አሸባሪነትም ወግ ሆነና እየተፎከረ ነው። መዋጋት ለአገር መሆኑ ቀርቶ በተቃራኒው እየሆነ፤ በባዶም ቢሆን እያሸለለ ይገኛል። ሕፃናትን ለእሳት እየማገዱ አካኪ ዘራፍ እንኳን የሰው የእንስሳም ባህርይ አልነበረም፤ አይደለምም። እናቶችን እያስለቀሱ “የእናቶች ዘመቻ” በሚል የዘመቻ ስያሜ መፎለል፣ ወንድም ላይ እየተኮሱ “ተቆጣጠርኩ” ማለት የጭካኔና የአረመኔነት ተግባር እንጂ ሰዋዊ ተግባር ሆኖም አያውቅም። በመሆኑም ይወገዛል፤ ጊዜው ሲደርስም ያስጠይቃል።
ህዳር 24/2013 ዓ/ም የሰሜን እዝ መከላከያ ላይ በአረመኔያዊ ሁኔታ ጭፍጨፋ በማካሄድ የተጀመረው የጁንታው አሸባሪ ተግባር እነሆ ሰንኮፉ እስከአሁንም አልተነቀለም። በዚህ ቢሉት በዚያ ፊቱን ወደ ሰላም ሊመልስ፤ ለውይይትም ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ሊመጣ አልቻለም። የባህርይ ነውና ዛሬም እዚያው ሽምቅ ውስጥ ነው ያለው።
ሺህ ጊዜ ዕርምጃ ቢወሰድበት፣ ሚሊዮን ጊዜ ቢነገረው የማይሰማው ሽብርተኛው ቡድን የሚሰጠውን የሰላም አማራጭ ሁሉ እያሽቀነጠረ በመጣል እራሱን ወደ ግብአተ መሬት አፋፍ እያስጠጋ ይገኛል። የሰላም ጥሪ ከፍተኛው ደረጃ በመሆኑ የሚታወቀውንና መንግሥት ለህዝብ ጥቅምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሲል ተግባራዊ ያደረገውን የተኩስ አቁም ውሳኔ ከምንም ባለመቁጠርና ጆሮውን ዳባ በማልበስ በራሱ ላይ ቁማር እየቆመረ ሲሆን፤ በራስ ላይ መቆመር ደግሞ መጨረሻው እርስ በእርስ መበላላት ነው።
ችግሩ በራሱ ላይ መቆመሩ፣ ተራ የፖለቲካ ሽቀላ ውስጥ መግባቱና እራሱን በራሱ ማጥፋቱ አይደለም፤ ከሁሉም የከፋው ችግር በህዝብ ስጋና ደም፤ ነፍስና ህይወት መጫወቱ፣ በተለይም በሴቶች፣ እናቶችና ሕፃናት መብት ላይ እስከ መጨረሻው የሀጢያት ጥግ ድረስ መጓዙ ነው።
አስር የማይሞሉ ግለሰቦች ከነበርንበት የምቾት ማማ (comfort zone) ለምን አሽቆለቆልን፣ ከተቆናጠጥነውና ለዕድሜ ልክ ካሰብነው የስልጣን እርካብ ለምን ተሽቀነጠርን፤ ከህዝብ ጫንቃ ላይ ለምን ወረድን፣ ከተዘፈቅንበት የሙስናና ሀብት ምንጭ ለምን ተንሳፈፍን ወዘተ በሚል ኩርፊያ ወደ መቀሌ በመኮብለል፣ ለህዝቡ አዛኝ ቅቤ አንጓች በመሆን፣ የትግራይ ህዝብ ላይ አንዳች የመጣ አደጋ እንዳለ በመስበክ፤ አብዝቶም ደረቅ ፕሮፓጋንዳን በመንዛት ይኸው አገርና ህዝብን፤ በተለይም ቆሜለታለሁ የሚሉለትን የትግራይ ህዝብ ለመከራ በመዳረግ እስከአሁንም የንፁሐንን ደም እያፈሰሰና እያስፈሰሰ፣ ሕፃናትና ሴቶችን ለጦርነት እየማገደ ይገኛል።
ህወሓት አዳዲስ ዘዴን መፍጠር እርሙ ነው፤ ወደ ዘመናዊነት መምጣት አይደለም መቅረብ እንኳን አይፈልግም፤ አይሆንለትምም። ሥራውም ሆነ አሠራሩ ገና ሲፈጠር “ሀ” ብሎ የጀመረውን የሙጥኝ ከማለት ውጪ ሌላ የተሻሉ አማራጮችን በመፍትሔነት ማምጣት ለእሱ ዕጣ ክፍሉ አይደለም። ለእሱ በዛሬና ትናንትና መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም። ሁሌም ያው ነው። ያው ነው ብሎ ስለሚያስብም የሚደልቀው ከበሮም ሆነ ድቤ ያውና ተመሳሳይ ነው። ድርጅቱ ከዕድሜው ውጪ የጨመረው ነገር የለም። ውሽት እርስቱ ነው፤ ጥፋትና ቅጥፈት የነፍሱ ክፋይ የህይወቱ እስትንፋስ ሲሆኑ፤ ካልገደለ፣ ካልዋሸ፣ ካላወደመ ወዘተርፈ ፋታ የለውም። ምን ጊዜም የመኖሩ ማረጋገጫ ሸፍጥና ሴራ እንጂ ሌላ ሆኖ አያውቅም። ይህ ደግሞ ዕድሜ ላለፉት ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ዓመታት በሚገባ የተመለከትነው ጉዳይ ነው።
በሀውዜን እልቂት የሚታማው ህወሓት ዛሬም ያንን የጎሬላ ስትራተጅ የሙጥኝ እንዳለ ነው (ገበያ ውስጥ ውጊያ መክፈት የመክፈት ስልት)፤ ከ”ደመሰስኩ” ፕሮፓጋንዳ ገና አልተላቀቀም። ሁሌም “ገደልን” እንጂ ሞትንን አያውቅም (የሴኩ ቱሬ ሌጋሲ በጌታቸው ተጠናክሮ ቀጥሏል)። ለንፁሐን የሚሰጠው ቦታም ሆነ ያለው ግምት ከዜሮ በታች ብቻ ሳይሆን ከሰብዓዊነት ጭምር የተነጠለ ነው። ሲበዛ ጨካኝ፣ እጅግ ሲበዛም ግፈኛ ነው።
በርእሳችን “አሸባሪነት፤ ባ’ዲስ አንኮላ አሮጌ ቅራሪ” ያልንበት ዋና ምክንያት ከሞላ ጎደል ከላይ የጠቃቀስናቸው ባህርያቱን ዛሬም ድረስ ከብብቱ ስር አለመጣሉና ለዛሬ የአሸባሪ ማንነቱ ተግባራት ማስፈፀሚያ እያደረገ መገኘቱ ነው። በተለይም “ደረስኩ”፣ “ደመሰስኩ”፣ “ያዝኩ”፣ “ተቆጣጠርኩ”፣ “ማረኩ”፣ “ወረርኩ”፣ “አላማጣ፣ ኮረም፣ ወልዲያ … ገባሁ”፤ “ለዳግም መንግሥትነት ደቂቃ ብቻ ቀረኝ” በማለት ሌት ተቀን በሚነዛው ለዛ ቢስ ፕሮፓጋንዳ፣ በሚያራምደው የሀሰት እምነት (Delusion)፣ ከጀርባቸው ፖስተርና የአካባቢ ስሞችን፤ታፔላዎችንና ፎቶግራፎችን በመለጠፍ “ተመልከቱ” በማለት ለአላማቸው ሲሉ የተጃጃሉትን የውጭው ዓለም ሰዎችን ልብ ለመርታት የሚያደርገው የሂትለር ህዝብ ግንኙነት ሹም ሲያደርገው የነበረውን ዓይነት ተግባር (ሂትለር ለዛ ዓይነቱ ውድቀት የበቃው በህዝብ ግንኙነቱ ሹም ሊታረም ባልቻሉ ተደጋጋሚ ስህተት ምክንያት መሆኑን ማስታወስ ይገባል) ቀጥሎበታል፡፡
ዘልአለም አለሙን ከነበረ አስተሳሰቡ (Mindset) – ጎጠኝነት፣ ዘረኝነት፣ ሴረኝነት ወዘተ – በፍፁም መለወጥና ወደ ዘመኑ መምጣት አለመቻሉ፤ እንዲሁም ዛሬም ድረስ “እገሌ ብሄረሰብ ጠላት ነው” ከሚልና ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍልስፍናን፣ የርእዮተ ዓለም ቅኝትን፣ እውቀትን፣ ማሰላሰልን፣ አዲስ ሃሳብ የማፍለቅ አቅምን የማይጠይቅ፣ ለራስ ጥቅም ብቻ ሲባል የተቀረፀ የፖለቲካ አጀንዳን ሰቅሎ ከጦርት ወደ ጦርነት፣ ከደደቢት ወደ ደደቢት፣ ከመንግሥትነት እንደገና ወደ መንግሥትነት (ምኞት ጥሩ ቢሆንም) … መሽከርከርን ዕድሌ፣ ዕጣዬ፣ ክብሬ፣ ማእረጌ፣ ጌጤ ብሎ አጥብቆ ይዞ መገኘቱ ነው – “አሸባሪነት፤ ባ’ዲስ አንኮላ አሮጌ ቅራሪ” ማለት ግድ የሆነብን።
