ጊኒዎርም ዛሬም ስጋት ነው
አካባቢው በርሃማ ከመሆኑ የተነሳ ውሃ ከህይወትም በላይ ህይወት ሆኖ አስፈላጊነቱ ፍንትው ብሎ የሚታይበት ነው፤ ውሃን እየተጎነጩ ካልሆነ የጸሀዩን ንዳድና የአካባቢውን ሙቀት መቋቋም አይቻልም። ይህ እንግዲህ በጋምቤላ ክልል በአቦቦ ወረዳ ያለ እውነት ነው። ይህ ወረዳ ለመጥፋት የተቃረበው የጊኒ ዎርም በሽታ ያገረሻል ተብሎ ስጋት ያሳደረበት ስፍራ ሆኗል።
በዚህ አካባቢ ቁጥራቸው በርከት ያሉ አልሚ ባለሀብቶች የአካባቢውን ነዋሪዎች በማሳተፍ የእርሻ ስራን ስለሚያከናው ለሰራተኞቻቸው የሚያቀርቡት ውሃ ጥራቱ ያልተጠበቀ መሆኑ በሽታው ከስጋት አልፎ ዳግም በሰዎች ላይ እንዳይገኝ ጠንካራ ሥራን ጠይቋል። የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የመስክ ምልከታና የውይይት መድረክ ላይም ችግር ሆኖ የተነሳው ባለሀብቶች በሚያለሟቸው መሬቶች ላይ ለሚያሳትፏቸው ሰራተኞች ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አለማቅረባቸው ነው።
ሙላት የእርሻ ልማት ውስጥ በመስራት ላይ ያለው ወጣት ኦጋለ ሌሬ እንደሚለው አካባቢው በጣም ሞቃት ከመሆኑ የተነሳ ውሃ ከአስፈላጊም በላይ ቢባል ማጋነን አይሆንም ይላል፤ ሆኖም አሰሪዎቻችን የሚያቀርቡልን ውሃ ጥራቱን የጠበቀ ባለመሆኑ፤ በተለይም ለጊኒ ዎርም በሽታ እንዳንጋለጥ ስጋት ቢኖርብንም እስካሁንም ጥራት የሌለውን ውሃ ከመጠጣት አልተቆጠብንም።
እንደ ኦጋለ ገለጻ ይህ ከጉድጓድ የሚወጣ ውሃ ከጊኒ ዎርም በሽታ ባሻገር የተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎችን እያስከተለባቸውና በየጊዜው እየታመሙ ቢሆንም አሰሪዎቻቸው ጉልበታቸውን ብቻ ስለሚፈልጉ ለሚጠጡት ውሃ ትኩረት መንፈጋቸውን ይናገራል። መንግሥት ጊኒ ዎርምን አጠፋለሁ ቢልም በዚህ መልኩ ግን በሽታው የሚጠፋ እንደማይመስለውም ይናገራል።
«ጫካ ስንሄድ በኬሚካል ተረጭተዋል የሚባሉ ኩሬዎችን እንዲሁም ከሥራ ወደ ማረፊያ ስንመለስ ደግሞ ማጥለያ (ፊልተር) እንጠቀማለን፤ እንደዚህም ሆኖ ግን ውሃው ጽዳቱን የጠበቀ ባለመሆኑ ጊኒ ዎርም ባይዘንም ለሌሎች የጤና ችግሮች ግን ከመዳረግ አልዳንም» የምትለው ደግሞ ወጣት አቡሩ ቾንጌ ናት ።
እንደ አቡሩ ገለጻ በአቦቦ ወረዳ ጊኒ ዎርም ባይታይም በአጎራባች ወረዳዎች ላይ እንዳለ እንደሚሰሙና ይህም እንደሚያሰጋቸው በመናገር ችግሩን ማለፍ የሚቻለው ደግሞ የእርሻው ባለቤቶች ፍቃደኛ ሆነው የተጣራ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሲያቀርቡ ብቻ መሆኑን ታብራራለች።
አቶ ሙላት ገብረ ስላሴ የሙላት እርሻ ልማት ባለቤት ሲሆኑ፤ በክረምት ጊዜ ከሁለት መቶ እስከ 250 ጊዜያዊ ሰራተኞች እንዲሁም 23 በቋሚነት የሚሰሩ ወጣቶችን ያስተዳድራሉ። እርሻ ልማቱ ሰራተኞቹን ከጊኒ ዎርም በሽታ ለመከላከል ንጹህ የመጠጥ ውሃ ቀድሞ በአካባቢው ካሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ያመጡ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ግን በማሳው የውሃ ጉድጓድ መቆፈሩን ይገልጻሉ።
ለወደፊቱም 50 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፈር አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ሙላት፤ እስከዚያ ድረስ ግን ሰራተኞች የተጣራ ውሃ ለማግኘት እንዲችሉ ማጣሪያ ቀሰም በደረታቸው ላይ በማሰር እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገና የሚያቀርቡት ውሃም ፍጹም ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን አቶ ሙላት ተናግረዋል።
አቶ ሙላት ይህንን ይበሉ እንጂ በስፍራው ያየነው 8 ሜትር ጥልቀት ያለው የውሃ ጉድጓድ በሰው ጉልበት የተቆፈረ ፣ዙሪያው በጭራሮ አጥር የታጠረና እጅግ የደፈረሰ ፣ሽታ ሊያመጣ የተቃረበ የውሃ ጉድጓድ ነው። ባለሀብቱ ግን ውሃው ዳስ የተሰራለትና ጥራቱን የጠበቀ ከጊኒ ዎርም ነጻ የሆነ ነው በማለት የመከራከሪያ ሀሳባቸውን አቅርበዋል።
በስፍራው የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩት፤ ውሃው እንደተባለው ጥራቱን የጠበቀ ሳይሆን ፍጹም ለመጠጥ የማይሆን ከጊኒ ዎርም ባሻገር ለተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች ሊያጋልጥ የሚችልና እንኳን የሰው ልጅ እንስሳቱም ይህንን ውሃ መጠጣት የለባቸውም።
ሚኒስትሩ ባለሀብቱ ለሰራተኞቻቸው ተስማሚ የሆነና ጥራቱን የጠበቀ ውሃ ማቅረብ እንዳለባቸው ተናግረው ይህ መሆኑ ደግሞ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከጊኒ ዎርም ከመከላከል ባሻገር አገሪቱ ከበሽታው ነጻ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ በአካባቢው ላይ በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ ሁሉ ከክልሉ ውሃ ልማት ቢሮ ጋር በመነጋገርና በጋራ ተግባብቶ በመስራት እስከ 50 ሜትር ድረስ ጥልቀት ያለው የውሃ ጉድጓድን መቆፈርና ከብክለት የጸዳ እንዲሁም የታከመ ውሃን ለሰራተኞቻቸው ማቅረብ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ይህ የስራ መመሪያ ተግባራዊ መደረግ አለመደረጉ የቅርብ ክትትል እንደሚደረግበት ገልጸው ባፋጣኝ ወደ ስራ በማይገቡ ባለሀብቶች ላይ ግን ጤና ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳሉ።
የዓለም ሎሬት እንዲሁም የጊኒ ዎርም የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን በበኩላቸው አገሪቷ ያላት ትልቁ ሀብት ህዝቦቿ በመሆናቸው በጤንነታቸው ላይ ይህን መሰሉ አደጋ ሲጋረጥ ምንም ዓይነት ድርድር አያስፈልግም፤ በመሆኑም ባለሀብቶቹ አገሪቱን ከማልማት ባሻገር ለማህበራዊ ኃላፊነታቸውም ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ብለዋል ።
እንደ ዓለም ሌሬት ዶክተር ጥበበ ገለጻ በዚህ መልኩ የሚሸት ውሃ ከጉድጓድ እየተቀዳ ለሰራተኞች ማቅረብ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር በመሆኑ ባለሀብቶቹ ወደ ክልሉ እንዲሁም ወደ አካባቢው ሲመጡ የገቡትን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ለሰራተኞቻቸው ጤንነት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
ፀገነት አክሊሉ