዝማል:: ነጋ አልነጋ ብለው ቁርስ እንኳን አፋቸው ሳያደርጉ ነው ከቤታቸው ወጥተው በሚሰባሰቡበት ሥፍራ የሚደርሱት:: የጨዋታው ጉጉት እንዳለ ሆኖ ግን የሚሄዱበት ቤት በሌሎች እንዳይቀደሙም ጭምር ነው በጊዜ የሚገናኙት:: በተለይ በአካባቢው በዕድሜም ሆነ ማህበረሰቡ ከበሬታ የሚሰጣቸው ሰው ቤት ቀድሞ መገኘት ሁሉም የሚፈልገው በመሆኑ የመጀመሪያ ለመሆን ሁሉም ይዘጋጃል:: የጨዋታ ቡድን ያላቸው ልጃገረዶች ቁጥራቸው ከ14 እስከ 16 የሚሆን ነው:: በዚህ መሠረት በየአካባቢው የተለያየ ቡድን ይኖራል ማለት ነው:: ወይዘሮ ትርሓስ እንደነገረችኝ፤ አባላቱ ከተሰባሰቡ በኋላ ቅድሚያ የሚሄዱት አቅራቢያቸው በምትገኝ ማርያም ቤተክርስቲያን ነው::‹‹ኣቲ ማርያም ፀሐይ፣ መጺኤያኮ ዛ መጽብዓዬ›› በማለት ምስጋናቸውን ያቀርባሉ:: ትግርኛው ወደ አማርኛ ሲመለስ እመቤቴ ማርያም ለበዓሉ ስላደረስሽኝ ስለቴን ላደርስ መጥቻለሁ ማለት ነው::
ከዚህ በኋላ ከትልልቅ ሰዎች ቤት ጀምረው በአካባቢያቸውና በአቅራቢያቸው በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች እየዞሩ ይጫወታሉ:: የቤቱ ደጃፍ ሲደርሱም የግቢውን በር እንዲከፍቱላቸው መምጣታቸውን የሚያመልክቱ ዘፈኖችን ይዘፍናሉ:: በሩ ተከፍቶላቸው ወደ ውስጥ እንዲገቡ ከተጋበዙ በኋላ ደግሞ ዘፈኑ ይቀየራል:: የቤቱ ባለቤቶች የመኖሪያ ቤት እና የግቢውን ውበት ያወድሳሉ:: የቤቱን ባለቤቶችም በየተራ ስማቸውን እየጠሩ ያሞግሷቸዋል:: በዚህ መልኩ ዘፈኑና ጨዋታው ይደምቃል:: የቤቱ ባለቤቶችም በጭፈራው ይቀላቀሏቸዋል::
የሚሰነባበቱት በሥጦታ ስለሆነ የሰጠ ብሩ እንደ ነሐሴ ውሃ እንዲፈስለትና ሌላም የመልካም ምኞት ምስጋና ይቀርብለታል::ይወደሳል:: ባለቤቶቹም ለሚቀጥለው አመትም በሰላም ለመገናኘት እንዲያበቃቸውና አብረው እንዲጫወቱ ቸር ተመኝተው ይለያያሉ:: በዚህ መልኩ በየቤቱ የሚመጡ ቡድኖች ስለሚኖሩ ለተቀባዮቹ መስተንግዶ ስለሚከብድ አንዳንዶች ለመሸለም ፈቃደኛ ላይሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል:: ግን ምርቃትና ምሥጋናን አይነፍጓቸውም:: ልጆቹ ደግሞ የሚፈልጉት ስጦታ በመሆኑ ሳይሰጧቸው ሲቀሩ አንተ ገብገባ ወይንም ቆንቋና፣ ስስታም የሚል መልዕክት ያለው ዘፈን ዘፍነው ይሄዳሉ:: ባህሉ ስለሆነ የሚቃወምም ሆነ የተለየ ነገር ለማድረግ የሚሞክር የለም:: በተቻለ መጠን ላለመሰደብ በሚችሉት ለመሸለም ነው ጥረት የሚያደርጉት::
ልጃገረዶቹ በየመካከልም አረፍ ብለው የየራሳቸውን ጨዋታ ይጫወታሉ:: ቀኑ የእነርሱ በመሆኑ ማንም ከልካይ የላቸውም:: ሳምንቱን በሙሉ በልጁ ላይ ጫና የሚያሳድር ወላጅም የለም:: ወይዘሮ ትርሓስ ከተማ ቀመስ አከባቢ ውስጥ በመሆኗ ከገጠሩ ለየት ባለም ከመኖሪያ ቤት ውጭ የመሄድ ልምድ አዳብረዋል:: በአካባቢው የቱሪስት መስህብ በመኖሩም ጎብኝ ቱሪስቶች ይገኛሉ:: እነርሱ ያሉበት ድረስ በመሄድ በአንዳንድ ንግድ ተቋማት ውስጥም እንዲሁ በመግባት ይጫወታሉ:: በተለይም የውጭ ሀገር ቱሪስቶች በአድናቆት ነበር የሚያዩዋቸውና የሚደሰቱት:: ልጃገረዶቹን የሚገላግላቸው ምሽት ነው:: ድካም የሚባል ነገር የለም:: ምግብ ስለመብላታቸው እንኳን አያስታውሱም:: በጨዋታው ደስታ ይጠግባሉ::
