በሽበርተኝነት ከተፈረጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት አላችሁ በማለት የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም በተጠርጠሩ የመርማሪ ፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡
ክስ የተመሰረተባቸውም ኮማንደር አለማየሁ ሐይሉ፣ ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፋይኔ ወልደ ሚካኤል፣ ዋና ሳጅን ኪዳኔ አሰፋ ሸማ፣ ዋና ሳጅን ርእሶም ክህሽን፣ ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ በዳዳ፣ ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሃሰን መኮንን፣ ምክትል ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን፣ ረዳት ኢንስፔክተር መንግስቱ ታደሰ አየለ፣ ረዳት ኢንስፔክተር መንግስቱ አለማየሁ ኃይሉ ሁንዴ እና ኢንስፔክተር ስንታየሁ ፈጠነ ለገሰ ናቸው፡፡
የክሱ ዝርዝር እንደሚያስረዳው በፌዴራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ወንጀል መርማሪ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት የግል ተበዳዮችን በኤሌክትሪክ ገመድ በመግረፍ፣ በብረት ጉጠት የጣት ጥፍራቸውን በመንቀል ፣ በሽብርተኝነት ተፈረጀው ከነበሩ የአርበኞች ግንቦት ሰባት እና የኦነግ የፖለቲካ ድርጅቶች አባል ናችሁ በማለት ሽጉጥ አፉቸው ውስጥ በመክተት፣ በግንብ ላይ በተሰካ ብረት ላይ ለረጅም ጊዜ እጃቸውን በካቴና በማሰርና በማንጠልጠል፤ ከግድግዳ ጋር በማጋጨት፣ ፊታቸውን በጥፊ በመምታት፣ የፊትንና የጺም ጸጉር ፒንሳ በሚመስል ነገር በመንጨት እንዲሁም ራሳቸውን በሚስቱበት ወቅት ውሃ በመድፋት በግድ የአሸባሪ ድርጅቶች አባል መሆናቸውን እንዲያምኑ በማድረግ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ፈጽመዋል፡፡
በተከሳሶች ላይ የቀረበው ክስ 78 ክሶችን የያዘ ሲሆን በግል ተበዳዮች ላይ ምርመራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ተበዳዮችን እጃቸውን በካቴና በማሰር፣ በምርመራ ክፍል ውስጥ በተዘጋጀ ሚስማር ላይ በማጠልጠል፣ በጣት እንዲቆሙ ማድረጋቸው የክስ መዝገቡ ያሳያል፡፡
እነዚህ ተከሳሾች በኤሌትሪክ ገመድ በመግረፍና በግንባር ግድግዳ በማስገፋት፣ በብልታቸው ላይ ሁለት እስከ አራት ሊትር ሃይላንድ ውሀ በማንጠልጠል ከ2 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት እንዲቆዩ በማድረግ፣ በኤሌክትሪክ በማስነዘር ፣ብልታቸውን በፒንሳ በመሳብ የጭንቀት ህመም እና ተያያዥ ድብርት እንዲደርስባቸው አድርገዋል ነው የተባለው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በቀዝቃዛና ጨለማ እስርቤት ውስጥ በማሰር፣ በእግራቸው መሀል እንጨት አስገብቶ በመገልበጥ የውስጥ እግራቸውን በኤሌትሪክ ገመድ በመግረፍ፣ በምርመራ ክፍሉ በተዘጋጀ ሚስማር ላይ በማንጠልጠል ለረዥም ሰዓት እንዲቆዩ በማድረግ፤ አድካሚ እና ከባድ ስፖርት በማሰራት፤ አፍንጫቸው ውስጥ እስክሪብቶ በመክተት፣ መቀመጫቸውን እና ጀርባቸውን ውሃ እየደፋ በኤሌክትሪክ ሽቦ በመግረፍ፣ ጺማቸውን በመንጨት ፣ብልታቸውን በቀጭን ሲባጎ በማሰር በግል ተበዳዮች ላይ ሞራላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት አስከትለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ነሀሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በቂሊንጦ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ላይ በደረሰው የቃጠሎ አደጋ ምክንያት በተጠረጠሩ ተጠርጣሪዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲያደርጉ ታዘው ከመስከረም 20 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት የምርመራ ስራቸውን ሲያከናውኑ እጃቸውን በካቴና አውራ ጣታቸውን ደግሞ በሲባጎ በማሰር፣ ሚስማር ባለው ጣውላ በመምታት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ ውሃ እየደፉ በመግረፍ ፣በደም የተነከረ እስፖንጅ አፉቸው ውስጥ በመጠቅጠቅ ከፍተኛ ስቃይ በማድረስ እና በምርመራ ክፍሉ ውስጥ ጣሪያ ላይ በማንጠልጠል ምርመራ ያደረጉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ተገቢ ያልሆነ የአሰራር ዘዴን መከተል ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾችም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 12ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ በእጃቸው እንዲደርስ በማድረግ የዋስትና መብት ጥያቄን ለማስከበር የሚደረገውን ክርክር ለመስማትና ክሳቸው በችሎቱ እንዲነበብ ለየካቲት 22ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙን ከፌዴራል ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል