ከአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት የመጡ እንግዶቿን “እንኳን ደህና መጣችሁ” ብላ የተቀበለችው ጅግጅጋ፤ ከየካቲት ስምንት 2011 ዓ.ም ጀምሮ በጉያዋ አቅፋ አክርማ ትናንት በሰላም ግቡ ብላ ሸኝታለች፡፡ ተሳታፊዎችም ስለ ጅግጅጋ ቀድሞ የነበራቸውን ስሜትና በቆይታቸው ያዩትን በማነጻጸር ስለ ሰላም ባለቤትቷ ተናግረውላታል፡፡ ፎረሙ አሉባልታን ሽሮ ይቻላልን በተግባር ቀይሮ ማሳየት እንድትችል እድል የፈጠረላት መሆኑንም በምስጋና አጅበው ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ ተሳታፊዎች መካከል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ትዕግስት ዘገየ አንዷ ናቸው፡፡ ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት “ፎረሙ ሲታሰብ በብዙዎቻችን ዘንድ ስጋት ነበር” ያሉት ወይዘሮዋ፤ ስጋቱም የተፈጠረባቸው በጅግጅጋና አካባቢዋ የነበረው የጸጥታ ጉዳይ አሳሳቢ ስለነበር እነርሱም ይሄንኑ በመስማታቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡
በጉዞ ላይ እያሉም በዓሉ በሰላም ይጠናቀቅ ይሆን፣ የሚለውን ስጋት አሳድሮባቸው እንደነበርም አውስተዋል፡፡ ነገር ግን በከተማዋ ከደረሱበት ቀን ጀምሮ በህዝቡ የነበረው አቀባበል እጅጉን ልዩ እንደነበር፤ ባለስልጣናቱ ሳይቀር እንግዶችን በያሉበት እየሄዱ ሲጠይቁና ምን ጎደለ እያሉ በፍቅር ሲንከባከቡ ማየቱ የነበረውን ስጋት በአንዴ ሸርሽሮ የሰላምና ደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡
ወይዘሮዋ እንደሚናገሩት፤ ከጅምሩ የነበረው አቀባበልና መስተንግዶ እስከመጨረሻው ቀን ድረስ መዝለቁ ከታሰበውና ከተጠበቀው በላይ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በተሳታፊው ላይ መተማመንን የፈጠረ፣ ለበዓሉም በሰላምና በድምቀት መጠናቀቅ ትልቅ ሚና የተጫወተ ተግባር ነው፡፡ እናም ክልሉም ሆነ ከተማው የሰላም ቦታ፤ ህዝቡም የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉ የጸና መሆኑን በተግባር አሳይቶ አረጋግጧል፡፡
ይህ ተግባርም ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ መሆን የሚገባው ሲሆን፤ ከተሞችም በተለይ እንግዳን እንዴት መቀበል እንደሚገባና እንዴት በህብረት መስራት እደሚቻል ከጅግጅጋ ከተማና ነዋሪዎቿ መማር ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የጅግጅጋ ነዋሪዎች በህብረት ይሰራሉ፤ ሁሉንም ሰው በፍቅር ያያሉ፤ ችግሮችን ለመፍታትም ሳይታክቱ ይሰራሉ፡፡ ቀጣይ አዘጋጅ ከተሞችም፣ በፍቅር ህዝብ ተቀብሎ የማስተናገድን ልምድ ከጅግጅጋ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
“ጅግጅጋ፣ በሰላሟም ሆነ በእድገቷ ከጠበቅኋት በላይ ሆና ነው ያገኘኋት” ያሉት ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ወለንጪቲ ከተማ የበዓሉ ተሳታፊ የሆኑት አቶ አብሹ አልዪ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ወደ ጅግጅጋ ሲመጡ ከመነሻው ስጋት ስለነበራቸው እየፈሩ ነበር ጅግጅጋ የገቡት፡፡
ሆኖም ሲደርሱ እንደተባለው ችግር ያለባት ሳትሆን ምንም ችግር የሌለባት የሰላም ከተማ ሆና አግኝተዋታል፡፡ በከተማዋ ትንሹም ትልቁም ሰው አክባሪና እንግዳ ተቀባይም ነው፡፡ በፍቅር ተቀብለውም በደስታ አስተናግደዋቸዋል፡፡ ለጸጥታና ሰላማቸውም ከጸጥታው ሃይል ያልተናነሰ ሰርተዋል፡፡ በዚህም አሉባልታን ሽረው የሰላም አውድ መሆን መቻላቸውን በተግባር ያሳዩ እንደመሆናቸው፤ በዚህ ረገድ ከጅግጅጋ ከተማ ተሞክሮ በመውሰድ ሁሉም ከተሞች በየአከባቢያቸው ሊተገብሩ ይገባል፡፡
ፎረሙ፣ የሶማሌን ህዝብ እንግዳ ተቀባይነትና ወንድም ወዳድነት ብቻ ሳይሆን ጨዋነቱንም በቅርበት ማየት የተቻለበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስትሩ አቶ ዣንጥራር አባይ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፤ ፎረሙ ውጤታማ ነበር፡፡ ውጤታማነቱም ከሰባት ወራት በፊት በክልሉ በተለይም በከተማው የነበረውን ችግር ተፈትቶ ይሄንን አይነት ፎረም በድምቀት አዘጋጅቶ በሰላም ማጠናቀቅ መቻሉ ነው፡፡ ይህ ሰላም የተገኘውም በህዝቡ ስራ ነውና የጅግጅጋ ህዝብ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ እንግዳ ተቀባይና ሰው ወዳድ ብቻ ሳይሆን ጨዋ ህዝብ መሆኑንም አቅፎ አሳይቷል፡፡
እንደ ሚንስትሩ ገለጻ፤ መድረኩ በሁሉም አገሪቱ ያሉ ከተሞችን በአንድ ያገናኘና ከተሞቹም በሰባት ቀናት ቆይታቸው ለፎረሙ ድምቀትና በስኬት መጠናቀቅ የድርሻቸውን ተወጥተዋል፤ ከከተማ እስከ ክልል ብሎም ፈዴራል ያሉ የጸጥታ አካላትም የማይተካ ሚና ተወጥተዋል፡፡ እናም ለተሳታፊ ከተሞችም ሆነ ለጸጥታ ሃይሉ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን በመጠቆም፣ ለውጡ እንዲቀጥል መስራት እንደሚገባ የገለጹት ሚንስትሩ፤ ለውጡ የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎችን መመለሻ እንደመሆኑ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ተግባራት ሊወገዱ፤ የሚናፈሱ ወሬዎችም በቃ ሊባሉ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፎረሙን የቃል ኪዳን ቦታ በማድረግና ተደምሮ ሁለት መሆንን ሳይሆን አንድ መሆንን በማጉላት ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልጽግና የሚሰሩበትን እድል መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በሶማሌ ክልል ህዝብ የተገለጸውን ሰው አክባሪ፣ ጨዋና እንግዳ ተቀባይ የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለማገልገል ቃል መግባት እንደሚያስፈልግ በመግለጽም፤ የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ይሄን ጨዋ ህዝብ ለማገልገል ከጎናቸው ካሉ አመራሮች ጋር የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
“እንኳን በሰላም ወደ ክልላችንና ከተማችን መጥታችሁ በዓሉ ላይ ተገኛችሁ፤ በዓሉም እንኳን በሰላም ተጠናቀቀ፤” ያሉት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ በዓሉ በድምቀት ተካሂዶ በሰላም መጠናቀቁ የነበሩ ስጋቶችና አሉባልታዎችን በማያሻማ መልኩ ያከሸፈና የከተማዋንም ሆነ የክልሉን ህዝብ ሰላማዊነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ በዓሉ ከተሞች እርስ በእርስ የሚተዋወቁበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እንደመሆኑ የክልሉ ከተሞችም በዚሁ ውስጥ የድርሻቸውን ተወጥተዋል፤ ለራሳቸውም ልምድ ወስደዋል፡፡ በዚህ መልኩ ዓላማውን እንዲያሳካ በተደረገው ዝግጅት ውስጥ ደግሞ ሊመሰገኑ የሚገባቸው በርካታ አካላት አሉ፡፡ በዚህም በዓሉ በድምቀት እንዲካሄድና በሰላም እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ላበረከቱ የጸጥታ ሃይሎች፣ በተለይም የክልሉ ህዝብ ከልብ የመነጨ ምስጋና ይገባዋል፡፡
እንግዶቹን በፍቅር ተቀብሎ በማስተናገድ የድርሻውን ለተወጣው የጅግጅጋና አከባቢው ህዝብም የላቀ ምስጋና በማቅረብም፤ የአሉባልታ ስጋት ሳይፈትናቸው ለዚህ በዓል ድምቀት የድርሻቸውን ላበረከቱ እንግዶችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የመልስ ጉዟቸውም የቀና እንዲሆንና በሰላም ወደየመጡበት እንዲገቡም ተመኝተዋል፡፡
በመጨረሻም የዘጠነኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም እንድታዘጋጅ አሶሳ ከተማ መመረጧን በማብሰር የተጠናቀቀው ይህ ፎረም፤ ከውጭ አገራት በበዓሉ ላይ ተሳታፊ ለሆኑ እህት ከተሞች ለጅቡቲ፣ ለበርበራና ሀርጌሳ ከተሞች የምስጋና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ ከዚህም ባለፈ ለበዓሉ መሳካት የስፖንሰር ድጋፍ አድርገዋል የተባሉ የአገር ውስጥና ዓለማቀፍ ድርጅቶችም የምስጋና ሥጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ውጤታማ ተብለው የተመረጡ ማህበራት፣ አንቀሳቃሾች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ተቋማት እንደየምድብ ደረጃቸው እውቅና፣የሜዳሊያ፣ የዋንጫና የላፕቶፕ ሽልማቶችም ተበርክቶላቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
ወንድወሰን ሺመልስ