ልጃገረዶቹ እንዲህ በአካባቢያቸውና ከአካባቢያቸው ርቀው ሲሄዱ የኋላ ደጀን ወይንም ጠባቂ አላቸው:: በሰፈሮቻቸው ወንዶች ነው የሚጠበቁት የሌላው ሰፈር ወንድ ሊተናኮላቸው ስለሚችል ነው ጥበቃው:: መተናኮሉ ግን ክፋት ያለው ሳይሆን ከፍቅር የመነጨ ነው:: በዚህ አጋጣሚ ከመካከላቸው በሰፈሯ የሚወዳት ልጅ በሌላ ሰፈር ልጅ ልትታይ ስለምትችል የሰፈር ወንዶቹ ጥበቃም በሌላ የሰፈር ወንድ እንዳትወሰድ ነው::
ከጨዋታው ከቀናት በኋላ ልጃገረዶቹ ተሰባስበው የሚያደርጉት ነገር የሰበሰቡትን ገንዘብ መጠን ማወቅና መከፋፈል ነው:: ምንም እንኳን ዋናው የልጆቹ ደስታ ጨዋታው እና ባህሉን ስለሚወደው ትኩረቱ በዚያ ላይ ቢሆንም ምን ያህል ገንዘብ ይደርሳቸው ይሆን? በገንዘቡስ ምን ያደርጋሉ? የሚለውንም ማወቅ ያጓጓል::
ወይዘሮ ትርሓስ እንዳለችው፤ የገንዘብ መጠኑ በየአመቱ ይለያያል:: በአንድ ቀን እስከ አምስት መቶና ከዚያ በላይ ይገኛል:: የገንዘቡ መጠንም ከፍ እያለ የሚሄደው እነርሱም ከፍ እያሉ ሲሄዱ ነው:: የሚሄዱበት ሥፍራ ይበዛል:: በታዳጊነታቸው ግን ገንዘቡ አነስተኛ ነው:: ተከፋፍለው ማስቲካ፣ ከረሜላ ገዝተው ይደሰታሉ:: ከፍ ካሉ በኋላ ግን የገንዘብ መጠኑም ከፍ በማለቱ ከላዩ ላይ ለቤተክርስቲያን ይሰጣሉ:: ይህ ሁሉም ነፍስ አውቆ ቁምነገር መጀመሩን ያሳያል:: ወይዘሮ ትርሐስ የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን እስክታጠናቅቅ ድረስ አሸንዳ ተጫውታለች:: ከዚያ በኋላ ቆይታዋ በከፍተኛ ትምህርት ተቋምና በሥራ ዓለም በመሆኑ ከጨዋታው ተለይታለች:: በየዓመቱ ግን የልጅነት ትዝታዎችዋ አልተለዩዋትም:: ቀኑን በአልባሳት በመዋብና ከጓደኞችዋ ጋር ተገናኝታ በመጫወት ለማስታወስ ጥረት ታደርጋለች::
ወይዘሮ ትርሐስ አንዳንዴም የልጅነቷን ጊዜ ስታስታውስ እምባዋን መቆጣጠር ያቅታታል:: የሁኑ ደግሞ የባሰ ሆኖባታል:: ቀደም ሲል በልጅነት በአሸንዳ ጨዋታ ላይ የምትጫወተው ዘፈኑ፣ጭፈራውንና ጓደኞችዋን በማስታወስ ነበር:: በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረው የፀጥታ ችግርና በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አሸባሪ ቡድን ተብሎ የተፈረጀው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሃት) በከፈተው ጦርነት በዓሉ ሊከበር ቀርቶ ድባቡም አለመኖሩ እጅግ ያሳዝናል:: ድርጊቱንም ትቃወማለች::
እርስዋ እንዳለችው ፖለቲከኞች እንዲህ የህዝብ ደስታ የሆነውን በዓል ከህዝብ በመንጠቅ መሆን የለበትም:: ‹‹አሸንዳ የሴቶች የነፃነታችን የእምነታችንም መገለጫ ነው:: ማንም ሊነጥቀን አይገባም:: መደሰት በራሱ ትልቅ ፀጋ ነው:: ሰላም፣ መተሳሰብ የምናበስርበትም ነው:: ዓለም ከእኛ የሚማረው ድንቅ ባህላችን ነው›› በማለትም የሆነውን በቁጭት ትናገራለች:: በዝምታ መታለፍም የለበትም ትላለች:: በተለይም ሴቶች ይህን ድንቅ የሆነውን የነፃነታቸውን በዓል ለማስመለስ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው እንዲሁም ፖለቲካና የማህበረሰብ ባህልና ልማዶች መለያየት እንዳለባቸውም ታምናለች::
ወይዘሮ ትርሓስ እንዳለችው፤ ከማህበረሰብ አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ገጽታ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና ሁሉም በየአካባቢው ባህሉን ለትውልድ ለማሸጋገር በደመቀ ሁኔታ በየአመቱ እያከበረ ባለበት በአሸባሪው ትህነግ ዘንድሮ ልጃገረዶች በዓላቸውን ሳያከብሩ መቅረታቸው የጉዳቱ አንዱ ማሳያ ነው::