ህወሓት መንግሥት በነበረባቸው የመጨረሻ ዓመታት (በኃይለማሪያም ደሳለኝ አስተዳደር ዘመን) በሀገሪቱ ቅጥ አጥቶ ህዝብን ሲያስለቅስ፣ ወደ እማይመለስ አመፅም ገፋፍቶ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግርና ከዚህ በመለስ እንኳን ሊባል ያልተቻለውን ሙስና አስመልክቶ የተካሄደ ጥናት ግኝት ላይ የፓርቲውና የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት (“ከፍተኛ አመራር” የሚባሉቱ) ውይይት ሲያደርጉ በነበረበት ወቅት (በመገናኛ ብዙሃን ተላልፏል) ከከፍተኛ አመራሮች አንዱ የሆኑት አባይ ፀሐዬ “ይህን ችግር ባስቸኳይ በዘመቻ መልክ ካልፈታነው መበላታችን ነው” (ምንም እንኳን ደብረ ፂዮን፣ በረከትና አንዳንዶች “በዘመቻ” በሚለው ባይስማሙና “መፈታት አለበት” በሚለው ቢስማሙም) ማለታቸው የማይረሳ ብቻ ሳይሆን በታሪክም የሚጠቀስ ነው።
ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል፣
በማለት ሰለሞን ቀድሞ ተናግሮታል። (ሲል መሀሙድ እንዳዜመው)
አሁን ጥያቄው “ታዲያ የመበያው ቀን ሲደርስ ይህ ሁሉ አልበላም ባይነትን ምን አመጣው ነው፤ ምን አመጣው???” ለምንስ ሲባል አገር ትታመሳለች? ለምንስ ሲባል ንፁሐን ህይወታቸውን ይቀጠፋሉ? የትግራይ ህዝብስ ምን በወጣው፣ ምንስ ባደረገ ለዚህ ዓይነቱ ኢሰብዓዊ ተግባር ይጋለጥ? ሁሉም ሊወያይባቸው፣ የጋራ አቋምም ሊይዝባቸው የሚገቡ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች!!!
ማጠቃለያችን የሚሆነው ህዝብን፣ በተለይም የትግራይ ሕፃናትን ለማስጨረስና ምንም ዓይነት ዘላቂነት የሌለውን ተራ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ድጋፍ (ፔትሮ ዶላር ዛሬም ይኖር ይሆን እንዴ? አዎ፣ አለ።) ለማግኘት ሲባል እየተደረገ ያለውን፣ “ፕሮፓጋንዳ” ለመባል እንኳን የማይበቃውን የቃላት ኳኳታ አስመልክተን አንዳንድ ትዝብቶችን ለመጋራት ሲሆን፤ ዋናው ትዝብታችንም የሰሞኑ “ደረስኩ”፣ “ደመሰስኩ”፣ “ያዝኩ”፣ “ተቆጣጠርኩ”፣ “ማረኩ”፣ “ወረርኩ”፣ “አላማጣ፣ ኮረም፣ ወልዲያ … ገባሁ” በሚል የሚደለቁ ከበሮና ድቤዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ “ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም” እንዲሉ ተግባሩ ለህወሓት የባህርይ ጉዳይ ነውና አይደንቅም ለማለት ነው። እንኳን ወደ ፊት መግፋ ቀርቶ ለጊዜውም የያዘውን አካባቢ በቅርቡ ማስረከቡ አይቀሬ ነው፡፡
ግርማ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2013