የባህል ጨዋታ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ በሌላም ስያሜ የሚጠራው ስያሜው ይለያይ እንጂ ተግባሩ ግን ተመሳሳይ ነው:: እንደሀገርም በተንቀሳቃሽ ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት የባህል፣ ሳይንስና ትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብም እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ይታወሳል:: ዛሬ ግን ያንን ደማቅ የልጃገረዶች የባህል ጨዋታ ከቱባው ቦታ ለማየት አልታደልንም:: ምክንያያቱ ደግሞ ትህነግ ነው::
ህወሃት፣ ጦርነት በመጫሩ ምክንያት ነሐሴ 16 ቀን ልጃገረዶች የሚጫወቱት ባህላዊ ጨዋታን አስቀርቷል:: ሀገርን በማስከበር ግዳጅ ላይ ነው የምንገኘው››ሲሉ የጎንደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ነግረውናል:: ዶክተር ሙሉቀን እንዳስታወሱት፤ በሰቆጣ አሸንዳ፣ በላልይበላ አሸንድዬ፣ በማዕከላዊ ጎንደር ሶለል በሚል ስያሜ፣ እንዲሁም በደቡብ ጎንደር የቡሄ በዓል እጅግ ደማቅ በሆነ ሥነሥርአት ነው የሚከበረው:: በትግራይ በተንቤን አካባቢም አሸንድዬ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች ይጠቀሳል:: በዓሉ በድምቀት የሚከበርባቸው በሙሉ የፀጥታ ችግር ያለባቸው በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ምንም አይነት የበዓል እንቅስቃሴ የለም::
በዓሉን ደረጃ በደረጃ ተንቀሳቃሽ የባህል ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ እንደሚመዘገብ በሂደት ላይ እንደነበርም ያስታወሱት ዶክተር ሙሉቀን፤በቱሪዝም ኢንደስትሪው በኩል ከነበረው ሚና በተጨማሪ ማህበረሰብን ከማህበረሰብ በማቀራረብና አብሮነትን በማሳደግ ሚናው የጎላ ነበር:: እንዲህ የማህበረሰብ እሴትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባለው ላይ ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ካሳደረው ጫና በላይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከፈተው ጦርነት እጅጉን እንደጎዳው ተናግረዋል::
በሌላ በኩል የበዓሉን ደማቅነትና ለቱሪዝም ኢንደስትሪውም ያለውን አበርክቶ የገለጹት ደግሞ የጎንደር የሆቴሎች ማህበር ፕሬዚደንት አቶ አማረ አጥናፉ ናቸው:: እርሳቸው እንዳሉት፤ በደቡብ ጎንደር ደብረታቦር አካባቢ የሚታወቀው አሸንድዬ የሚባለውን የልጃገረዶች የባህል ጨዋታ ከዘመን መለወጫና የመስቀል በዓላት ባልተናነሰ ደማቅ እንደሆነና በዓሉንም ለመታደም ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ወደሥፍራው ይሄዳሉ እንቅስቃሴውም ለቱሪዝም ኢንደስትሪው መነቃቃት ተስፋ አሳድሮ ነበር፡ዛሬን ያጣነው ነገር የጦርነትን አስከፊነት ማሳያ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም::
ለምለም መንግስቱ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2013